የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፣ የመከላከያ ህብረት ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ሰራዊታችን በፈፀማቸው ውጊያዎች የማይተካ ሚና መወጣቱን አረጋገጡ ፡፡

ኢትዮያን ለማዳን በተካሄደው የህልውና ዘመቻ እና በስራ አፈፃፀማቸው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሎጀስቲክስ የሰራዊት አባላት የማዕረግ እድገት፤ የሜዳይ፤ የእውቅናና የምስጋና ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፣ የመከላከያ ህብረት ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የተቋሙን 80 በመቶ ሃብት የያዘና በውስጡ በርካታ የሙያተኛ ስብጥር በመያዙ ውግያን በመደገፍ ያስመዘገቡት ስኬት የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከህግ ማስከበር ዘመቻው በፊት ሽብርተኛው በዋና መምሪያው ስር የሰገሰጋቸው አባላቶች የሎጀስቲክስ ድጋፍ ስራውን ለማደናቀፍ የሸረቡትን ሴራ በአጭር ጊዜ በማምከን ፣ ዋና መምሪያውን በአዲስ አደረጃጀት አዋቅሮ ለተልዕኮ ማዘጋጀት የሎጀስቲክስ አመራሩ ውጤት በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡

የመከላከያ ህብረት ሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል አብዱራህማን ኢስማኤል በበኩላቸው ፣ ሃገርን ለማዳን ባደረግነው ውጊያ አሸባሪው ሃይል ከጥቅም ውጪ ያደረጋቸውን ከቀላል እስከ ከባድ ተሸከርካሪዎችና መሳሪያዎችን በመማረክና ከደበቀበት ጫካ በመልቀም አስፈላጊው ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ስራ በመመለስ ሰራዊቱ እንዲጠቀምባቸው ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

የሎጀስቲክስ አባላት ቀን ከሌት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሰራዊቱ የሚያስፈልጉ በርካታ ሎጀስቲካዊ አቅርቦቶችን በወቅቱ በማድረስ ሰራዊቱ ለሚያደርጋቸው ውጊያዎች የጀርባ አጥንት በመሆን ማገልገላቸውንም ሌተናል ጀነራል አብዱራህማን እስማኤል ተናግረዋል፡፡

በስራ አፈጻፀማቸው አጥጋቢ ውጤት አስመዝግበው የማዕረግና የሜዳይ ሽልማት የተበረከተላቸው አባላት በሰጡት አስተያየት ፣ ሽልማቱና የእውቅና አሰጣጡ በቀጣይ ለሚጠበቅባቸው ተልእኮ ግዳጃቸውን በከፍተኛ ሃላፊነትና ተነሳሽነት ለመወጣት እንደሚያነሳሳቸው ገልፀዋል፡፡

በስነ-ስርአቱ ላይ የማዕረግ ዕድገት፤ የሜዳይና የእውቅና ሰርተፍኬት ለሎጀስቲክስ ሙያተኞች የተሰጠ ሲሆን ፣ በህልውና ዘመቻው ላይ የበኩላቸውን ድጋፍ ላበረከቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፤ ለተለያዩ ሲቪል ተቋማትና ድርጅቶች የእውቅናና የምስጋና ሰርተፍኬት ተሰጥቷል፡፡

ብስራት ጸልይ
ፎቶግራፍ ብርቱካን ረጋሳ

Leave a Reply