ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘሩ ከ3 ሺህ 400 በላይ የሳይበር ጥቃቶችን መመከት መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በሳይበር ደህንነትና ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ 96 በመቶ የሳይበር ጥቃትን የመመከትና የመቋቋም አቅም መገንባት ችላለች፡፡

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘሩ ከ3 ሺህ 400 በላይ የሳይበር ጥቃቶችን መመከት ተችሏል ነው ያሉት፡፡ ጥቃቶቹ ተፈጽመው ቢሆን ኖሮ በአገር አቀፍ ደረጃ አደገኛ ሁኔታ ይፈጥሩ እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡

ከጥቃት ሙከራዎች መካከል 33 በመቶ የሚሆነው የመሰረተ ልማት ቅኝት፣ 25 በመቶ የድረ-ገፅ ጥቃት፤ 21 በመቶ ሰርጎገብነት፤ 19 በመቶ የማልዌር ጥቃት እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ ገፆችን መጥለፍ እና የኦንላይን ማጭበርበር መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የፋይናንስ ተቋማት፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ አምራች ተቋማት እና ሚዲያዎች ደግሞ ዋነኛዎቹ የጥቃት ኢላማዎች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ በተጨማሪም ጥቃት የደረሰባቸውን በፍጥነት ወደ አገልግሎት መመለስ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

“የሳይበር ደህንነት ጥቃት የዓለማችን ቀጣዩ ወረርሽኝ ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት መከላከል ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ የሳይበር ህግጋትን አክብሮ በመጠቀም ለሳይበር ጥቃት መከላከል የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዲጂታል ሉዓላዊነት የሁሉም አገራት ስጋት በመሆኑ ሚዲያዎች ጉዳዩን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን በስፋት እንዲሰሩም ማሳሰባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው

Leave a Reply