ምክር ቤቱ ጡረታ ለማሻሻል የቀረቡትን ሁለት ረቂቅ አዋጆች አፀደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባው የመንግስት ሰራተኞች እና የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ጡረታ ለመደንገግ የቀረቡትን ሁለት ረቂቅ አዋጆች በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡

የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ የመንግስት ሰራተኞች የጡረታ ረቂቅ አዋጅን አስፈላጊነት በተመለከተ የአገራችን ማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ አንዱ አካል በመሆኑ የመንግስት ሰራተኞችን የጡረታ ፈንድ ቀጣይነት በማረጋገጥ ኢንቨስትመንትን በማዳበር ግልጽ የሆነ የአስተዳደር ስርአት እንድኖር ለማደረግ ታሳቦ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ አያይዘውም ጠንካራ እና አስተማማይ ፈንድ እንዲኖር በማድረግ በጡረታ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ወደ ኢንቨስትመንት በመቀየር ጡረተኞች ቢያነስ በእየሶስት ዓመቱ ደመወዛቸው እንዲሻሻል ማድረግ እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

ሰብሳቢው አክለውም የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ጡረታ ረቂቅ አዋጅ አስፈላጊነትን በተመለከተ የማህበራዊ ዋስትናን ስርአት በማሳፋፋት ለማህበራዊ ፍትህ ለድህነት ቅነሳቀው አስተዋፅኦ እንዳለው ታሳቦ የቀረበ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከሰራተኞች የጡረታ ዕድሜ ጣራ ጋር በተያያዘ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ጥያቄ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት 60 ዓመት ያገለገሉ ባለሙያዎችን ተቋሙ ካመነበት ለአምስት ዓመት ለሁለት ጊዜ በማራዘም እስከ 70 ዓመት ማሰራት የሚቻል እንደሆነ በውሳኔ ሃሰቡ ላይ መካተቱን አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው የግል ድርጅት ባለሃብቶች እራሳቸውን ተቀጣሪ በማድረግ በከፍተኛ ደመወዝ የተቀጠሩ አድረገው ከመንግስት ከፍተኛ የጡረታ ገንዘብ ያስቀሩ እንደነበርና አዋጁ ይህን አሰራር ማስተካከል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱ በሁለቱም ረቂቅ አዋጆች ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ የመንግስት ሰራተኞች ጡረታ ለመደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሁለት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ እና የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ጡረታ ለማደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአንድ ተቃውሞ፣ በሶስት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በውሎው የመንገድ ትራንስፖርት ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ለዝርዝር እይታ ለከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን በማህበራዊ ገጹ ላይ ዘግቧል።

Leave a Reply