የስብዕና ማማ “እጄ እንደተቆረጠ አላስብም፣ አገሬን ለማዳን ባልሳተፍ ኖሮ መኖር አልችልም ነበር” ዳግም ዘማቹ ጀግና

እጄ እንደተቆረጠ አላስብም፤ የማስበው ሙሉ እንደሆንኩ ነው፡፡ የሰው ልጅ እግሩ ወይንም እጁ አሊያም ዓይኑ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእኛ መጥፋት የሌለበት ህሊናችን ነው፡፡ መኖር ያለበት የምናስብበት አዕምሮ ነው፡፡ አዕምሯችን እስከሠራ ድረስ ማንኛውንም ነገር መሥራት እንችላለን። በሕይወት መትረፌ በራሱ ዕድለኝነት ነው። ሊያቆስለኝ ሳይሆን ሊገድለኝ የመጣ መሣሪያ ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ተረፍኩኝ፡፡ እጄ ስለተቆረጠ ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር አይሰማኝም፡፡ ውስጤ እጅግ ደስተኛ ነው፡፡ አዕምሮዬ የሚያስበው ይከፋኝ የነበረው ለአገሩ አስተዋፅኦ ባላደርግ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ባልሳተፍ ኖሮ መኖር አልችልም፤ ያመኝ ነበር፡፡ አሁን ግን የምችለውን አድርጌ ስለሆነ ውስጤ ደስተኛ ነው፡፡

በቀድሞ አጠራር ወሎ ክፍለሀገር ቦረና አውራጃ ከላላ ወረዳ 025 ቀበሌ ተወለዱ፡፡ እስከ 1983 ዓ.ም ቤተሰባቸውን በሥራ በመርዳትና ትምህርታቸውን በመከታተል አሳለፉ፡፡ የኢህአዴግን መንገድ የተቀላቀሉት በ1982 ዓ.ም ነበር፡፡ መጀመሪያ በሕዝባዊ ሸንጎ ተቀላቀሉ፡፡ ከዚያም በ1983 ዓ.ም ደግሞ በራሳቸው ፍላጎት ወደ ውትድርና ገቡ፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ነፃ የምትወጣ ስለመሰላቸውና በትግል ነፃ የምትሆን ከሆነ የዜግነቴን ልወጣ ግድ ይለኛል ብለው ወደ ውትድርናው ሕይወት ገና በለጋ ዕድሜያቸው መግባታቸውን ያስታውሳሉ፡፡

ኮሎኔል ሁሴን ለ31 ዓመታት በአገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ አገልግለዋል፡፡ አሸባሪ የሕወሓት ጁንታ በአገር መከላከያ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ክህደት ሲፈፅም በጡረታ ከተገለሉበት ዳግም ወደ አገር መከላከያ ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበው ጠላትን ሲያደባዩ ቆይተዋል፡፡ ጠላትን ክፉኛ በመምታት ድል አስመዝግበዋል፡፡ ከሚመሩት ሰራዊት ጋር ሆነው በርካታ ጀብዶችን ፈፅመዋል፡፡ ከዕለታት በአንዲት ቀን ግን ከጠላት በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ እጃቸው ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡ በሕክምና ሲረዱ ቢቆዩም እጃቸው ጥቅም ስለማይሰጥ በሐኪሞች ውሳኔ አንድ እጃቸው ተቆርጧል፡፡

ኮሎኔል ሁሴን አህመድ ግን ‹‹እጄ እንደተቆረጠ አላስብም፤ የማስበው ሙሉ እንደሆንኩ ነው›› ይላሉ። የሰው ልጅ እግሩ ወይም እጁ አሊያም ዓይኑ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእኛ መጥፋት የሌለበት ህሊናችን ነው፡፡ መኖር ያለበት የምናስብበት አዕምሮ ነው፡፡ አዕምሯችን እስከሠራ ድረስ ማንኛውንም ነገር መሥራት እንችላለን፡፡ በሕይወት መትረፌ በራሱ ዕድለኝነት ነው። ሊያቆስለኝ ሳይሆን ሊገድለኝ የመጣ መሣሪያ ነበር። አጋጣሚ ሆኖ ተረፍኩኝ፡፡ እጄ ስለተቆረጠ ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር አይሰማኝም፡፡ ውስጤ እጅግ ደስተኛ ነው፡፡ አዕምሮዬ የሚያስበውና ይከፋኝ የነበረው ለአገሬ አስተዋፅኦ ባላደርግ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ባልሳተፍ ኖሮ መኖር አልችልም፡፡ ያመኛል፡፡ አሁን ግን የምችለውን አድርጌ ስለሆነ ውስጤ ደስተኛ ነው›› ሲሉ የከፈሉትን መስዋትነት ለኢትዮጵያ ቢያንስ አንጂ አይበዛም ይላሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ውትድርና ሲገቡ የመጀመሪያ ምድብዎ ምን ነበር?

ኮሎኔል ሁሴን፡- ወደ ውትድርና ስገባ በእግረኛ ክፍለ ጦር ውስጥ ነበርኩ፡፡ እግርኛ ክፍለጦር የቆየሁት እስከ 1984 ዓ.ም ድረስ ነው፡፡ ከዚያን በኋላ በሙሉ ያገለገልኩት በሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ውስጥ ነው።ያደኩት ፈጠን ብዬ ነው፡፡ የታንከኛ ሻምበል አዛዥ፣ የታንከኛ ሻለቃ አዛዥ፣ የታንከኛ ሬጅመንት አዛዥ፣ የሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ፣ የስምንተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ፣ ሎጂስቲክስንም በተለያዩ ኃላፊነቶች ቦታዎች ስመራ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከእግረኛ ወደ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የተዘዋወሩት እንዴት ነበር?

ኮሎኔል ሁሴን፡- በወቅቱ መመዘኛ የነበረው፤ የትምህርት ዝግጅት፣ ሥነ ምግባር፣ የሥራ አፈፃፀም ብቃት፣ አካላዊ ብቃትን ማዕከል ያደረገ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሜካናይዝድ ሙያተኛ ዘመናዊ መሣሪያ እና ቴክኖሎጂ ስለሚመራ ትልቅ ኃላፊነትና ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው ዘው ብሎ አያዝም ትልቅ ብቃት ይጠይቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ውጭ የነበርዎት የሥራ ሁኔታ ምን ይመስላል?

ኮሎኔል ሁሴን፡- በውጭ አገራትም ሻለቃ መርቼ መጥቻለሁ፡፡ በ2004 ዓ.ም በጎረቤት አገር ሱዳን በነበረው አለመረጋጋት የሰላም ማስከበር ሥራውን የኢትዮጵያ ሰራዊት ኃላፊነቱን ሲቀበል ለሎጂስቲክስ ምክትል አዛዥ በመሆን በዳርፉር ግዛት የ11ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ ምክትል አዛዥ በመሆን ለ18 ወራት አገልግያለሁ፡፡ በዚህ ወቅት የሥራ ቋንቋ በአማርኛ ብቻ ባልሆነበት ሌሎችም የዓለም አገራት በተሳተፉበት ከአመራሮች ጋር ተግባብቼ ሠርቼ ግዳጄን ተወጥቻለሁ። በ2009 ዓ.ም ባለኝ የሥራ አፈፃፀም ተመርጬ የሻለቃ አዛዥ ሆኜ በአብዬ ግዛት ሠላም ማስከበር ለ18 ወራት ሠርቼ ተመልሻለሁ፡፡

በነበረኝ የሻለቃ አፈፃፀም ግዳጅ በተባበሩት መንግሥታት ‹‹ስታፍ ኦፊሰር›› ሆኜ በአብዬ በስታፍ አገልግዬ በ2013 ዓ.ም ወደ አገሬ ገብቻለሁ፡፡ በ2013 ዓ.ም ወደ አገር ቤት ከገባሁ በኋላ የአገር መከላከያ ሰራዊት በጡረታ አሰናብቶኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አገራችን በጁንታው ስትጠቃ አገሬ መወረር የለብትም ብዬ በደላንታ እና ፀሐይ መውጫ ግንባር ሚሊሻ ይዤ ስዋጋ ነበር፡፡ በኋላ የአገር መከላከያ ጥሪ አድርጎልኝ ወደ ሜካናይዝድ ስቀላቀል ሚሊሻውን ለሚመለከተው አካል አስረክቤ ነበር፡፡

See also  በአዳማ ከተማ የምርጫ ሂደቱን ለማወክ በመሞከርና በምርጫ ጣቢያ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት የተከሰሱ ተቀጡ

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅትስ የነበርዎት ሚና ምን ነበር?

ኮሎኔል ሁሴን፡– በውጊያው ተሳትፌ ነበር፡፡ በወቅቱ ለሎጂስቲክስ የታንከኛ ብርጌድ የአንደኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ነበርኩ፡፡ ከዝግጅት እስከ ውጊያው ፍፃሜ 1991 ዓ.ም ጀምሮ በኃላፊነት ከምክትል አዛዥ እስከ አዛዥነት አገልግያለሁ፡፡

በኢትዮ- ኤርትራ 1991 ዓ.ም ማዕረጌ መቶ አለቃ ነበር፡፡ 1992 ዓ.ም ደግሞ ማዕረጌ ሻምበል ነበር፡፡ በዚህ ውጊያ የማስታውሰው ብዙ ነገር አለ፡፡ አገር ስትወረር ለሕይወታችን የምንሰስትበት ጉዳይ አልነበረም፡፡ በወኔ የተወጣንበትና አገራችንንን ከመደፈር የታደግንበት ወቅት ነበር፡፡ በጣም ከባድ ግዳጅ ቢሆንም የሕዝብ ድጋፍ ስለነበር ለማሸነፋችን ትልቅ እግዛ አድርጎልናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት ሰራዊቱን ይወጋል ብለው ይገምቱ ነበር?

ኮሎኔል ሁሴን፡- ሰራዊቱን ይወጋሉ ብዬ አልገነዘብም ነበር፡፡ ምክንያቱም ያሳደጉን እነርሱ ናቸው፡፡ አሳድገው፣ አሰልጥነው፣ አብቅተው መልሰው ይበሉናል ብለን አናስብም ነበር፡፡ መተናኮሱ እንደሚኖር በተለይ ደግሞ አማራ ላይ ያለው ጥላቻ የቆየ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ አንዳንድ ምልክቶችም ይታዩ ነበር፡፡ ብዙውን ጊዜ የቆየሁት ትግራይ ውስጥ ነው፡፡ ያለውን ነገር እገነዘባለሁ፡፡ እኔ ከ22 ዓመታት በላይ በትግራይ ክልል ቆይቻለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉ ሕዝቡ ያን ያክል ሰራዊቱን የሚጠላ አልነበረም፡፡

መጨረሻ ላይ ግን ሰራዊቱን በተኛበት ሲያርዱት አናውቃቸውም ነበር ማለት ነው ብያለሁ፡፡ በተኛንበት ይወሩናል፤ ያጠቁናል ብለን አናስብም፡፡ ምክንያቱም ገንዘባችንን እያወጣን ትምህርት ቤት እየገነባን፣ አዝመራ እያጨድን፣ ሕዝቡን እያገለገልንና እያለማን፣ ችግኝ እየተከልንና እየተንከባከብን ለቁም ነገር ያበቃን ነን፡፡ ስለዚህ ‹‹ባጎረስን እንነከሳለን›› ብለን አናስብም ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው፡፡ ያጎረሰው እጃችንን መልሰው ነከሱት፡፡ ዞሮ ዞሮ እነዚህን ዓመታት ስንቆይ ጁንታው ባላሰብነው መንገድ ጥቃት ፈጽሟል፡፡ ይህ ጥቃት ደግሞ እጅግ የሚዘገንን ምንጊዜም ታሪክ የማይረሳው ነገር ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጁንታው ክህደት በፈፀመበት ወቅት እርስዎ ምን ይሰሩ ነበር?

ኮሎኔል ሁሴን፡– ከአገር መከላከያ ሰራዊት በጡረታ ከተገለልሁ በኋላ እረፍት ያገኘሁት አምስት ወር ብቻ ነበር፡፡ በመሃል ውጭ ነበርኩ፡፡ ዩኒፎርሜን ያወለቅሁት ለአምስት ወራት ብቻ ነው። ጁንታው ሰራዊቱን ያጠቃው ውጭ እያለሁ ነበር፡፡ እኔም አገሬን መታደግ አለብኝ ብዬ ጥያቄ ያቀረብኩት እዚያ እያለሁ ነበር፡፡ ይህንን ለማወቅ አመራሮችን በመጠየቅ እውነታውን መረዳት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሌሎች ወደ ውጭ እንውጣ ጥቅም ማግኘት አለብን እያሉ እንዴት እርስዎ ወደ አገሬ ልግባ ብለው ጠየቁ?

ኮሎኔል ሁሴን፡– ትክክል ነው፡፡ እኔ ወደ አገሬ ልመለስ ብዬ ያስጠየቀኝ የጥቅም ማጣት አይደለም። የተሻለ ይከፈለኝ ነበር፡፡ ውጭ የማገኘው ደመወዙ እዚህ ከማገኘው ጋር አይወዳደርም፡፡ ነገር ግን አገር ከምንም በላይ ነው፡፡ በገንዘብ አይለካም፡፡ እኔ አገሬን የምለካት በጥቅማ ጥቅም እና በገንዘብ አይደለም። የአገር ፍቅር መለኪያው በጣም ከባድ ነው፡፡ የሚያመው ውስጥህን ነው፡፡ አብሬያቸው ያደኩኝ፣ ያሳደኳቸው የሰራዊት አባላት የመራኋቸው እና የመሩኝ አመራሮች ሲመቱ በጣም ያማል፡፡ በዚህ ጊዜ የምታገኘው ጥቅም አይታይህም፡፡ ስለዚህ በወቅቱ የነበረውን ኮርስ ኮማንደር ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ አገሬንና መከላከያን መታደግ አለብኝ አቅሙ አለኝ የሚል ጥያቄ አቀረብኩኝ፡፡ ወደ አገሬ እንደተመለስኩም የአገር መከላከያ ገብቼ ጠየኩኝ፡፡ ትንሽ ጠብቅ ስንጠራህ ትመለሳለህ ተብዬ አምስት ወር እንደቆየሁ ተጠራሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የአገር መከላከያ ሰራዊቱን ከተቀላቀሉ በኋላ የመጀመሪያ ስምሪትዎ ምን ነበር?

ኮሎኔል ሁሴን፡- አጋጣሚ ሆኖ በደቡብ ወሎ ዞን ለመጀመሪያ ጊዜ አለን ብለን የቀረብነው ሁለት ኮሎኔሎች ነን፡፡ የተነሳነው አገር እና ክልሉን መታደግ አለብን ብለን ነው፡፡ በተፈለግነው ቦታ ለመሰማራት ዝግጁ ነበርን፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ሚሊሻን ይዘን መጀመሪያ በደላንታ ግንባር ተሰለፍን፡፡ በደላንታ ግንባር ሚሊሻውን እያስተባበርኩ እያለሁ ደቡብ

 ዕዝ በአካባቢው ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የሜካናይዝድ ሙያ ስላለኝ የደቡብ ዕዝ የሜካናይዝድ ዕዝ እንድመራ እንዳስተባበር ተጠየኩኝ። እኔም መንግሥት በሚመድበኝ ቦታ ለመሥራት ዝግጁ ነበርኩ፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በተጨማሪም ፍላጎቱም ነበረኝ።በዚህም ደላንታ ግንባር የነበረውን የጠላትን ኃይል በመደምሰስና በማጥቃት ላይ ነበርኩ፡፡

See also  ለ25,791 እድለኞች የጋራ መኖርያ ቤት ዕጣ ወጣ

የጠላት ፍላጎት ጋሸናን በመቁረጥ ወደ ደብረታቦር በመግባት አማራ ክልልን ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠር ህልምና ፍላጎት ስለነበረው ያንን ህልም ለማክሸፍ፤ ጋሸናን ለሁለት በመቁረጥ፣ የላሊበላ፣ ጎንደር፣ ወልዲያ መስመርን በመቁረጥ ጁንታው ወደ መሃል ዘልቆ እንዳይገባ ካደረጉት አመራሮች መካከል አንዱ እኔ ነኝ።

አዲስ ዘመን፡- ጉዳት የደረሰብዎት በየትኛው አካባቢና መቼ ነበር?

ኮሎኔል ሁሴን፡- እኔ ጉዳት የደረሰብኝ ጋሸናን ከተቆጣጠርን በኋላ ከወልዲያ አቅጣጫ የሚመጣው ጠላት ለመመከት ታንኮችን ይዤ እያስተባበርኩ እያለ ነሐሴ 2013 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት ከጠላት በተተኮሰ ዲሽቃ ጉዳት ደርሶብኛል፡፡ በዚህም ግራ እጄን ተጎድቻለሁ፡፡ በሕክምና ሲረዳ የሚድን ባለመሆኑ ቆይቶ ተቆርጧል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጉዳት ከደረስብዎት በኋላም ሲያዋጉና ሲያስተባብሩ እንደነበር የቅርብ ሰዎች ነግረውኛል፡፡ ይህን ለምን ለማድረግ ወሰኑ?

ኮሎኔል ሁሴን፡- የእውነቱን ለመናገር ከሆነ ማድረግ እስከምችለው ድረስ ውጊያው መቀጠል አለበት፡፡ እኔ ስለቆሰልኩ ውጊያው መቆም የለበትም። በጁንታው እጅም መውደቅ የለብኝም ምክንያቱም አመራር ነኝ። ወደ ኋላ ወጥቼ መታከም አለብኝ፡፡ በወቅቱ እጄ ታስሮም መምራት የማልችልበት ደረጃ ደርሼ ነበር። በመሆኑም በጠላት እጅ ሳልወድቅ የወገን ኃይል አወጣኝ፡፡ ነገር ግን የተመለስኩት ታንኮቹ እንዲቀጥሉ መመሪያ ሰጥቼ ነው፡፡

ታንኮቹ ወደፊት መቀጠል እንዳለባቸው፤ በተለይም ለእግረኛው ድጋፍ እንዲሰጡ መደረግ እንዳለበት አሳውቄያለሁ፡፡ ከዚያም የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና እርዳታ እንዳገኝ ተደረገ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ደም ማቆም የተደረገልኝ ጋሸና ነበር፡፡ ከዚያ ወደ ወገል ጤና መጣሁ፡፡ በመቀጥል ወደ ደሴ መጣሁ፡፡ በመጨረሻም ወደ አዲስ አበባ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ገባሁ፡፡ በሐኪሞች ውሳኔ እጄ በጣም ተጎድቶና እንደማይሠራ ሲታወቅ እንዲቆረጥ ተደርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እጅዎ ሲቆረጥ የመጉደል ስሜት አልተሰማዎትም?

ኮሎኔል ሁሴን፡– እጄ እንደተቆረጠ አላስብም፤ የማስበው ሙሉ እንደሆንኩ ነው፡፡ የሰው ልጅ እግሩ ወይንም እጁ አሊያም ዓይኑ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእኛ መጥፋት የሌለበት ህሊናችን ነው፡፡ መኖር ያለበት የምናስብበት አዕምሮ ነው፡፡ አዕምሯችን እስከሠራ ድረስ ማንኛውንም ነገር መሥራት እንችላለን። በሕይወት መትረፌ በራሱ ዕድለኝነት ነው። ሊያቆስለኝ ሳይሆን ሊገድለኝ የመጣ መሣሪያ ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ተረፍኩኝ፡፡ እጄ ስለተቆረጠ ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር አይሰማኝም፡፡ ውስጤ እጅግ ደስተኛ ነው፡፡ አዕምሮዬ የሚያስበው ይከፋኝ የነበረው ለአገሩ አስተዋፅኦ ባላደርግ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ባልሳተፍ ኖሮ መኖር አልችልም፤ ያመኝ ነበር፡፡ አሁን ግን የምችለውን አድርጌ ስለሆነ ውስጤ ደስተኛ ነው፡፡

ከባድ የሚሆነው እስከውጊያ ድረስ ያለው ጊዜ ነው። እውነቱን የምነግርህ፤ የውትድርና ከባዱ ነገር እስከዚያ ድረስ ያለው ፈተና እጅግ አድካሚ ነው። ያለው ጭቃ፣ ዝናብ፣ ያለው ውጣ ውረድ በጣም ፈታኝና አድካሚ ነው፡፡ ሕዝቡ የወታደሩ ነገር ቢያከብርለትና ዘላለም ቢያስታውሰው በግሌ ደስ ይለኛል፡፡ ዘላለም አገራችን ይህንን ባትረሳው ደስ ይለኛል፡፡ ወታደር ችግር ሲመጣ የሚደገፍ ሠላም ሲመጣ የሚረሳ መሆን የለበትም፡፡

ወታደሩ የችግሩ ብዛት መገለጫ የለውም፡፡ ፈተናው መገለጫው ይህ ነው አልልም፡፡ ለጁንታው ጭካኔ መግለጫ እስካልተገኘለት ድረስ ለውትድርና የሚከፈለው ውጣ ውረድ መጨረሻው ይህ ነው ብዬ ለመናገር በጣም ይከብደኛል፡፡ ቃላት አላገኝለትም በጣም ከባድ ነው፡፡ በውትድርና መሞትና መቁሰሉ መጨረሻ ላይ የሚያጋጥም ችግር ነው፡፡ ከዚያ በፊት ያለው ውጣ ውረድ ግን እጅግ ከባድ ነው፡፡ ያንን መቋቋም ይጠይቃል፡፡ ይህን ስናገር አንድ ነገር አለ፡፡ የሕዝባችን ነገር ሁልጊዜ ጭንቅላቴ ላይ ይመጣብኛል። እንባዬ ይቀድማል፡፡ ሕዝብ ሲያርድና ሲያቀርብ እንባዬ ይመጣል፡፡ እነርሱን ሳላስደስት፤ አገሬን ሰላም ሳላደርግ የሚለው ሃሳብ ይቀድማል፡፡ ምክንያቱም ሕዝባችን የሚደግፈው ሞልቶ ተርፎት አይደለም፤ እየቸገረው ነው፡፡ የሚደግፈን ከራሱ ቀንሶ ነው ፡፡

ስለዚህ የማስበው የሕዝባችን ውለታ እስከመጨረሻው መክፈል ነበረብኝ ብዬ ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ መቁሰል ሲያጋጥምና አካል ሲጎድል ሁሉም እንዳሰቡት ላይሆን ይችላል፡፡ አሁንም ቁጭ ብሎ ማዘዝ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አገራችን ድሃ አይደለችም። ከወታደሩም ከሕዝቡም ከሁሉም ፊታውራሪ አለ፡፡ ይህንንም ያስቀጥላሉ የሚል ፅኑ ዕምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን አገሬ ከፈለገችኝ አይደለም አንድ እጅ ሌላውም ቢጨመር ሕይወትም ቢጠፋ ጁንታው እስካለ ድረስ እኔም ስለማልኖር የበኩሌን ለማድረግ ዝግጁ ነኝ። ጁንታው እስከሚያበቃለት ድረስ ሥራችን መቀጠል አለበት ብዬም አምናለሁ፡፡

See also  ማዕድን ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጉሮሮ – “የሕዝብ ሃብት ለሚያባክኑ ዝምታ የለም” ታከለ ኡማ

አዲስ ዘመን፡- በጦርነቱ ሂደት ሰሜን ሸዋ ድረስ ዘልቀው በአጭር ጊዜ ሲባረሩ እንደ አንድ ወታደራዊ አመራር ምን ተገነዘቡ?

ኮሎኔል ሁሴን፡- እነርሱ ሰሜን ሸዋ ሲደርሱ ጦርነቱ አልቋል ብለው ነበር፡፡ በእኔ ዕምነት ደግሞ ሰሜን ሸዋ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ ቢገቡም ኢትዮጵያን ይገዛሉ የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይፈልግ በራሱ ላይ የሚጫንበትን ነገር የሚቀበል አይመስለኝም፡፡ ለጊዜው ዕድል ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ መሃል መግባት ሊግጥም ይችላል፤ ነገር ግን እንደሚሸነፉ ጥርጥር የለኝም፡፡ በ1983 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ መንገድ እያሳየ የተቀበላቸው ሕዝቡ ነው። እኔ ራሴ የተቀበልኳቸው መንገድ እያሳየሁ ነው፡፡ ዛሬ ግን የሚቀበላቸው የለም፡፡ ሕዝቡ ዛሬ አያበላቸውም፤ መንገድ አያሳያቸውም፤ አይቀበላቸውም፡፡ ስለዚህ እንኳን ደብረሲና ቀርቶ አዲስ አበባ ቢገቡ ተመልሰው እንደሚንኮታኮቱ ይገባኛል፡፡ መንገድ ተከትሎ አዲስ አበባ መግባት ብቻ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ሰፊ ናት፤ ብዙም ናት። ከዓላማጣ እስከ ሸዋ ያለው ብቻ አይደለም፡፡ በጣም ትልቅ አገር ነው፡፡ ሰሜን ሸዋ ለመድረስ የፈጀባቸው አምስት ወር ነው፡፡ ለመመለስ ደግሞ የወሰደባቸው 15 ቀናት ናቸው፡፡ ከገቡበት የተመለሱበት በጣም ፈጣን ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የሰራዊታችን ቁርጠኝነት የሕዝባችን ደጀንነት ከምንጊዜው በላይ ይህን ኃይል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት አለብን ብሎ ስለተነሳ ነው፡፡ ይህ የጥምር ኃይሎች ውጤት ነው። ቀደም ሲል የሕዝብ ድጋፍ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የተደረገው ግን ለየት ያለ ነው፡፡ ዛሬም እንደሚጠፉ አልጠራጠርም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ የሕዝብን ተጋድሎ የሚያሸንፍ ኃይል የለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ ላደረጉት ተጋድሎ እና አስተዋፅኦ በአገር መከላከያ የደቡብ ዕዝ የተሰጥዎት እውቅና ምን ስሜት ፈጠረብዎት?

ኮሎኔል ሁሴን፡- ለእኔ የተሰጠኝ እውቅና ጥሩ አዋጊ እና ተዋጊ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሜዳሊያ ነው፡፡ ይህን ሽልማት የማየው ከምንም በላይ ነው፡፡ ስለገንዘብ አጀንዳ የለኝም፡፡ ከዚህ በኋላ ባለኝ ጊዜና ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ለእኔ ያንሳል ብዬ አላስብም፡፡ አቅሜ እስከቻለ ድረስ ለራሴም አላንስም እሠራለሁ፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የከፈልኩት ዋጋ ነው፡፡ ለአገሬ የከፈልኩት ዋጋ ማንም አስገድዶኝ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ መክፈል የነበረብኝ ዋጋ ነው። እኔ ለዚህ ዋጋ ክፍያ አልጠይቅም፤ አያስፈልገኝም። የነበሩትን አመራሮች፣ የወላጆቻችንና የአባቶቻችን አደራ ለማስቀጠል የከፈልኩት ዋጋ እስከሆነ ድረስ ለእኔ ይህ ይደረግልኝ አልልም፡፡ ከምንም በላይ ለእኔ ትልቁ ነገር ዕውቅናው ነው፡፡ ዕውቅናውን ለሰጠኝ ደቡብ ዕዝ ደግሞ በትልቁ አመሰግናለሁ፤ ምክንያቱም ከእውቅና በላይ ትልቅ ነገር የለም፡፡ ከዚህ በተረፈ በግሌ የሚገጥሙኝን ነገሮች እወጣዋለሁ ብዬ አስባለሁ። ችግር ሊኖር ይችላል፤ ይኑር! እጋፈጠዋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለቤተሰብዎ ሊነግሩኝ ፈቃደኛ ነዎት?

ኮሎኔል ሁሴን፡- ሰባት ልጆች ወልጃለሁ፡፡ አራቱ በእኔ ሥር ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ራሳቸውን ችለዋል።አሁን ባለው ሁኔታ በመከላከያ ውስጥ የምቀጥል አይመስ ለኝም፡፡ እኔም ቦርድ ስወጣ ከእነርሱ ጋር እኖራለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊ ስሜት ይዘው ያደጉ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክት አልዎት?

ኮሎኔል ሁሴን፡- አጋጣሚ ሆኖ ይህን ዕድል ማግኘቴ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክት አለኝ፡፡ ውትድርና የቅብብሎሽ ሥራ ነው፡፡ እኔ በግሌ 31 ዓመት ለአገሬ ኢትዮጵያ በውትድርና አገልግዬ ቦርድ እየወጣሁ ነው፡፡ ለእኛ ተተኪ ያስፈልጋል፡፡ ሰራዊታችን ተተኪ ይፈልጋል። ምንጊዜም መተካካት አለበት፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ወደ አገር መከላከያ ሰራዊት እንዲገባ ሕዝቡ ልጆቹን መርቆ መላክ አለበት፡፡

ውትድርና በግዳጅ ሊሆን አይገባም፡፡ እኔ ቢያንስ ከልጆቹ አንዱን ወደ ውትድርና ዓለም እንዲቀላቀል እና እንደ እኔ ሜዳሊያ እንዲያነሳ ኮትኩቼ አሳድጌ አስገባለሁ፡፡ የማሰለጥነው ከቤት ጀምሬ ነው፡፡ የምንኖረው አገራችን ሰላም ስትሆን ነው፡፡ ለዚህም የማይበገር የማይደፈር ሰራዊት ሲኖራት ነው፡፡ ሕዝቡም የሚተማመንበትና የሚኮራበት ማለት ነው። ይህ የሚሆነው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና መሣሪያዎችን ሲታጠቅ ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም አገሬን እወዳለሁ የሚል ዜጋ የአብራኩን ክፋይ ከአገር መከላከያ ሰራዊት እንዲቀላቀል ማድረግ አለበት፡፡ አገር ዝም ብሎ አይመጣም፡፡ ስለዚህ ሕዝባችን ይህን ሊገነዘብ ይገባል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ኢትዮጵያን የሚመስል ሰራዊት እንዲኖረንም ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ልጆቻቸውን ልከው የአገር መከላከያን ማጠናከር አለባቸው፡፡

ሌላው ልማት የሚቀጥለው ሠላም ካለ ነው፡፡ ሠላም ባለመኖሩ የተፈጠረውን ክፍተት እየተመለከትን ነው፡፡ ከተሞች እንደነበሩት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ሰራዊቱን በመደገፍ አካባቢውን በማልማት አካባቢውን በንቃት ሊከታተል ይገባል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ በአንድነት ሆነን አገራችን መጠበቅ አለብን፤ ጠላትንም መደምሰስ ይጠበቅብናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኮሎኔል የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ ሆነው ሃሳብዎትን ስላካፈሉን እናመሰ ግናለን፡፡

ኮሎኔል ሁሴን፡- እኔም እዚህ ወልዲያ ድረስ መጥታችሁ ስለሰራዊታችን ቁመና ስለተገነዘባችሁ እና ተገቢውን መረጃ ለሕዝብ ስለምታስተላልፉ ከልብ አመስግናለሁ፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን የካቲት 10/2014 ዓ.ም

Leave a Reply