ከሁሉ በፊት የአገርና ክልላችንን ጥቅም እናስቀድም!

ከምንም በላይ በሕግና ሥርዓት ልናምን ይገባል። መንጋነትን ልንፀየፍ ይገባል። “ሕዝቤን እወዳለሁ” የሚል ቢኖር በቅድሚያ “ሕግና ሥርዓትን” ይውደድ። በመንግሥትም ሆነ በድርጅት አሰራር ሕግና ሥርዓትን ማክበር የተረጋጋ አገር/ክልል ለመፍጠር አይተኬ ሚና አላቸው። የአርነት መንገድ ሕግና ሥርዓት ናቸው። ለዚህም ነው’ኮ በሕግና ሥርዓት መመራት የአርነት ባለቤት ያደርጋል! የሚባለው።

Chuchu Alebachew ነጻ አስተያየት

የአገራችንም ሆነ የክልላችን ፖለቲካ ስክነት ተስኖታል። ከፖለቲካዊ ህመም ለመዳን ብዙ ሙከራዎች እየተደረጉ ቢሆንም እስካሁን የተፈለገውን ያክል ፖለቲካዊ ስክነት አልታየም። ዙሪያችን በከበበን የህልውና አደጋ ልክ ዝግጁነት የለንም። ወታደራዊ ዝግጁነታችን የሚበረታታ ቢሆንም ፖለቲካዊ ተግባራቶቻችን ላይ የሚቀረን ብዙ ነው። ተሻጋሪ አጀንዳዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ በዕለት ደራሽ ‘ትርኪ ምርኪ’ ጉዳዮች ላይ እንጠመዳለን።

እንናገረው ካልን በአገራችንም ሆነ በክልላችን ሊነሱና በመንግስት/ድርጅት ምላሽ ሊሰጣቸዉ የሚገባቸው እጅግ በርካታ ችግሮችና የአሰራር ግድፈቶች አሉ። ሆኖም የአገራችን በተለይም የክልላችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ከብዙ ነገር እንድንቆጠብ ያስገድዱናል። ስክነት የሚጠይቅ ውስብስብ ጊዜ ላይ እንገኛለን። እሴት በማይጨምሩ፣ ችግር ፈች ባልሆኑ የቅርብ አዳሪነት መገለጫ በሆኑ ተራ ብሽሽቆች ባንጣድ ይመከራል። አሁን ኃይል የምናሰባስብበት ፣ የጋራ መምከሪያ አቅም የምናከማችበት ጊዜ ነው። እንደየሁኔታው ችግሮች ቢኖሩብን እንኳ ትልቁን ስዕል መሳት የለብንም። ምክንያቱም ቅሬታዎችን በቅጡ አቅርቦ መፍትሄ ለማግኘት የተረጋጋ አገርና ክልል መኖር ቀዳሚው ጉዳይ ነውና። ይሄንን ስል ነገሮችን በስክነት አዳምጦና መርምሮ ምላሽ የሚሰጥ አመራር የመኖር/ አስፈላገነትን ዘንግቸዉ አይደለም።

በተመሳሳይ ሁነት መንግስትም ሆነ ድርጅት በማናቸውም ወገን የሚቀርቡ ቅሬታወችን በተቻለ መጠን ሰከን ብሎ ማዳመጥና ምላሽ ለመስጠት ቢሞክር ጥሩ ነው። በተለይም ለሚቀርቡ ህጋዊ ጥያቄዎች እንካ ስላንትያ አይነት መልስ ቢቀር ጥሩ ነዉ። ይሄ አካሄድ ከገጠመን/ለወደፊቱም ሊገጥመን ከሚችል የፖለቲካ መካረር ወጥተን የፖለቲካ ስክነትን በማስፈን በኩል ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብየ አምናለሁ።

ብቻ በእኔ ዕይታ ብዙ ነገሮችን እያወቅንም ቢሆን ለጊዜው ዘለናቸው፣ ለአገራችን በተለይም ለአማራ ክልል የህዝብና የግዛት አንድነትና ፖለቲካዊ መረጋጋት የየድርሻችንን ሚና ብንጫወት ጥሩ ይመስለኛል። ፖለቲካዊ መረጋጋት ከተፈጠረና የህልዉና ስጋታችንን ካስወገድን በሁዋላ ብዙ እጅግ ብዙ የምንነጋገርባቸዉ ጉዳዮች ይኖራሉ። ስለሆነም ነገሮችን ሁሉ በተረጋጋና በአሰተዉሎት እንያቸዉ። ያለበለዚያ ነገሮች ሊበላሹብንና ትልቁን ነገር ልናጣ እንችላለን።

ከምንም በላይ በሕግና ሥርዓት ልናምን ይገባል። መንጋነትን ልንፀየፍ ይገባል። “ሕዝቤን እወዳለሁ” የሚል ቢኖር በቅድሚያ “ሕግና ሥርዓትን” ይውደድ። በመንግሥትም ሆነ በድርጅት አሰራር ሕግና ሥርዓትን ማክበር የተረጋጋ አገር/ክልል ለመፍጠር አይተኬ ሚና አላቸው። የአርነት መንገድ ሕግና ሥርዓት ናቸው። ለዚህም ነው’ኮ በሕግና ሥርዓት መመራት የአርነት ባለቤት ያደርጋል! የሚባለው።

ለሁሉም አካላዊና ህሊናዊ ትኩረታችን አንድ ለእርስ በርስ ፍትጊያ ሳይሆን ለጠላት መታገያ፤ አንድም ደግሞ ጠላት በሚሰጠን አጀንዳ ሳይሆን ህልውናችን ከማፅናት፣ የሀገርና ሕዝብ ጥቅምን ከማስከበር አኳያ ሊሆን ይገባል። በግራም ሆነ በቀኝ ያለነው የፖለቲካ ተዋናዮች ራሳችንን ማሸነፍ (Ego- ኢጓችን መሻገር ካልቻልን) የሕዝባችን ስጋት እንጅ አለኝታ መሆን አንችልም።

በነገራችን ላይ የልዩ ሀይል ምልመላ ስራችን ምን ላይ ደርሶ ይሆን? የአማራ ማህበረሰብ” አንቂዎች” እስኪ ቢያንስ በዚህ አጀንዳ ዙሪያ በጋራ ቁሙ።

ስለሕዝብና ሀገር ጥቅም ሲባል አውቀን እንታረም

Leave a Reply