ብራስልስና መቀሌ

ጠ/ሚር አብይ ብራስልስ ላይ አውሮፓውያንን እያግባቡ ነው። ዲፕሎማሲው ጥሩ መስመር የያዘላቸው ይመስላል። መጨበባጡንና መተቃቀፉን ብቻ ወስደን ከዲፕሎማሲ ውጪያዊ መልክ አንጻር ካየነው ከአውሮፓ ህብረት ጋር የነበረው የሻከረ ግንኙነት እየለሰለሰ የሚመጣበት እድል ከፊታችን እንደሚገኝ የሚያመላክት ነው። ህወሓት ደግሞ ከመቀሌ አካኪ ዘራፍ ይላል። በሞትና ህይወት መሀል ሆኖ እያጣጣረም ቡራ ከረዩ ለማለት አቅም አላጠረውም። ሰማይና ምድር ቦታ መለዋወጥ የማይችሉትን ያህል ደረቅ እውነት እቀለብሰዋለሁ ብሎ እያፏጨ ነው። በእርግጥም ብራስልስ እየተቀየረች ነው። መቀሌ ግን ቆማ ቀርታለች።

እውነት ለመናገር የአውሮፓ ህብረት ላለፉት ሁለት ዓመታት ከእውነትና ፍትህ ጋር አልነበረም። አሁንም ቢሆን ፍንጭ እንጂ ለውጥ አላየንም። ህብረቱ የመቀሌው ቡድን ቁጥር አንድ ጠበቃና ተከላካይ ሆኖ መዝለቁ በታሪኩ አሳፋሪ ገጽታው ነው ማለት ይቻላል። ይህን ጸያፍ ቡድን በአናቱ እያጎረሰ፣ ሲደክመውና ትንፋሽ ሲያጥረውም ጉልበትና አቅም እየሆነው፣ በህይወት መቆየት ከሚችለው በላይ እንዲቆይ በፊት ለፊት ተጋፍጦለታል። የ100ሚሊዮን ህዝብን ፍላጎትና መብት ወደጎን ገፍቶ በዘረኝነት ያበዱ ጥቂት ወንጀለኞች ለተሰባሰቡበት የህወሀት ቡድን ወኪል ሆኖ ሲሟገትለት ሰንብቷል። ለህወሀት ከመቃብር ፈንቅሎ መነሳት ትልቁን ድርሻ ያበረከተው የአውሮፓ ህብረት ስለመሆኑ በታሪክ ውስጥ ሲጠቀስ የሚኖር እውነት ነው።

የአውሮፓ ህብረት ሸውራራና የተወላገደ አቅጣጫ ኢትዮጵያን ዋጋ አስከፍሏታል። የምትፈልገው ገንዘብ ተይዞባታል። ጫናው ቀላል የሚባል አይደለም። የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ መንግስት ጀርባውን ሰጥቶ፣ እውነትን ጨፍልቆ፣ መርህንና ሀቅን ደፍጥጦ የመጣበት ጠመዝማዛ መንገድ ማንንም አልጠቀመም። ህወሀትንም ቢሆን ከመቃብር ከማስጣል ያለፈ ትርጉም ያለው ድል አላስገኘለትም። በእርግጥ ህብረቱ በሰሞኑ መድረክ ላይ በመጣበት አባጣ ጎርባጣ መንገድ እንደማይቀጥልበት ፍንጭ አሳይቷል። ሌላ መንገድ እንዳለ የተረዳ ይመስላል። ይህ ሁኔታ ደግሞ መቀሌን ምቾት እንደሚነሳት ጥርጥር የለውም። ምንም እንኳን ይህ ነው የሚባል ይፋዊ የአቋም ለውጥ በአውሮፓ ህብረት በኩል ባይታይም የየሀገራቱ መሪዎችና የህብረቱ ባለስልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የተቀበሉበት ሁኔታና የተለዋወጧቸው ሀሳቦች ነገ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ተስፋ እንድንሰንቅ የሚያደርገን ነው።

ኢትዮጵያ ደከም ብላ በምትወቀስበት የዲፕሎማሲው ጎኗ ላይ ጥርሷን ነክሳ ለውጥ ልታሳይ እንደሆነ የሰሞኑ የብራስልሱ መድረክና ያለፈው የአዲስ አበባው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ የያዘችው ቁመና ይመሰክራሉ። የጦር ሜዳው ድል በዲፕሎማሲው ካልተደገፈ ሙሉ የሆነ አሸናፊነት እንደማያጎናጽፍ የተረዱት የኢትዮጵያ መሪዎች ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው ዲፕሎማሲው ላይ ዘመቻ ከፍተዋል። የጂኦ ፖለቲካው ውስብስብ ጉዳዮችን ያገናዘበ ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫ ተከትሎ ዘመቻው እንደሚቀጥልም ከቅርብ ሰዎች ያገኘሁት መረጃ አረጋግጦልኛል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጀመረው የሪፎርም እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ትርጉም ያለው ለውጥ ባያስመዘግብም ወደፊት የኢትዮጵያን ቁመና የሚመጥን ገጽታ ይዞ እንደሚመጣ ግን በደማቁ የምንጠብቀው ውጤት ይሆናል።

ህወሓት አራተኛ ዓመት ተዝካሩን እያወጣ ባለበት በዚህ ሰሞን የበላይነት ይዞ በቆየበት የዲፕሎማሲው መድረክ መራር ሽንፈት ሊገጥመው እንደሚችል ተረድቶታትል። ብራስልስ እየሆነ ባለው ሁኔታ ያልተደሰቱት ህወሀቶች በዲጅታል ሰራዊታቸው አማካኝነት የአውሮፓ ህብረትን እያብጠለጠሉት ይገኛሉ። ብራስልስና መቀሌ ተናበው፣ ስለ አንድ ጉዳይ አንድ ገጽ ላይ ሆነው በቆዩባቸው ያለፉት 16ወራት በህወሀቶች ጸሎት ውስጥ የአውሮፓ ህብረት ስሙ ከምስጋና ጋር ሲነሳ ቆይቷል። የሰሞኑ የህብረቱ አዝማሚያ ግን መቀሌን ስጋት ውስጥ ከቷታል። በጦር ሜዳው የተሸነፈው የህወሀት ቡድን በዲፕሎማሲውም ከተረታ ነገር ዓለሙ አበቃለት ማለት ነው። የደብረጺዮን የሰሞኑ ፉከራ ኩርፊያን ማሳያ ተደርጎ ቢወሰድ የሚያስኬድ ነው። ምናልባትም መቀሌ ለብራስልስ ቅያሜዋን የገለጸችበት መልዕክት ሆኖም ቢመነዘር ስሜት ይሰጣል። የአውሮፓ ህብረት ስለ ድርድር አብዝቶ እየተናገረ ባለበት በዚህን ወቅት ድርድር እንደማይኖር የሚያረጋግጥ አቋም መቀሌ ማንጸባረቋ ነገሮች በቀጣይ ምን መልክ እንደሚኖራቸው ለመገመት የሚከብድ አይሆንም።

ደብረጺዮን ያስተጋባውና “ቅድመ ሁኔታ” በሚል የጮኸው የህወሀት አቋም አንገቴ ላይ ሲባጎ አጥልቃችሁ ሞቴን ስጡኝ ከሚል ኑዛዜ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። እንኳን ተሸንፈህና አከርካሪህ ተሰባብሮ ይቅርና በለስ ቀንቶህ አዲስ አበባን ብትቆጣጠርም የማታቀርበውን ቅድመ ሁኔታ በሞት አፋፍ ላይ ሆነህ ይህ ካልተደረገ ብለህ ብታቅራራ የመቃብርህን የመንገድ ርቀት ታሳጥረዋለህ እንጂ ሌላ የምታመጣው ነገር የለም። ነገሮች መቀየራቸው አይቀርም። ብራስልስ እንደነበረች ልትዘልቅ የማትችልበት ሁኔታ ይኖራል። ዋሽንግተን ዲሲም ፊቷን ልታዞር ትችላለች። የኢትዮጵያ መንግስት ዲፕሎማሲው ላይ በያዘው መስመር ገፍቶበት ከሄደ ብራስልስና ዋሽንግተን ዲሲ ቋንቋቸው መለወጡ የማይቀር ነው። የሚያዋጣቸው ከመንግስት ጋር መስራት እንጂ ከሽፍታ ጋር መተሻሸት አይደለምና። ለራሳቸውም ሲሉ የመጡበትን ጠመዝማዛማ መንገድ መቀየራቸው የሚጠበቅ ነው።

መልዕክቴ #share_ሼር ይደረግ Nesay Mekonen

Leave a Reply