ከ “ፔትሮ ዶላር” ወደ “ሃይድሮ ዶላር” ነጻ አሳብ

በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ የራሳቸውን ምህዋር ተከትለው በፀሐይ ዙሪያ ከሚዞሩ ከዘጠኝ በላይ ፕላኔቶች መካከል ሕይወት ላላቸው ፍጥረታት ለኑሮ ምቹ እንድትሆን ተደርጋ በልዕለ ኃያሉ ዲዛይነር የተመነደሰችው የእኛዋ ፕላኔት ምድር ናት። ታዲያ የሕይወት ማህደር ትሆን ዘንድ ከሁሉም ተመርጣ በልዩ ሁኔታ ዲዛይን የተደረገችው እናት ፕላኔታችን ምድር በአብዛኛው የተሠራችው ከውሃ ነው። ማለትም የብስ የምንለው ውሃ የሌለበት ደረቁ ክፍሏ ሩብ ብቻ ሲሆን ሦስት አራተኛው አካሏ በውሃ የተሸፈነ ነው።

ይህ እንግዲህ እንዲሁ በዘፈቀደ የሆነ አይደለም። አብዛኛው የምድር ክፍል ውሃ መሆኑ እንደራሱ እንደ ዲዛይነሩ ጥበብ ከፍ ያለ የገዘፈ ሚስጥር የተሰደረበት እንጂ። ምክንያቱም በምድሪቷ ላይ የሚኖር ሕይወት ያለው ፍጥረት ሁሉ የሚኖረው ውሃን የሕልውናው ዋስትና አድርጎ ነውና። ሰውም ሆነ እንስሳ በሕይወት ለመኖር በዋነኝነት ሁለት ነገሮችን የግዴታ ይፈልጋል። የሚተነፍሰው አየርና የሚመገበው ምግብ ይፈልጋል።

ለሰው ልጆችና ለእንስሳት በሕይወት መኖር የግድ አስፈላጊ የሆኑት እነዚህ ሕይወት ግብዓቶች ማለትም አየርና ምግብ የሚገኙት ደግሞ ከዕጽዋት ነው። ሆኖም ሕይወት ያላቸው አካላት የእስትንፋሳቸውና የምግባቸው ምንጭ የሆኑት ዕፅዋት ያለ ውሃ በምድር ላይ መብቀል አይችሉም። ታዲያ “የሚበሉት ውሃ፣ የሚጠጡት ውሃ” የሚለው የታላቋ የጥበብ ሰው የድምጻዊ እጅግአየሁ ሽባባው(ጂጂ) ዜማ ከኢትዮጵያ በሚወስድላቸው ለም አፈር ዘርተው አብቅለው፣ የዓባይን ውሃ በልተውም ጠጥተውም ለሚኖሩት የሲና በረሃ ግብጻውያን ብቻ የተዘፈነ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?

በበኩሌ “የሚበሉት ውሃ፣ የሚጠጡት ውሃ” የሚለው የጂጂ አንድ መስመር ስንኝ የመላ ዓለሙን ሚስጥር ጠቅሎ የያዘ አንድ ግዙፍ እውነታ በቃላት ተዓምራዊ ኃይል አማካኝነት በምልዓት የተገለጸበት ዕጹብ ድንቅ አዕምሯዊ ብቃት ይመስለኛል። ምክንያቱም ውሃን በልተውና ጠጥተው የሚኖሩት በበረሃማ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በምድር ላይ የሚገኙ ሁሉም ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ናቸውና። ኧረ እንዴውም ውሃን በልታና ጠጥታ የምትኖረው ሕይወት ራሷ ናትና!

ይሁን እንጂ እንደ ግሎባል ሪሰርች ጸሐፊው እዮሃኪም ሃጎፒያን ከሆነ በዓለም አቀፍ የሙቀት መጨመር፣ እየተስፋፋ በመጣው ድርቅ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የውኃ ብክለት ምክንያት ከዓመት ዓመት ቁጥሩ እያሻቀበ ለሚሄደው የዓለም ሕዝብ የበቂ ንጹህ ውሃ አቅርቦት እጥረት በዚህ ዘመን እጅግ አስጨናቂ ከሆኑ የሰው ልጆች ፈተናዎች መካከል አንዱ ሆኗል። እ.ኤ.አ. በ2015 የግብርና ምርት በመጨመሩ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የውኃ ፍላጎት በ17 በመቶ ሊጨምር ችሏል። በተመሳሳይ በአውሮፓውኑ 2025 በመላው ዓለም እየጨመረ በሚሄደው የዓለም ሕዝብ ቁጥር ምክንያት የውኃ ፍጆታ ፍላጎትን በ 40 በመቶ ሊያሳድገው እንደሚችል ተተንብይዋል። በመሆኑም ይላሉ ጸሐፊው፤ “በሃያኛው ክፍለ ዘመን ነዳጅ ወሳኙን ሚና ሲጫወት እንደቆየው ሁሉ፤ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ውሃ እጅግ በጣም ውዱ የዓለማችን የተፈጥሮ ሃብት ይሆናል”።

ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ከዓመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት መሆኑን ደንግጓል። የግሎባል ሪሰርቹ እዮሃኪም ሃጎፒያን እንደሚሉት ከሆነ በዓለም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በተደረጉ ጦርነቶች ከሞቱት ሰዎች ይልቅ በአሁኑ ሰዓት በውሃ ወለድ በሽታዎች ምክንያት እየሞተ ያለው የሕዝብ ቁጥር ይበልጣል። ከንጹሕ ውሃ እጥረት ጋር በተያያዘ በዓለም ላይ በእያንዳንዷ ሰዓት 240 ሕጻናት ይሞታሉ። በንጽሕና ጉድለት ሳቢያ በየዓመቱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሕጻናት በኮሌራና በታይፎይድ በሽታዎች ይሞታሉ።

እነኝህ የማይታመኑ የሚመስሉ አሳዛኝና አስደንጋጭ ሐቆች በምድር ላይ በሕይወት ለመቆየት የንጹሕ ውሃ አቅርቦት ምን ያህል ወሳኝና አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ያረጋግጣሉ። እናም ቀጣዩን የዓለም የኃይል ሚዛን የሚወስነው የውሃ ሃብትና አጠቃቀሙ ይሆናል።

እንግዲህ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ገዜ ጀምሮ “ወዳጃችን” ግብጽን እረፍት የነሳት ይህ ሐቅ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። አልሆንላት ብሎ እንጂ እንኳንስ አድጋ በልጽጋ ኃያል ሆና ማየት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከነጭራሹ ባትኖር ደስ የሚላት እንደ ንጉሶቿ እንደነ ፈርኦን ልቧ በድንቁርና የደነደነው እቡይዋ ግብጽ ግድቡን በተመለከተ እውነቱን መቀበል ያቃታት ለዚህ ነው።

ግብጽ ዓባይን ያለ ስጋት ለመጠቀም ኢትዮጵያን ወርራ ሕዝቦቿን ማንበርከክ አለባት። ይህ የማይቻል ከሆነም አገሪቱን በመንግሥት አልባነትና ባለመረጋጋት ውስጥ እንድትቆይ ማድረግ ይኖርባታል የሚሉ ሀሳቦች ይሰነዘራሉ። ይሄን መሰል ሃሳብ ደግሞ በአንድ ወቅት የግብጽ ፈርኦን አማካሪ የነበረው የዋርነር ሙዚንገር አንዱ ማሳያ ነው። ግብጾቻችን የሚያስቡት እንግዲህ እስከዚህ ነው።

ዓባይን በተመለከተ ዘመኗን ሁሉ አሁንም ድረስ ግብጽ የምትከተለው ፖሊሲም በዚሁ አረመኔያዊ ምክር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ዓለም ይታዘበዋል። እናም በክፉ መካሯ ሃሳብ የጸናችው ግብጽ “ሌባ እንደ ራሱ አመንዝራ እንደ ነፍሱ” እንዲሉ “ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ ገድባ አስቀርታ ልታጠፋኝ ነው” የሚል የምቀኝነትና የሐሰት ክሷን አጠናክራ የቀጠለችበት ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጀርባ ያለው የተደበቀው ፍርሃቷ ከዚህ አስተሳሰቧ የሚቀዳ ነው።

የሚያሳስባት የግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሳይሆን ኢትዮጵያ በውሃ ሃብቷ መጠቀም ስትጀምር በቀጣይ የምትፈጥረው አገራዊ ኃይል ነው። ቀጣዩ የዓለማችን የኃይል ሚዛን ማስጠበቂያ ውሃ መሆኑን እሷ ብቻ የምታውቀው ይመስል ግብጽ የምትጨነቀው “እንግዲህ ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን መጠቀም ከጀመረች በአፍሪካም ሆነ በዓለም ላይ ተገዳዳሪ ኃይል ሆና መምጣቷ ነው” የሚለው ነው ግብጽን የሚያስጨንቀው እውነተኛ ምክንያት።

ግብጽ ሆይ ጭንቀትሽ ይገባናል። ነገር ግን ብልህ አንች ብቻ አይደለሽም፤ ውሃ ኃይል መሆኑ እኛም እናውቃለን። ለዚያም ነው የውሃ ሃብታችንን መጠቀም የጀመርነው። እናም ግብጽ ሆይ ሽህ ጉድጓድ ብትቆፍሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ እንዳሉት ግድባችንን ከመሙላት የሚያግደንም ማንም ምድራዊ ኃይል የለም! ለዚያም ነው የሞላነው! የኃያልነት ጉዟችንም ጀምረናል፤ እንቀጥላለንም። ደጉ ነገር ግን ኃይላችንን የምንጠቀመው፤ ኃያል መሆንም የምንፈልገው አንች እንደምታስቢው ለጥፋት አይደለም። የእኛ ኃያልነት ሌላውን በማጥፋት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ በማልማት እንጂ።

ምክንያቱም እኛ ሁሉንም ነገር የምናደርገው እስከመጨረሻው እውነትንና የእውነትን መንገድ ተከትለን ነው። ምንም እንኳን ከአብራኳ በተገኘው ልጇና ከ86 በመቶ በላይ በምታዋጣው ውድ ሃብቷ መጠቀም ማንም ምድራዊ ኃይል የማይከለክላት ተፈጥሯዊ መብቷ ቢሆንም፤ በኖረው የብዙ ሺህ ዘመናት የዳበረ የእኩልነትና ፍትሐዊነት ዕሴቷ ግድቡን የምትገነባውም ሌላውን ለመጉዳት ሳይሆን ተባብሮ ለማደግ ነው።

በመሆኑም በግድቡ ምክንያት ግብጽ ሊፈጠረብኝ ይችላል የምትለውን ማንኛውንም ስጋት በቅንነት ተቀብሎ ለማየትና በእርግጥ ችግር የሚፈጥር ሆኖ ከተገኘም ተገቢውን መፍትሔ ለማበጀት ከመጀመሪያው ጀምራ በሯን ክፍት አድርጋ እየሠራች ትገኛለች።

በእርግጥ ቀድሞውንም ቢሆን ግብጽ አልጠግብ ባይነት ምቀኝነቷ ያንገበግባታል እንጂ ኢትዮጵያ አንጡራ ሲሳይዋን ዓባይን “በቤትህ እደር” ስትል ወደ ግብጽም ሆነ ወደ ሌሎች የታችኛው ተፋሰስ አገራት መሄድ የለብህም፤ እኔን ብቻ እንጅ እነርሱንም አትጥቀም ማለቷ አይደለም። እንዲያውም ከዓባይ በሚገኘው ሲሳይ ሌሎችንም ለመጥቀም፣ በተለይ ደግሞ ግብጽን በየዓመቱ ከሚደርስባት በደለል መሞላትና በጎርፍ መጥለቅለቅ ስጋትና ጥፋት ሊያድን የሚችል ዓለም አቀፍ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ንድፍና ስልትን በመከተል ነው ግድቡን እየገነባች ያለችው። ይህንንም በውሃ ኃይልና ግድብ ግንባታ ምሕንድስና ትልቅ ስምና ዝናን ያተረፉ፤ ከምትተማመንባቸው ምዕራባውያን አገራት የተመረጡ፣ በዘርፉ አንቱ የተባሉ የፈረንሳይ፣ ደችና ጀርመን ዓለም አቀፍ አጥኝ ድርጅቶች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሳሿን ግብጽን ጨምሮ በአንድም የታችኛው ተፋሰስ አገር ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትል አረጋግጠዋል።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ግድቡ በማንም ላይ ጉዳት እንደማያደርስ በዓለም አቀፍ አጥኝዎች ሳይቀር አስመርምራ አረጋግጣ ዓለም አቀፍ አሠራርን ጠብቃ ግድቧን በጥንቃቄ እየገነባች ቢሆንም እልኋን ለማስጨረስ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ከግብጽ ጋር ስትደራደር ከርማለች። ይሁን እንጅ ትዕግስት ፍርሃት የመሰላት ግብጽ የግድቡ ግንባታ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ መምጣቱንና ኢትዮጵያም በሃብቷ መጠቀሟ የማይቀር መሆኑን ስትረዳ “ዘመድ ከዘመዱ አህያ ከአመዱ” እንዲሉ የግብር አጋሮቿን በመተማመን ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ በመውሰድ “ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ ልትሞላው ነው” በማለት የቂል ክሷን አቀረበች።

የቢጤዎቿን የእነ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል፣ ራስ ብቻ ደህና” ባህርይ ስለምትተማመንም ድርድሩን አሜሪካና የዓለም ባንክ ይታዘቡልኝ በማለት እዬዬ አለች። ትዕግስቷ የማያልቀው ስልጡኗ ኢትዮጵያም አሜሪካና የዓለም ባንክ እነማን እንደሆኑ ጠንቅቃ ብታውቅም “ታግሶና አክብሮ ማሸነፍን” ከነ መይሳው ካሳ፣ ከነ በዝብዝ ካሳ፣ ከነ እምዬ ምኒሊክ የወረሰችው ሃብቷ ነውና እሽ እስኪ እንዳልሽው ይሁንልሽ ብላ በጨዋ ትህትና ፈቀደችላት። ይሁን እንጂ እንደተጠበቀው አሜሪካና ዓለም ባንክ በብርሃን ፍጥነት ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት ተቀይረው በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኗቸውን በማሳረፍ ያልበላቸውን ማከክ ጀመሩ።

ከዚያም በካንጋሮ ዝላይ ማራቶን ዘልለው አዛዥ ነን ብለው አረፉ። እነ ግፍ አይፈሬ አሜሪካ በወዳጃቸው ትዕዛዝ ተመርተው፤ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ሺህ ዘመናት በማይደረስበት ከፍታ ጸንተው የቆሙበትን የፍትህ ቀይ መስመር አልፈው በዓባይ ግድብ አያያዝ እና በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ ሰነድ አዘጋጅተው በአስቸካይ ፈርሙ አሉ። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ዋ! ብለው በአንድነት ተነሱ። መሪዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ በ “ታላቋ አሜሪካ” የድፍረት ትዕዛዝ ሳይሸበሩ እንደ አባቶቻቸው ቆፍጠን ብለው “የአገራችንን ጥቅም የሚነካ ማንኛውንም ዓይነት ስምምነት አንፈርምም!” አሉ።

“አስር ጊዜ የታላቋ ብሪታንያ ንግሥት አትበል፤ እዚህም የታላቋ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነው ያለው” ብለው ነበር አጼ ቴዎድሮስ እነርሱ ብቻ ታላቅ የሆኑ ለሚመስላቸው የያኔው የ “ታላቋ ብሪታኒያ” መልዕክተኛ። ታዲያ ዶክተር አብይስ የ“ታላቋ አሜሪካ”ን ትዕዛዝ እሽ ይበሉ እንዴ!? አላሉምም፣ አይሉምም! ምክንያቱም እርሳቸውም እኮ የታላቋ ኢትዮጵያ መሪ ናቸው። እናማ ነክተው እሳቱ ካልበላቸው በቀር ከእነርሱ በላይ ኃያል ወይም ጀግና የሌለ የሚመስላቸው ቂሎቹ ምዕራባውያን እነ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ “ኢትዮጵያ፣ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ስምምነት ላይ ሳትደርስ እና ሰነዱ ላይ ሳትፈርም በግድቡ ላይ ምንም አይነት ውሃ መሙላት እንዳትጀምር” በማለት ስንፍናቸውን ገለውም ነበር። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የልማትን ጉዳይ ወደጸጥታው ምክር ቤትም እንዲወሰድ ተደርጎማል።

የደነፋ ቢደነፋም ግን ጽኑዋ አገር ኢትዮጵያ ይህ ሁሉ የምቀኝነት መሰናክል ሳይበግራት ሁሉንም እያሸነፈች የታላቅነት ጉዞዋን ቀጥላለች። በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ሆናም ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት አጠናቅቃ ለሦስተኛው እየሠራች ትገኛለች። በዚህም ለመጀመሪያው ዙር ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችላትን ውሃ በመያዝ በሁለቱ ተርባይኖች ወደ 750 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል በሙከራ ደረጃ ማመንጨት ጀምራለች። እናም ግብጽና አጋሮቿ የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ሁሉንም ዓይነት ዘዴ ተጠቅመው የቻሉትን ሁሉ ቢያደርጉም ትዕግስተኛዋ ኢትዮጵያ ሁሉንም ጽናት እያሸነፈች በድል አድራጊነት ወደፊት እየገሰገሰች ትገኛለች።

አሁን ላይም ከጫና ተቀባይነት ወደ ጫና ፈጣሪነት እየተሸጋገረች ትመስላለች። በዚህም የኃይል ማመንጫ ግድብ ብቻ ሳይሆን የኃያልነት ማመንጫ አሸናፊነትን ጭምር ገንብታ ዕውን ለማድረግ ጫፍ ደርሳለች። ይህም የዓለም የኃይል ሚዛን ከ “ፔትሮ ዶላር” ወደ “ሃይድሮ ዶላር” እየተለወጠ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ታላቋ አገር ኢትዮጵያም ጊዜዋን ጠብቃ ሃብቷን ጥቅም ላይ አውላ ዳግም ወደ ኃያልነት መንበር እየመጣች ለመሆኗ ማረጋገጫ ነው። ኢትዮጵያን ዳግም ኃያል አድርጎ እግዚአብሔር ይባርክ! ሰላም!

ይበል ካሳ

አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply