ዩክሬን ከአየር የሚመጣ ጥቃት መከላከል አትችልም ” አብቅቶለታል”፤ ፕሬዚዳንቱ ደም እንዲለገስ ጠየቁ፤

“ዓለም ሁሉ ከዩከሬን ጋር በጸሎት አብሮ ነው” ሲሉ ጆ ባይደን ሰማያዊ መፍትሄ የተመኙለት የዩክሬን ቀውስ ወደ ጦረነት ሲቀየር ቅድሚያ የተደረገው የዩክሬንን የአየር ጥቃት መከላከል አቅም አልባ ማድረግ ነበር። የፎክስ ቲቪ ወኮል ከኬቭ በቀጥታ ” It has gone” ሲል የዩክሬን የአየር መከላከያ ሙሉ በሙሉ በውደሙን ዘግቧል።

ፐሬዚዳንት ጆ ባይደን የተከተሉትን መንገድ ሲተች የሰነበተውና ” ትራምፕ በስልጣን ላይ ቢሆኑ ኖሮ ይህ አይሆንም ነበር” የሚል ጠንካራ ወቀሳ ያተመው የፎክስ ቲቪ ዘጋቢ ስቲቭ ከኬቭ እንዳለው የዩክሬን የአየር መከላከያ አቅም አልባ መሆኑንንብቻ ሳይሆን፣ የሩሲያ ሃይሎች ወደ በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ዋና ከተማዋ እያመሩ መሆኑንን ነው።

በዩክሬን 40 ሰዎች መሞታቸውና ከዛም ውስጥ 10 ሲቪል እንደሆኑ፣ ቁጥሩም ከዛ በላይ እንደሚጨምር መረጃዎች ከኬቭ እየወጡ ነው። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ደም እንዲለገስ ጠይቀዋል። ውቀታዊ ሁኔታዎችን ለማሳወቅ በአገራቸው ቴሌቪዥን የቀረቡት ፐሬዚዳንቱ፣ በአገሪቱ የክተት አዋጅ ጥሪም አስተላልፈዋል።

ኔቶ አንድን ሰላማዊ አገር፣ ሉዓላዊ አገር፣ መውረር ተቀባይነት እንደሌለው በዋና ጸሃፊው ስቶልተንበርግ አማካይነት ዛሬ ረፋዱ ላይ አስታውቋል። ኔቶ በባህር፣ በየብስና በአየር ያሰማራውን ሃይል ይፋ አድርጓል። ዋና ጸሃፊው ” የተሰባሰብነበት ዋና ዓላማ ይህ ነው” ሲሉ ሩሲያ አሁን እየፈጸመች ላለው ተግባሯ የጋራ ምላሽ እንደሚሰጥ፣ ሰላምም ዋጋ እንደሚያስከፍል፣ አውሮፓ ከስጋት ነጻ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

ናቶ ጀቶች በዝግጅት ላይ መሆናቸውንና ወታደራዊ እቅዳቸውን በየትኛውም ጊዜ ሊያከናውኑ እንደሚችሉም ዋና ጸሃፊው አስታውቀዋል። ዝርዝሩን ግን ለጊዜው ይፋ እንደማያደርጉ ተናግረዋል። እንደ ጸሃፊው ገለጻ ኔቶ ያመረረ መሆኑ ተመልክቷል። ነገ የኔቶ አገሮች ይሰበሰባሉ።

ቢቢሲ የሚከተሉትን ማስታወሻዎች ለመረጃ እንዲሆኑ በገጹ አስፍሯል።

  • በሞስኮ ሰዓት አቆጣጠር ሲነጋጋ 11፡ 55 ላይ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ምሥራቃዊ ዶንባስ ግዛት “ወታደራዊ ዘመቻ “ እንደሚካሄድ አስታወቁ።
  • ሩሲያ ራሷን ለመከላከል ይህንን ወታደራዊ ዘመቻ እንደከፈተች ያስታወቁት ፕሬዚዳንት ፑቲን የዩክሬን ወታደሮች መሣሪያቸውን እንዲያስቀምጡ አሳስበዋል። በሩሲያ ላይ በማንኛውም የውጭ ኃይሎች የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች “ፈጣን” ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል።
  • ሩሲያ የዩክሬንን መሠረተ ልማቶችን በሚሳኤል መምታቷን ዩክሬን አስታውቃለች። ዩክሬን በምላሹ የሩሲያ አውሮፕላኖችን መትታ መጣሏን ብትገልጽም የሞስኮ ባለሥልጣናት ይህንን አልተቀበሉትም።
  • ወታደሮች የጫኑ መኪኖች እና ታንኮች በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ዩክሬን ገብተዋል። ወታደሮችን የጫነ መኪና በአጎራባቿ ቤላሩስ አልፎ በዋና መዲናዋ ኪየቭ በስተሰሜን በኩል ተሻግሯል። ሌላኛው ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2014 ሩሲያ ከዩክሬን በወሰደቻች ክሬሚያ ግዛት በኩል በደቡብ ገብቷል።
  • እስካሁን በተፈጸሙ ጥቃቶች ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
  • የፈሩ ነዋሪዎች ከዋና ከተማዋን ኪየቭ ለመሸሽ ሲሞክሩም ረዥም የትራፊክ መጨናነቅ አጋጥሟል። ሌሎች ነዋሪዎች በየባቡር ጣቢያዎች ጊዜያዊ መጠለያዎችን በመሻት ላይ ናቸው። የቢቢሲ ዘጋቢዎች እንደተናገሩት ነዋሪዎች ጥቃት እንደሚደርስባቸው ቢጠብቁም የወረራው መጠን ግን አስገርሟቸዋል።
  • ዩክሬን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (ወታደራዊ ሕግን) አውጃለች። የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ሩሲያን ከዓለም አቀፍ የስዊፍት የገንዘብ ማስተላለፊያ ሥርዓት ማገድን ጨምሮ ጥብቅ ማዕቀቦች እንዲጣልባት ጠይቀዋል ።
  • ወረራውን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በሰባት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ ደርሷል። የሩስያ መገበያያ ገንዘብ ሩብል በዶላር፣ በዩሮ እና በፓውንድ ያለው ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆል አሳይቷል።
  • ወራራውን የዓለም መሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ እያወገዙት ይገኛሉ። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጦርነቱ “አሰቃቂ የሕይወት ጥፋት” ያስከትላል ብለዋል። የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የደረሰው ያልተጠበቀ ጥቃት በጣም እንዳስደነግጣቸው ተናግረዋል።

Leave a Reply