ጥብቅ እርምጃ የሚሻው – ከሃይማኖት ተቋማት እስከ መንግሥት ጓዳ የዘለቀው ሙስና

ሙስና ለዕድገታቸው ጠንቅ ሆኖባቸዋል ከሚባሉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷና ዋነኛዋ አገር ናት። በየወረዳው፣ በየፍርድቤቶችና፣ በትላልቅ ባለስልጣናት ጭምር ሙስና መቀበል ልክ እንደመብት የሚታይበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። 

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም በሙስና መስፋፋት ረገድ ከዜጎችና ከባለሙያዎች በሚሰበሰብ መረጃና ግምታዊ አሰራር በየዓመቱ በሚያወጣው ሪፖርት እ.አ.አ. በ2020 ለኢትዮጵያ ከ100 ነጥብ 39 ሰጥቷታል። 

ይህም ኢትዮጵያን ሙስና እጅግ ተስፋፍቶባቸዋል ከሚባሉ አገራት ተርታ ያሰልፋታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም አስከፊ የሆነውን የሙስና ችግር በማጋለጥ ረገድ ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅ ከሰሞኑ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ አንስተዋል፡፡

የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ጥናትና የማማከር አገልግሎት የሚሰጠው ፍሮንቲየር አይ ተቋም የኢትዮጵያ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር በላይነህ ለገሰ ተቋማቸው እ.ኤ.አ. በ2021 ሙስና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ጉዳት በተመለከተ ጥናት መሥራቱን ገልጸው፤ በጥናቱ ውጤት መሰረት ሙስና ኢትዮጵያ ውስጥ የገነገነ አገራዊ ችግር ሆኖ መቀጠሉን ይጠቁማሉ። 

ሌብነትን መከላከል የሚገባቸው ተቋማት ጭምር የለየለት ዘረፋ ውስጥ መግባታቸውንም ያነሳሉ፤ በተለይም የሃይማኖት ተቋማት፣ የጉምሩክና ቀረጥ ተቀባይ ተቋማት፣ የመሬት አስተዳደር እንዲሁም ከፌዴራል አንስቶ እስከ ወረዳ ደረጃ ያሉ ፍርድ ቤቶች ላይ ሙስና በመስፋፋቱ ዜጎች ምሬት ውስጥ መሆናቸውን ይገልጻሉ። 

ሙስና በድብቅ የሚከናወን በመሆኑ የሚጠፋውን ገንዘብ በትክክል ማወቅ ባይቻልም፤ የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ በሙስና ከሚገኘው ገንዘብ 30 ቢሊዮን ዶላር ወደውጭ እንደሚወጣ ይፋ አድርጓል።

ይሁንና ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊወጣ የሚችልበት ሁኔታ አለ ይላሉ። ምክንያቱም ሙስና በየትኛውም ስፍራ እየተለመደ የመጣ በመሆኑ እንደአገር ከዚህም በላይ መጠን ያለው ገንዘብ ሊወጣ ይችላልና፤ ሕዝብ እየተበዘበዘ ስለመሆኑ ማወቅ አያዳግትም ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡

በጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሪ ጋር የተዛመዱ፣ ከአስመጪና ላኪነት ጋር በተያያዘ እንዲሁም በየመንግሥት ተቋማት ጉዳይ ለማስፈጸም በሚል የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች እንዳሉ መንግሥትም ሕዝብም ያውቃል።

ዋናው ጉዳይ ግን ከወሬ በዘለለ ቁርጠኛ ርምጃ መውሰድ ነው። አስፈላጊውን የሕግ ቅጣት እየሰጡ አስተማሪ ውሳኔ መስጠት ይጠበቃል። ለዚህም የመንግሥት ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ይላሉ።

በሙስና ሰዎችን ተጠያቂ ማድረግ ሲጀመርና አንዱን ሲነካ በጥቅም የተሳሰሩ ሰዎች ስላሉ ሌላውንም ሰው ሊነካ ይችላል ያሉት ዶክተር በላይነህ፤ ለዚህም አሰራሮችን ግልጽ ማድረግና ሌብነቱም ሲገኝ ሁሉንም ተጠያቂ በማድረግ ዘላቂ መፍትሄን ማምጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በሙስና የሚጠየቁ ሰዎች ከመንግሥት የፖለቲካ አካሄድ አፈንግጠዋል የሚባሉ ሰዎች ናቸው፤ ይሁንና ዘርፈውም ከመንግሥት ጋር የሆኑ ሰዎች በብዛት ተጠያቂ አይደረጉም የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ጥናት ማዕከል መምህሩ ዶክተር አብዱለጢፍ ከድር ናቸው። 

እንደ ዶክተር አብዱለጢፍ ገለጻ፤ ሙስና የሚገባውን ደረጃ ትኩረት ስላልተሰጠው፤ ዘርፈ ብዙ ውጥንቅጦችን በአገር ላይ እያስከተለ ነው። ከዚህ ቀደምም ያለው ሆነ የቀጠለው ፖለቲካዊ ስርዓት በሙስናና ጥቅም ትስስር ላይ የተመሰረተ ነው።

አገርን አገለግላለሁ በሚል ጥልቅ ዓላማ ይዞ ሳይሆን እበላለሁ በሚል መንፈስ ነው ሰዎች ሹመቶችን የሚቀበሉትም ይላሉ። ስለሆነም ይህን ስር የሰደደ አስተሳሰብ እንዲወገድ ጥረት ማድረግ፤ እንዲሁም ችግር ሲገኝ አስተማሪ ርምጃ መውሰድ ከሕግ አስፈጻሚ አካላት ይጠበቃል። 

ይህ ሲባል ግን ሕግ አስፈጻሚውም በራሱ የሙስና ሰለባ በመሆኑ ርምጃው መጀመር ያለበት እዚያው አስፈጻሚዎቹ ጋር ነው ብለዋል። ምክንያቱም ሙስና የኢኮኖሚ ችግር ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰብም ሆነ የአገር አብሮ የመቀጠል ትልቁ ፈተና ነው። ስለዚህ ሙስናን ወይም ሌብነትን መቀነስ ካስፈለገ ከመንግሥት ጋር የተጠጉትንም ጭምር ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ይሞግታሉ።

ስለሆነም ካንጀት ካለቀሱ ዕንባ አይገድም እንደሚባለው ሁሉም የሕግ አስፈጻሚዎች በሃቀኝነት ከሰሩ ውስብስብ የሆነውን የሙስና ወንጀል እንዲቀንስ ማድረግ ይችላሉ። መረጃ ላይ መሰረት ያደረገ አሰራርን በመከተልና የፖለቲካ ወገንተኝነትን ባራቀ መንፈስ በመቆጣጠር ዋነኛ ሙሰኞችን ማደን እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ።

ዶክተር አብዱለጢፍ እንደሚሉት፤ አስተማሪ የሕግ ርምጃ በመውሰድ ከዚህ ችግር አገር እንድትድን ማድረግ ያስፈልጋል። 

በዚህ ሂደት ህብረተሰቡም ሆነ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሙስናን በማጋለጥ ረገድ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ መሆን እንዳለባቸው ይመክራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንደገለጹት፣ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን የምርመራ ሥራዎችን በየተቋማቱ እንዲሠሩ እና ተቋማቱም ለመገናኛ ብዙሃን በራቸውን ክፍት እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን  የካቲት 20 /2014

Related posts:

ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት መኖር እና የሚያስከትለው ውጤት
በዳኝነት ስርአቱ ላይ የሚታዩ የሙስና ተግባራትን ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ ይፋ ሆነ
ጉቦ ስትቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘችው የመሬት ልማት መኔጅመንት ባለሙያ ክስ ተመሰረተባት
የደህንነት ሰራተኛ ነኝ በማለት ወንጀሎችን ሲፈፅም የነበረው ተከሳሽ በፅኑ እስራትና ገንዘብ ተቀጣ
ከሳኡዲ ተመላሾች መካከል ወንጀል የፈጸሙ ላይ ምርመራ ሊጀመር ነው- የሰው ንግድ አንዱ ነው
በኢድአልፈጥር በዓል የጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል የተጠረጠረው ፖሊስ ፍርድ ቤት ቀረበ
የከተማ መሬትን በወረራ ለመያዝ ጥብቅ ደን በጨፈጨፉ 97 ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ
የመኪና ሌቦቹ ተፈረደባቸው
መድሃኒት ከመጋዘን ሲቸበችብ የተደረሰበት ሚካዔል ዘውገ ተፈረደበት
ለባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የተዘረጋ የኤሌክትሪክ ሽቦ የሰረቁ በጽኑ እስራት ተቀጡ
አስመስሎ በመፈረም ከ12 ሚሊየን ብር የዘረፉ ተከሰሱ
ከ33 ሺህ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ምንነትና ልዩ ባህሪያት
በ25 ሄክታር የባለሃብቶች አትክልትና ፍራፍሬ ማሳ ላይ ጉዳት ያደረሱ ተጠርጣሪዎች ተያዙ
ደብረጽዮንና ጌታቸውን ጨምሮ 37 ተከሳሾች በመገናኛ ብዙሃን ጥሪ እንዲደረግላቸው ታዘዘ

Leave a Reply