ሚተራሊዮን

ሚተራሊዮን 24 ምዕራፎችና 262 ገፆች ያሉት ባዮግራፊክ ይዘት ያለው ግሩም ድንቅ መጽሀፍ ነው። ለማስታወቂያ ሳይሆን እውነትን ለመግለፅ።

ከቀኑ 7:00 ጀምሬ ከምሽቱ 2:30 ነበረ የጨረስሁት። የገረመኝ በፍጥነት መጨረሴ ሳይሆን የታሪኩ ጥልቅ የምርምር እሳቤው ነበረ።

ከባህርዳር ጎንደር፣ ከዋግህምራ ግሺ አባይ፣ ከአዲስ አበባ እስራኤል፣ ቴላቪቭ ቤተልሄም~ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ሥፍራ እሰከመካነ መቃብር፣ ታዕምራዊ ሥፍራና ታሪካዊ ቦታ በምናብ ይዞን ይሄዳል። በእውነት የጸሀፊው ብዕር እንደ ግዮን ዥረት ሁሉንም ያጥግብ!

ሚተራሊዮን የተባለች ውብ ሴት… ልጆች ያሏት፣ ሀብት የሞላት፣ ነገርግን ከማህጸኗ በወጡት ጡት ነካሽ ልጆች የምትሰቃይ፣ ዘወትር እህህህ… እያለች የምታቃስት፣ ጸጋው ሞልቷት በድህነት የምትማቅቅ፣ ውበት ኖሯት በጉስቁልና የጠወለገች፣ ያለማቋረጥ ከገላዋ ደም እንደውኃ የሚፈስባትን እናት ለማዳን የሚደረግ ከፍተኛ መሥዋዕትነትን በባዮግራፊካል አጻጻፍ ቅርጽ ይተርካል።

መጽሐፉ የአገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታንም ይዳስሳል።

አዎ! ፖለቲካችን በጣም ይረብሻል፣ የፖለቲከኞቻችን ነገረ ሥራ ሁሉ ከተሥፋ ይልቅ የመከራ ነጋሪት የሚጎስም ነው።

የምወዳትን፣ የምመካባትን፣ አገሬ ክብሬ፣ የምላትን ኢትዮጵያ “ትፈርሳለች ትበታተናለች” እያሉ ያሟርቷሉ። እንደ ቁራ ተሰብስበው መበተኗ አይቀሬ መሆኑን ይለፋሉ። በቃ ትውሉዱን ሁሉ ተስፋ ያስቆርጡታል።

ይህ የፖለቲካ መስመር ከ60ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሥልጣን ማግኛ ዘዴ ሆኖ ተቀጣጥሏል። ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ቀናዒ እንደሆነ አገሩን ከሀይማኖቱ ለይቶ የማያይ ልበ ስሱ፣ አንጀቱ ርኅሩህ መሆኑን ስለሚያውቁ በሚወደው ነገር እያስፈራሩና እየተገዘቱ ዝም እንዲል አድርገው ወደ ሥልጣን መንጠላጠል የታወቀ ዘዴ ሆኗል።

በአገሪቱ አንድ ማዕዘን ላይ ያለን ነገድ ሰበብ አድርገው “እገነጥላለሁ” “እበታትናለሁ” ሲሉ “በቃ ይሁንልህ አንተ እንደወደድህ ይደረግ” ተብሎ ማዕከላዊውን ሥልጣን እንዲቆናጠጥ በር ከፍቷል።

እንደ ፖለቲከኞች ከሆነ ኢትዮጵያ የጨው ክምር ነች። እንኳን ጥንታዊት አገር በጢስ ያረጀ ቤት እንኳን ይፈርሳል ሲባል ይጨንቃል አይደል እንዴ? ኢትዮጵያ በህሌናችን ውስጥ በጽኑ ተስላ በፍቅር ታትማ እንዳትኖር በጥፍራቸው እየቧጨሩ ሕሊናችንን ያደሙታል።

ኢትዮጵያ እነርሱ ሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ምቹና የተረጋጋች አገር፣ ሲወርዱ ግን አብራቸው የምትወርድ የእንቧይ ካብ ያደርጓታል።

ከዚህ የማስፈራራት ፖለቲካ፣ ከዚህ “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” አስተሳሰብ ወጥቶ የተስፋና የቅንነት ፖለቲካ ይመጣል። እስከዚያ “እንቁራሪቶች ሲጮሁ ባህሩ ሁሉ የእነርሱ ይመስላቸዋል” እንደተባለው ከእነርሱ የሚገዝፍ፣ የሚበልጥ፣ የሰከነ መረዋ ድምጽ ሲመጣ ቃጭል ድምጻቸውን ይዘው ለመጨረሻ ጊዜ ከላይዋ ላይ እንደ ትቢያ ይራገፋሉ።

ጸሀፊው…ከኢትዮጵያ የተፈጥሮ በረከቶቿ ውስጥ ዓባይን መዘዝ አድርጎ ከግዮን ወንዝ ጋር ያለውን አንድነት ይተርክልናል።

የአባይ ወንዝ መነሻው ሰከላ ወረዳ ግሺ አባይ ነው። የዚህ ወንዝ መነሻ ጋን ወይም ምንጭ በተለያዩ አጥኚዎች ብዙ ተብሏል። ከነዚህ ውስጥ የግሪክ አፈታሪክ እንደሚያትተው “የግሺ አባይ አካባቢ በመሬት ውስጥ የተቀበረ ታላቅ ሀይቅ/ Great Subtranian Lake/ በማለት ይገልጻል። ዘመናዊው ሀይድሮሎጂስቶች ጭምር የግሺ ዓባይ አካባቢ የውኃ ጋን መሆኑን ይስማማሉ። ብቻ ስለ ዓባይ ብዙ ብዙ ይባላል። ድጋሚ ጥናት መደረግ አለበት ብየ አምናለሁ።

ይሁንና ከግሺ ዓባይ ወጥቶ አባይ ተብሎ የኢትዮጵያን መሬት ሰንጥቆ፣ አፈር ማዕድናትን ተሸክሞ፣ ቃልኪዳናችንን ይዞ ነው ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚሄድ።

እንደ ታላቁ መጽሀፍ ቅዱስ ቢሆን ኖሮ ከግሺ አባይ ወጥቶ ኢትዮጵያን ሁሉ መክበብ ነበረበት። ነገር ግን ከኢትዮጵያ መልከዓ ምድር አቀማመጥ አኳያ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄን ያስነሳል።

እስራኤላውያንን “ማርና ወተት የምታፈስ አገር ትወርሳላችሁ” ተብለው ከነዓን ሲደርሱ የጠበቃቸው ግን ደረቅ ምድር ነበር። ነገርግን አሉ ” እግዚአብሔር አይዋሽም” ማርና ወተት ምድሪቱ ካላፈሰሰች የእኛ ስንፍና እንጂ የእርሱ መዋሸት አይደለም” ብለው አመኑ። እናም ከናጌብ በረሃ እስከ ጃፋ፣ ከሰማሪያ እስከ ይሁዳ ምድር በደረቅ መሬት ላይ ማርና ወተት ፈለቀ።

“ግዮን ኢትዮጵያን ሁሉ ይከብባል” የተባለው ግዮን ግን መክበብ ሳይሆን አቋርጦ አፈርና ጥሪት አሟጦ የሚሄድ ሆነ። እግዚአብሔር ዋሸ? ታላቁ መጽሀፍስ አበየ? አይደለም! እኛ የዚህ ትውልድ አካሎች በተስፋው ቃል አለማመናችን ነው። “ከገነት ወጥቶ ኢትዮጵያን ሁሉ ይከባል” የተባለውን ዘንግተን አንቀላፍተን ውኃውን ቁልቁል እንዲሄድ መፍቀዳችን፣ የመንፈሳዊ እሴት ዝለት የወለደው የሥጋ ስንፍና ያመጣው ነው።

ኢትዮጵያ ሕመሟንም መድሀኒቷንም፣ ድህነቷንም ብልጽግናዋንም፣ ጉስቁልናዋንም ውበቷንም በጉያዋ የያዘች ምሥጢር አገር ነች። እንዴት ነው መድሀኒት ይዘን መታመም? እንደምን ያለ ነው ብልጽግና ቁልፉን እያለን ድሀ መሆን? ኃይል ታቅፎ ደካማ መሆን? እንደምን ያለ ይሆን ውብ የሚያደርገን ብርሀን ይዘን በጨለማ መኖር?

ፀጋ ይዘን መጎሳቆል፣ እንደምን ያለ ይሆን በደምና በሥጋ ተሳስረን ቃልኪዳን መጠበቅ ሲገባን እርስ በርስ መባላት?

ግዮን ኢትዮጵያን ይከባል ሲባል ፉካሪያዊ ሚስጥሩን ከወሰድነው …የዓባይ ውኃ ሀይል፣ ፈውስና በረከት ነው።

ልብ በል የዓባይ ግድብ ሲያልቅ ኃይል ያመነጫል። ይህ ሀይል ኢትዮጵያን ሁሉ ይከባል። እስከ ሞያሌ፣ ከካራማራ እስከ አሶሳ ድረስ ኢትዮጵያን በብርሀን ይከባል። በዚያ ፋብሪካዎች ያሽካኩበታል። ባቡሮች ይወነጨፉበታል፤ መንደሮችና ከተሞች ይደምቁበታል።

በተራራማ አገራቸው በየሸንተረሩ እየተንደረደሩ የሚፈሱትን ወንዞቻቸውን በጨለማ ብርሀን፣ የድካም ጉልበት፣ የርኩስ መንፈስ መቀደሻ፣ የህሙማን መፈወሻ የጥም መቁረጫ፣ ከሀጢአት መንጺያ፣ ጸጋቸው ይሆን ዘንድ ፈጣሪ በታላቁ መጽሀፍ ቅዱስ የተጻፈ ቃልኪዳን ሠጥቶናል።

እነሆ በተስፋይቱ ምድር የተፈጠርን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለዚህ ቃልኪዳን ፍቺ እንተጋ ዘንድ ይገባናል። ከገባንበት የሞራል ውድቀት ቀና ለማለት ዳግመኛ መወለድ አለብን።

ማጠናቀቂያዬ~

መጽሐፉን እንድታነቡት እጋብዛችኋለሁ፣ ታተርፉበታላችሁና። መጽሐፉ የከሸፈ ትውልድን ያንጻል። የጸሀፊው ብዕር እንደ ግዮን ዥረት ሁሉንም ያጥግብ!

ፀሐፊ አለማየሁ ዋሴ ምሥጋናዬ ጥልቅ ነው።

Via – book for all Fb

Leave a Reply