ከዩክሬን ግጭት ለማምለጥ የሚሞክሩ አፍሪቃውያን ፖላንድ ድንበር ላይ ዘረኝነትና አድልዎ እንደደረሰባቸው ተናገሩ። ዩክሬን የነበሩት እነዚሁ አፍሪቃውያን ጦርነቱ ሲነሳ ከዩክሬን ወደ ፖላንድ ለመሻገር ሲሞክሩ ባለስልጣናት ድንበር ላይ አስቁመው አጉላልተውናል ብለዋል። ብርዱ በበረታበትና ምግብም ማግኘት ችግር በሆነበት በዚህ ወቅት ላይ ድንበር ጠባቂዎች ነጭ ስደተኞችን ወደ ፖላንድ በቀላሉ ሲያስገቡ እነርሱን ግን በክፋት እንዳይሻገሩ እንዳስቆሙዋቸው ተናግረዋል።እነዚሁ አፍሪቃውያን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን ያሳራጯቸው፣ ሁኔታውን የሚያሳዩ አንዳንድ ቪድዮዎች በርካቶችን ማስቆጣታቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዲ ፒኤ ዘግቧል።

ከፍተኛ በተባለ የዩክሬን የትምህርት ጥራትና በአነስተኛ ክፍያዋ የተሳቡ በሺህዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ዩክሬን ውስጥ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። አብዛኛዎቹም ከናይጀሪያ፣ጋና ፣ኬንያ፣ደቡብ አፍሪቃ፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ናቸው። ናይጀሪያ የዩክሬን ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቃለች ። ድርጊቱ እንዳሳሰባቸው የተናገሩት የናይጀሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂኦፍሪ ኦኒያማ የዩክሬኑ አቻቸው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል። የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ በበኩላቸው የዩክሬን ድንበር ጠባቂዎች ሁሉንም የውጭ ዜጎችን እንዲያስወጡ ትዕዛዝ የተሰጣቸው መሆኑን አስታውቀው በአፍሪቃውያኑ ላይ ደረሰ የተባለውን መድልዎ ለማጣራትና አፋጣኝ እርምጃም ለመውሰድ ቃል እንደገቡላቸው ኦኒያማ በትዊተር አስታውቀዋል። የፖላንድ ባለስልጣናት በበኩላቸው የቀረበውን ቅሬታ ውድቅ አድርገዋል። የደቡብ አፍሪቃ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሌይሰን ሞንየላ ደቡብ አፍሪቃውያን ተማሪዎችና ሌሎች አፍሪቃውያን በዩክሬንና በፖላንድ ድንበር ላይ መንገላታታቸውን በትዊተር ጽፈው ነበር።የጋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሺርሊ አዮርኮር ቦችዌይ ግን ጋናውያን ተማሪዎች ችግር አላጋጠማቸውም ብለዋል። ከዩክሬን ከወጡ 220 ጋናውያን ውስጥ 38ቱ ካለምንም ችግር የፖላንድን ድንበር ማቋረጥ ችለዋል እንደ ሚኒስትሯ። ሆኖም ከ460 በላይ ጋናውያን ግን ወደ ጎረቤት አገራት ለመሄድ በጉዞ ላይ ናቸው ብለዋል። የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘገባ ኢትዮጵያውያኑ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አላካተተም።

Bia Jamal abdulaziz

Africa studies in Ukraine boarder discrimination

Leave a Reply