• ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)


የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለ126ኛው የዐድዋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው፤ ዐድዋና ኋላ ቀርነት፤ ዐድዋና ድህነት፤ ዐድዋና የእርስ በእርስ መከፋፈል አብረው አይሄዱም፡፡ ጨለማና ብርሃን ናቸው'” ሲሉ አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።

እንኳን ለዐድዋ ድል 126ኛ ዓመት አደረሳችሁ!

ጀግኖች እናቶቻችንና አባቶቻችን ቅኝ ተገዥነትንና ባርነትን፣ የበታችነትንና ውርደትን እምቢ ብለው ታሪክ የሠሩበትን የዐድዋ ድል በዓል ለማክበር በመቻላችን ዕድለኞች ነን፡፡ በዓሉ ነጻ የወጣንበት አይደለም፡፡ ነጻነታችን እንዳይደፈር በክንዶቻችን ያስጠበቅንበት እንጂ፡፡ እኛ የነጻነት በዓል የለንም፤ የድል በዓል እንጂ፡፡ ይህ ምን ጊዜም ስንኮራበት የምንኖር ታሪካችን ነው፡፡

የዐድዋ ድል አፍሪካውያን፣ እስያውያንና ደቡብ አሜሪካውያን የባርነትን ቀንበር እንዲሰብሩ፤ የቅኝ ግዛትን ሸክም እንዲያስወግዱ፤ የበታችነትን ፖሊሲ እንዲያስቀይሩ አድርጓቸዋል፡፡ የዐድዋ ድል በጥቁርና በነጭ መካከል የነበረውን የተበላሸ ትርክት የቀየረ፤ የጥቁር ሕዝቦችን ማንነት ያስመሰከረ ገድል ነው፡፡ ኢትዮጵያን መንካት የሚያስከትለው መዘዝ ምን እንደ ሆነ አስተምሮ ያለፈ ደማቅ ሐውልት ነው፡፡

የዐድዋ ድል ውድ ገንዘብ ነው፡፡ ወደ ብዙ ነገሮች ሊመነዘር የሚችል፡፡ ጥያቄው ግን ‘ይሄን ውድ ገንዘብ ለተገቢው ነገር መንዝረን ተጠቅመንበታል ወይ?’ የሚለው ነው፡፡ ኋላ ቀርነትን ለማስወገድ፤ ድህነትን ለማጥፋት፤ ረሃብን ከመገለጫነት ለማስቀረት፤ ዴሞክራሲንና ፍትሕን ለማስፈን፤ አንድነትንና ወንድም/እኅትማማችነትን ለማጽናት፣ ያደረግነውን ጥረትና ያገኘነውን ስኬት ስንመዝነው፣ የዐድዋ ድል በተገቢው መንገድ ተመንዝሮ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ያሳየናል፡፡

ባርነትንና ቅኝ ተገዥነትን፣ የበታችነትንና ውርደትን እምቢ ብለን የከፈልናቸው መሥዋዕትነቶች በሀገራችን ሉዓላዊነት፣ ክብርና ነጻነት ላይ ወሳኝ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ የማትደፈር፣ በነጻነቷ ዘለዓለም የምትኖርና ሉዓላዊት የሆነች ሀገር እንድትኖረን አድርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከእነዚህ እኩል እምቢ ልንላቸው የሚገቡን ነገሮች ነበሩ፡፡ እነርሱን እምቢ ባለማለታችን ታሪካችንና ጉዟችን ምርቅና ፍትፍት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ነጻነታችን፤ ድላችን፣ ክብራችንና ኩራታችን ሙሉ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

የቅኝ ግዛትና የባርነትን ያህል – ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለምንድን ነው አምርረን ያልታገልነው? የበታችነትና የውርደትን ያህል ረሃብንና ኢዴሞክራያዊነትን ለምንድን ነው መሥዋዕትነት ከፍለን አሽቀንጥረን ያልጣልነው? በቅኝ ከመገዛትና በባርነት ከመማቀቅ የሚታደጉን ጀግኖች የጦር መሪዎችን ያፈራነውን ያህል፣ በድህነትና በኋላ ቀርነት ከሚመጣ ውርደት የሚታደጉን መሪዎች ያላፈራነው ለምንድን ነው? በቅኝ ገዥዎቻችን ላይ አንድ ሆነን የተነሣነውን ያህል በድህነትና በኋላ ቀርነት ላይ አንድ ሆነን ለመነሣት ያልቻልነው ለምንድን ነው? ባርነትን እንመረራለን፤ ቅኝ ተገዥነትን እንጸየፋለን፤ ከእነዚህ ጋር ለአንድ ቀንም ውለን ለማደር ፈቃደኞች አይደለንም፡፡ ታድያ ከኋላ ቀርነትና ለድህነት ጋር ለሺህ ዘመናት ለመኖር እንዴት ቻልን? ለምን አላንገሸገሹንም? ለምን አላስመረሩንም? አንድ ሆነን ያገኘነውን የዐድዋ ድል ተከፋፍለን እንዴት እናከብረዋለን?

ቅኝ ገዥዎችን ያሳፈርንባቸው፤ ወራሪዎችን የቀጣንባቸው የድል ቀናት ሞልተውናል፡፡ እየደጋገመ የሚያጠቃንን ድርቅና ረሃብ፤ እጅ ተወርች ያሠረንን ኋላ ቀርነት፣ ዛሬም ስንዴ እንድንለምን የሚያደርገንን ድህነት የቀጣንባቸውን የድል ቀናት የምናከብረውስ መቼ ይሆን?

እኛ ስለ ዐድዋ ስንናገር – እነርሱ ስለሚረዱን እህል፤ እኛ ስለ ማይጨው ስንተርክ – እነርሱ ስለሚሰጡን ርዳታ፤ እኛ ስለ ካራማራ ስናወራ – እነርሱ ስለሚሰደዱት ወገኖቻችን፤ እኛ ስለ ዶጋሊ ድል ስንኮራ – እነርሱ ስለ ሕጻናት መቀንጨር እየነገሩን ይገዳደሩናል፡፡ በጀግኖች እናቶቻችንና አባቶቻችን ገድል እንዳንኮራ በሰነፎቹ ልጆቻቸው ምክንያት ሊያሸማቅቁን የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይሄ ነው ታሪካችንን ምርቅና ፍትፍት ያደረገብን፡፡

የዐድዋ ድል ልጆች ሆይ!

የዐድዋን ድል እንደ ውድ ገንዘብ መንዝረን መጠቀም ከፈለግን፣ ሐሳባችንንም፣ ብዕራችንንም፣ ዕውቀታችንንም፣ክህሎታችንንም፣ ጉልበታችንንም ሦስት ነገሮችን በዋነኛነት ለማጥፋት እናውላቸው፡፡

ድህነትን፣ ኋላ ቀርነትንና መከፋፈልን፡፡ እነዚህ ሦስቱ ጠላቶቻችንን በዐድዋ ገጥመን እንዳሸነፍናቸው አፍረው ከተሸነፉ፣ ኢትዮጵያ በቀድሞ ጀግኖቿ የምትኮራ ብቻ ሳትሆን፣ በአዲሶቹ ጀግኖቿም በክብር የምትጠራ ሀገር ትሆናለች፡፡ የመጀመሪያውን ዐድዋ በክብር የሚያስጠራው ሁለተኛው ዐድዋ ነው፡፡ ሁለተኛው ዐድዋ ደግሞ በሦስቱ የኢትዮጵያ ዋና ዋና ጠላቶች በድህነት፣ በኋላ ቀርነትና በመከፋፈል ላይ የሚደረገው ዘመቻ ነው፡፡

እነዚህን ድል ካደረግን ሌሎች ችግሮች ሁሉ በእነዚህ ትከሻ ላይ የተቀመጡ ናቸውና በራሳቸው ጊዜ ድል ይሆናሉ፡፡

የዐድዋ ድል 126 ዓመት ሆነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ ጠላቶቻችን ከዐድዋም በፊት ነበሩ፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ከዐድዋ ድል በኋላም መቀጠላቸው ነው፡፡ ብረትን መቀጥቀጥ እንደ ጋለ ነው ብለን በፋሺዝም ላይ የሰነዘርነውን በትር ወደ እነርሱ አዙረነው ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ በሁለመናዋ የበለጸገች ሀገር በሆነች ነበር፡፡ በድህነትና በኋላ ቀርነት ውስጥ ሆነን፤ ከዚያም ብሶ ተከፋፍለንና ተለያይተን ቀጣዮቹን የዐድዋ ድል በዓላት ማክበር የለብንም፡፡ 130ኛውን፣ 140ኛውንና 150ኛውን የዐድዋ ድል በዓል፣ በበለጸገችው ኢትዮጵያ ዐደባባዮች፣ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጸንተን እንድናከብራቸው የመቁረጫው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ዐድዋና ኋላ ቀርነት፤ ዐድዋና ድህነት፤ ዐድዋና የእርስ በእርስ መከፋፈል አብረው አይሄዱም፡፡ ጨለማና ብርሃን ናቸው፡፡

መልካም የድል በዓል ይሁንልን!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ !
የካቲት 23 ፣ 2014 ዓ.ም.

Leave a Reply