ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ማን ናቸው?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 4ኛው ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ በቀድሞው አጠራር በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረታቦር አውራጃ ልዩ ሥሟ ማር ምድር በመባል በመትታወቅ ቀበሌ ከአባታቸው ከብላታ ፈንታ ተሰማ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ለምለም ገሰሰ በ1930 ዓ.ም ተወለዱ። ከኤጲስ ቆጶስ ሹመታቸው በፊትም አባ ዘሊባኖስ ፈንታ ተብለው ይጠሩ ነበር።

ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ በተወለዱበት አካባቢ ንባብና ዳዊት ከዚያም አጭታን ኪዳነምህረት በምትባል ደብር ምዕራፍና ጾመ ድጓ ተምረዋል። ከዚያም ትምህርታቸውን በመቀጠል ወደ ጎጃም ሄደው በጎንጂ ቴዎድሮስ ገዳምና በዋሸራ በጊዜው ከሚደነቁ መሪ ጌታዎች የቅኔ ትምህርታቸውን ለአራት ዓመታት ተከታትለዋል። ቀጥሎም ወደ ትውልድ ሀገራቸው ተመልሰው በደብረታቦር አውራጃ እስቴ ወረዳ አጋጥ ደብረ ጽዮን የምዕራፍ፣ ጾመ ድጓና ድጓ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።

ብፁዕነታቸው የአቋቋም ትምህርት፣ ዝማሬ መዋሥዕት ከተለያዩ መምህራን ወስደዋል። ጋይንት ወረዳ በምትገኘው ቤተልሔም ቆይተው ድጓ አስመስክረው በመምህርነት ተመርቀዋል። ከዚያም ወደተወለዱበት አካባቢ በመመለስ በአረጊት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ለሰባት ዓመታት ያህል ድጓ አስተምረዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያትክ አቡነ መርቆርዮስ በ1961 ዓ.ም ማዕረገ ምንኩስናን ከጣና ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ ማዕረገ ቅስናንም ከጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል። ፓትርያርኩ የገዳምን ሥርዓት ይበልጥ ለማጥናት በነበራቸው ፍላጎት በባህርዳር አውራጃ ልዩ ሥሙ ጋሾላ በተባለ ገዳም ገብተው የገዳሙን ሥርዓት እያጠኑና ገዳማውያኑን እያገለገሉ ለሁለት ዓመታት ያህል ቆይተዋል።

ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅዳሴና በማሕሌት እያገለገሉ ትርጓሜ ሐዲሳትንና አቡሻኽርን ተምረዋል። ዘመናዊ ትምህርታቸውንም በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ተከታትለዋል። በተጨማሪም ለመምህራን የተደረገውን የስብከት ዘዴ ኮርስ ለሁለት ዓመታት ተምረው የምሥክር ወረቀት ተቀብለዋል።

በቤተክርስቲያን አገልግሎት ዘመናቸውም የደበረብሥራት ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ ሆነው ባገለገሉበት ጊዜ ብዙ ለውጥ ያመጡ መልካም ተግባራትን አከናውነዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ቤተክርስቲያን ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም ባደረገችው የ13 ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በካህናትና በምዕመናን በከፍተኛ ድምፅ ተመርጠው የኦጋዴን አውራጃ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሾመዋል። በቦታው በጠላት የወደሙ ቤተክርስቲያናትን ሲያሠሩ፣ በጦርነት ውስጥ የተሸበረውን ሕዝብ ሲያረጋጉ ከቆዩ በኋላ በዚሁ ዓመት ወደ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተዛውረዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ከነሐሴ 29 ቀን 1980 ጀምሮ 4ኛው ፓትርያርክ ሆነው ተሾመው ቤተክርስቲያኒቱን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ብፁዕነታቸው ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ በፖለቲካዊ ግፊት ሀገራቸውን ለቀው እስከወጡበት ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም ድረስ ለቤተክርስቲያን አጠቃላይ አመራር ሲሰጡ ቆይተዋል። እርቅ ወርዶ ከ26 ዓመት የስደት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ቤተክርስቲያኒቱንና ምዕመኖቿን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ባደረባቸው ሕመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ምሽት ላይ እንዳረፉ የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳወቀ ሲሆን፤ ሲኖዶሱ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባም ሥርዓተ ቀብራቸው መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲከናወን ውሳኔ ተላልፏል።

 ውብሸት ሰንደቁ

አዲስ ዘመን የካቲት 26/2014

Related posts:

«ሕወሓት ጦርነትን እንደ አምልኮ የሚቆጥር ቡድን ነው» – ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ
«በሕገወጦች ላይ ያለ ምኅረት እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ይህ የመንግሥት ተግባር ነው» የአማራ ክልል
125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ
«በአገሩ መከላከያ ላይ አፉን የሚከፍት ሕዝብ የለም፤ መንግስትም አይታገስም» ክብር ለመከላከያ ሰራዊት!!
በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል የተደረገውን የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት ምክር ቤቱ አጸደቀ
የሞት ፍርደኛው የ25 ዓመታት ሰቆቃ! ከመሬት በታች የታፈኑት አባት
«ኢትዮዽያን ማስቀጠል ከሚፈልጉት ጎን በመሆናችን የሚከፋ ከአለ እርሱ መፍረሷን የሚናፍቅ ብቻ ነው!»
ደብዳቤ ለኢትዮጵያ - ከቢልለኔ ስዩም
የዓለም ባንክ የ300 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ፈረመ
"እናቴ ፍጹም እስር ቤት እንድትገባ አልፈግም" ብሎ እግሩን ያጣው ወጣት ምስክርነት ለሮይተርስ
"አልዘምትም" ወይም "ከጠላት ጎን እሰለፋለሁ" ማለት ሲቻል ማውሰብሰብና ማድበስበስ አይገባም!
አብዱላሂ ፋርማጆ ለአዲሱን ፕሬዝዳንት «ሁሉም ወገኖቼ እንዲደግፉህና እንዲጸልዩልህም እጠይቃለሁ»
መንግስ የጸጥታ ሃይሎች ለየትኛውም ዓይነት ትንኮሳ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ማድረጉን አስታወቀ
በትግራይ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ እየደረሰ ነው፤ ከሺህ በላይ የጭነት መኪኖች ታግተዋል፤ 76 ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ተልኳል
የደህንነት ጥናት አዲሱ ምዕራፍ - ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ

Leave a Reply