« የፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ አንድ ሊትር ዘይት 82 ብር ከ15 ሳንቲም ነው» የበላይነህ ክንዴ

አንድ ሊትር ዘይት : የመሸጫ ዋጋ

የበላይነህ ክንዴ ፊቤላ ኢንዱስትያል ኃ/የተ/የግ/ማህበር ዘይት በዝቅተኛ ዋጋ ለገበያ እያቀረበ ነው

– የፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ አንድ ሊትር ዘይት 82 ብር ከ15 ሳንቲም ነው፣

– መንግስት ያስቀመጠውን ኮታ ተደራሽ አድርጓል፣

– እስካሁን 66 ሚሊዮን ሊትር ዘይት አምርቶ ለክልሎች አሰራጭቷል፣

– መንግስት በፈቀደው የውጭ ምንዛሬ መሰረት 105ሺ ሜትሪክ ቶን ድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት ገዝቷል፣

ከአንድ አመት በፊት የምግብ ዘይት ማምረት የጀመረው ፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኃ/የተ/የግ/ማህበር ባሳለፍነው አንድ አመት በ 5ዙር አንድ መቶ አምስት ሺ /105ሺ/ ሜትሪክ ቶን ድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ከ66 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት አጣርቶ ለገበያ አቅርቧል፡፡

ፊቤላ ምርት ሲጀምር አለም ላይ የነበረው የአንድ ሜትሪክ ቶን ድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት ዋጋ 762.50 ዶላር የነበረ ሲሆን በወቅቱ ፌቤላ አንድ ሊትር ዘይት በ40 ብር ለገበያ ሲያቅርብ ነበር ፤ ይሁንና ባለፉት ወራት አለም ላይ የድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁናቴ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ኮቪድ፣አለም ላይ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ፣የሎጀስቲክስ አቅርቦት ችግር እንዲሁም ከሰሞኑ በዩክሬንና በራሽያ መካከል ያለው ግጭት በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡

ድርጅታችን ማምረት ከጀመረ አንስቶ መንግስት በሚፈቅደለት ውስን የውጭ ምንዛሬ አማካኝነት ድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት እየገዛ አጣርቶ ለገበያ እያቀረበ ሲሆን በተለይ በ4ተኛ ዙር አንድ ሜትሪክቶን ድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት 1361 ዶላር በአምስተኛ ዙር አንድ ሜ/ቶን የድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት 1407 ዶላር ገዝቷል፡፡ ይሁንና ይህ የዋጋ ጭማሪ ፊቤላ በአራተኛ ዙር ከገዛበት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረ ቢሆንም ንረቱ በዘይት ገበያ ላይና በዜጎች ኑሮ ላይ ሊያሥከትል የሚችለውን ጫና በመረዳት ድርጅታችን በ4ተኛ ዙር ባመጣበት ዋጋ በአምስተኛ ዙርም ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ ሳይደርግ ለገበያ ለማቅረብ ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፍቃደኝነቱ በመግለጽ16.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ማሰራጨት ጀምሯል ፡፡ በዚህም መሰረት የአምስተኛ ዙር የፋብሪካ በር የመሸጫ ዋጋ ከየካቲት ወር ጀምሮ

ባለ 5 ሊትር የ1 ሊትር ዘይት ዋጋ 85 ብር ከ63 ሳንቲም ሲሆን ድምር 425ብር ከ63 ሣንቲም ባለ 20 ሊትር የ1ሊትር ዋጋ 82 ብር ከ72 ሳንቲም ድምር 1640 ብር ከ72 ሣንቲም ባለ 25 ሊትር የ1 ሊትር ዋጋ 82 ብር ከ15 ሳንቲም ድምር 2050 ብር ከ15 ሣንቲም መሆኑን መግለጽ እንወዳለን ፡፡ ድርጅታችን ፊቤላ ዘይት ካመረተ በኃላ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለክልሎች ባስቀመጠው ድርሻ መሰረት ህጋዊ ፈቃድ በተሰጣቸው 31 ያህል አከፋፋዮች አማካኝነት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ለክልሎች እያከፋፈለ ነው፤ ክልሎችም በየዙር በሚሠጣቸው ኮታ መሰረት ባለፉት 4 ዙሮች የተሰጣቸውን ኮታ በመውሰድ ለተጠቃሚዎች አድርሰዋል፤ ፊቤላ ሲመሰረት በቀን 1.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም ቢኖረውም በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ፣በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በድፍድፋ የፓልም ዘይት ዋጋ በየጊዜው መጨመርና ሌሎች ለፋብሪካው የሚያሥፈልጉ ግብአቶች በመወደዳቸው በአሁኑ ሰዓት ካለው የማምረት አቅም በ50 በመቶ ብቻ እያመረተ ይገኛል፡፡ ይሁንና ፌቤላ ለክልሎች እንዲያቀርብ የሚሰጠው የድርሻ ምጥጥን ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከክልሎቹ ንግድ ቢሮዎች ጋር በመመካከር የሚወሰን መሆኑ እየታወቀ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፌቤላ በቂ ምርት አያቀረበልኝ ባለመሆኑ በጂንአድ ተገዝቶ እየቀረበ ነው በሚል ያወጣው መረጃ ስህተት መሆኑንና በ5ተኛ ዙር የክልሉ ንግድ ቢሮ ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዘይት እንድናቀርብ ኮታ ደልድሎ ያልመደበ መሆኑን ማረጋገጥ እንወዳለን ፡፡ ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከአንድ እስከ አራት ባሉት ዙሮች ለከተማ አስተዳደሩ የተመደበለትን ኮታ ያቀረብን ሲሆን በ4ተኛ ዙር ብቻ 431ሺ ተመድቦለት 455ሺ ሊትር ዘይት ማቅረብ የቻልን መሆናችንን ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

የበላይነህ ክንዴ ፊቤላ ኢንዱስትያል ኃ/የተ/የግ/ማህበር

Leave a Reply