ከ3 ሚሊየን ብር በላይ በቢሮው አስቀምጦ የተገኘው ተከሳሽ በ13 ዓመት ፅኑ እስራና በ75 ሺህ ብር አንዲቀጣ ተወሰነበት

የብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ሳይኖረው የባንክ ስራን በመስራት ከ3 ሚሊየን ብር በላይ በቢሮው አስቀምጦ የተገኘው ተከሳሽ በ13 ዓመት ፅኑ እስራና በ75 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት አንዲቀጣ ተወሰነበት ።

ፈድሉ ነጋሽ መሃመድ የተባለው ተከሳሽ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 29 (1)(ሐ) ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በሚል ነበር ዐቃቤ ህግ ክስ የመሰረተበት ፡፡

ተከሳሹ ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ የብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ሳይኖረው በባንክ ስራ መስራት ወንጀል ያገኘውን ገንዘብ በወንጀል ተጠርጥሮ በአራዳ ክፍለ ከተማ ሀብተጊዎርጊስ ድልድይ አካባቢ በሚገኘው ቢሮው ውስጥ በተደረገ ብርበራ 3‚266‚300 ( ሶስት ሚሊየን ሁለት መቶ ስልሳ ስድስት ሺህ ሶስት መቶ ብር ) አስቀምጦ የተገኘ በመሆኑ በፈፀመው በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበታል ።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ለተከሳሽ የዐቃቤ ህግ ክስ እንዲደርሰው ተደርጎና ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉንና ክሱን እንዲያስተባብል ተጠይቆ ተከሳሽም “ ዐቃቤ ህግ የመሰረተብኝን ክስ ተረድቸዋለሁ ነገር ግን ወንጀሉን አልፈፀምኩም ምክንያቱም ገንዘቡ የእኔ ሳይሆን ግለሰቦቹ አስቀምጥልን ብለው የሰጡኝ ነው“ ሲል ክዶ ቢከራከርም ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ዝርዝር 4 የሰው፣ የሰነድና የኢግዚቪት ማስረጃዎች ለችሎቱ አቅርቦ ያሰማና ያስረዳ በመሆኑ ግራ ቀኙ ክስርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አሳልፏል ።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የካቲት 30/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ በ13 ዓመት ፅኑ እስራትና በ75 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ሲወስን በኢግዚቪትነት የተያዘው ገንዘብ ደግሞ በአዋጁ አንቀፅ 35 መሰረት ለመንግስት ገቢ አንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥቷል ።

Via – Ministry of justice

Leave a Reply