የአማራ ክልል አመራሮች ላይ ግድያ የፈጸሙ ተፈረደባቸው

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያ ጥፋተኛ በተባሉ 31 ተከሳሾች ላይ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወሰነ።

በእነ ሻምበል መማር ጌትነት የክስ መዝገብ ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸው የፍርድ ሂደታቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ 55 ተከሳሾች መካከል ቀደም ሲል 20ዎቹ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ተደርጓል።

እንዲከላከሉ ከተባሉት መካከል ደግሞ አራቱ በነጻ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ በቅርቡ መወሰኑ ይታወሳል። በቀረበባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃ ጥፋተኛ የተባሉት ቀሪ 31 ተከሳሾች ላይ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም መሰረት 1ኛ ተከሳሽ ሻምበል መማር ጌትነት፣ 15ኛ ተከሳሽ በላይሰው ሰፊነው እና 44ኛ ተከሳሽ ልቅናው ይሁኔ በሌሉበት እያንዳንዳቸው በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኖባቸዋል። ሙሉጌታ ፀጋዬ፣ ሃምሳ አለቃ አሊ ሀሰን እና ፈቃዱ ምትኩ የተባሉ ሦስት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት፤ ሻለቃ አዱኛ ወርቁ እና ሻምበል ታደሰ እሸቴ የተባሉ ተከሳሾች

ደግሞ በ17 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል። ፍርድ ቤቱ ሻምበል ውለታው አባተና ሃምሳ አለቃ አበበ መልኬ እያንዳንዳቸው በ16 ዓመት፣ እንዲሁም ሃምሳ አለቃ ሲሳይ ገላናው እና ሃምሳ አለቃ በላቸው ዘውዴ በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።

ከዚህ ተጨማሪ ሃምሳ አለቃ አሰፋ ጌታቸውን ጨምሮ ሌሎች 18 ተከሳሾች ላይ እያንዳንዳቸው በ16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት 23ኛ ወንጀል ችሎት ትናንት ባስቻለው ችሎት ወስኖባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾቹ የማህበራዊ አገልግሎትን፣ የቤተሰብ ኃላፊነትን፣ ለሀገር የተከፈለ ዋጋን፣ የጤና ሁኔታ እንዲሁም በአብዛኞቹ ተከሳሾች ላይ የወንጀል ሪከርድን ከዚህ ቀደም አለመኖርን በቅጣት ማቅለያነት መያዙንም አመልክቷል።

በማክበጃነት ደግሞ በህብረትና በማደም ህገመንግሥትና ህገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል በመናድ ከሕግ ውጭ ስልጣን ለመያዝ ሙከራ ማድረግ ከጥፋቶቹ መካከል ተጠቅሰው ይገኙበታል።

በሌሉበት በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው 1ኛ፣ 15ኛና 44ኛ ተከሳሾችን ፖሊስ ካሉበት አፈላልጎ በመያዝ ለማረሚያ ቤቱ እንዲያስረክብ ትዕዛዝ በመስጠት ፍርድ ቤቱ የዕለቱን ችሎት አጠናቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Related posts:

ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት መኖር እና የሚያስከትለው ውጤት
በዳኝነት ስርአቱ ላይ የሚታዩ የሙስና ተግባራትን ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ ይፋ ሆነ
ጉቦ ስትቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘችው የመሬት ልማት መኔጅመንት ባለሙያ ክስ ተመሰረተባት
የደህንነት ሰራተኛ ነኝ በማለት ወንጀሎችን ሲፈፅም የነበረው ተከሳሽ በፅኑ እስራትና ገንዘብ ተቀጣ
ከሳኡዲ ተመላሾች መካከል ወንጀል የፈጸሙ ላይ ምርመራ ሊጀመር ነው- የሰው ንግድ አንዱ ነው
በኢድአልፈጥር በዓል የጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል የተጠረጠረው ፖሊስ ፍርድ ቤት ቀረበ
የከተማ መሬትን በወረራ ለመያዝ ጥብቅ ደን በጨፈጨፉ 97 ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ
የመኪና ሌቦቹ ተፈረደባቸው
መድሃኒት ከመጋዘን ሲቸበችብ የተደረሰበት ሚካዔል ዘውገ ተፈረደበት
ለባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የተዘረጋ የኤሌክትሪክ ሽቦ የሰረቁ በጽኑ እስራት ተቀጡ
አስመስሎ በመፈረም ከ12 ሚሊየን ብር የዘረፉ ተከሰሱ
ከ33 ሺህ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ምንነትና ልዩ ባህሪያት
በ25 ሄክታር የባለሃብቶች አትክልትና ፍራፍሬ ማሳ ላይ ጉዳት ያደረሱ ተጠርጣሪዎች ተያዙ
ደብረጽዮንና ጌታቸውን ጨምሮ 37 ተከሳሾች በመገናኛ ብዙሃን ጥሪ እንዲደረግላቸው ታዘዘ

Leave a Reply