“ ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ ህዝባዊ እምቢተኝነት ይሆናል” ባልደራስ

ገዢው ፓርቲ በምርጫ ፖለቲካ ለመዳኘት ፍቃደኛ እንዳልሆነ አረጋግጠናል ያለው ባልደራስ ፤ በቀጣይ የሚከናወነው የወረዳና አካባቢያዊ ምርጫ እንደ ሀገራዊው ምርጫ አይነት ፌዝ የሚሆን ከሆነ ወደ ህዝባዊ እምቢተኝነት እገባለሁ ብሏል፡፡

ህዝቡ በሰሜኑ ጦርነት ተጋርዶ የ 2013 ምርጫን በቅጡ መገምገም አልቻለም ያለው ፓርቲው ፣ በቀጣይ ይከናወናል ተብሎ በሚጠበቀው አካባቢያዊና የወረዳ ምርጫ ሁለንተናዊ ሁኔታውን ገምግመን እንከን የሚኖረው ከሆነ የትግል ስልታችን ህዝባዊ እምቢተኝነት ይሆናል ብሏል፡፡

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ሊቀ መንበር አቶ እስክንደር ነጋ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ቤተሰቦቻችንንና ስራችንን ትትን እየታገልን ያለነው ለስኬት በሚያበቃ፣ ሌሎች ሀገራትም እንዲያልፉ በተገደዱበትና ውጤታማ በሆነ ስትራቴጂ እንጂ ፣ ዝም ብለን ለመባዘን አይደለም ብለዋል፡፡

ትግል ሶስት ደረጃዎች አሉት ያሉት ሊቀመንበሩ ፤ የመጀመሪያውና ተመራጩ መንገድ የምርጫ ፖለቲካ ነው፣ የምርጫ ፖለቲካ በተደላደለ ዲሞክራሲ ያለ አካሄድ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ በምርጫ ስልጣን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ግን ሁለተኛው ደረጃ ህዝባዊ እምቢተኝነት ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሶስተኛው ደረጃ የትጥቅ ትግል ነው፣ እኛ ግን በትጥቅ ትግል አናምንም፣ በህዝባዊ እምቢተኝነት ግን ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚሉት አቶ እስክንድር ፤ ጠጠር ሳንወረውር እንደ ቱኒዚያና እንደ ታህሪር አደባባዩ የፀደይ የአረብ አብዮት በሞራል ልዕልና አምባገነናዊ ስርአትን ለማፍረስ ነው ራዕይ የሰነቅነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለደራስ ወይም ሌላ ፓርቲ የምርጫ ፖለቲካ አይሰራም ብሎ ስለተናገረ ብቻ ሳይሆን በመጀመርያ ህዝቡ ከጥርጣሬ በላይ (Beyond Reasonable Doubt) በተግባር በምርጫ ውስጥ ገብቶ፤ ምርጫው ውጤት እንደማያመጣ ማየት መቻል አለበት ብለዋል፡፡

በህወሀት አገዛዝ የምርጫ ፖለቲካ እንደማይሰራ በ 97 ምርጫ ካወቀ በኋለ ምርጫ ፖለቲካን ትቶ በማግስቱ ነው ህዝቡ ወደ ህዝባዊ እምቢተኝነት የገባው ሲሉ አክለዋል፡፡
2013 ምርጫ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ ፖለቲካ እንደሚሰራና እንደማይሰራ ፍንትው ባለ መንገድ እንዳንመለከት ያደረገን ህወሀት ነው ያሉ ሲሆን ጥቅምት 24 በለኮሰው ጦርነት ሳቢያ ህዘቡ በጣም ግልፅ ያለ መልስ ሳያገኝበት ነው ምርጫው ያለፈው ብለዋል፡፡

ህወሀት በምርጫ ፖለቲካ ለመዳኘት ፍቃደኛ ያልነበረውን ያህል አሁን ያለው ገዢ ፓርቲም ፍቃደኛ እንዳልሆነ በፓርቲ ደረጃ ያለ ብዥታ አረጋግጠናል ሲሉ አቶ እስክንድር ነጋ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

ሔኖክ አሥራት FM 108

Leave a Reply