ዕንባ ጠባቂ ተቋም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን አስመልከቶ በቀረበ ቅሬታ «አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል»

የ2013 ዓ.ም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን አስመልከቶ በቀረበ ቅሬታና በተካሄደ ምርመራ መሰረት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ


“ዛሬ በዴሞክራሲያዊ ባህሪ ያላስተናገድነውን ትውልድ ነገ መብትህን በሰላማዊ ወይም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ጠይቅ የማለት የሞራል ልዕልና አይኖረንም”

በሀገራችን መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን ለመከታተል ይቻል ዘንድ የተለያዩ የዴሞክራሲ ተቋማት ተመስርተዋል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ተልዕኮው ህገ- መንግስታዊ መርሆች በትክክል እንዲተገበሩ፣ ግልጽ የሆነ መንግስታዊ አስራር እንዲኖር ፣ዜጎች የመብታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑና መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን ማስቻል ነው፡፡

ተቋሙም ይህንኑ ህገ- መንግስታዊ ተልዕኮ ለማሳካት ይችል ዘንድ በተሻሻለው የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1142/2011 ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር መካከል አንዱ ዜጎች አስተዳደራዊ በደሎችን አስመልክተው የሚያቀርቧቸውን ቅሬታዎች ተቀብሎ በመመርመር የአስተዳደር ጥፋት የተፈጸመ መሆኑን ሲያረጋግጥ ተገቢውን የመፍትሄ ሀሳብ መስጠት ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደግሞ በራስ ተነሳሽነት ምርመራ የማካሄድ ስልጣን እንዳለው አንቀጽ 7(2) ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡

በዚህም መሰረት በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን አስመልክቶ ለተቋሙ የቀረቡ ጥቆማዎች እና በተለያዩ ሚዲያዎች ጉዳዩን አስመልክቶ የቀረቡ ዘገባዎችን መነሻ በማድረግ ችግሮችን በምርመራ በመለየት ተገቢውን የመፍትሄ ሃሳብ ለመስጠት በተደረገ የራስ ተነሳሽነት ምርመራ ሪፖርት መሰረት ተቋሙ ተከታዩን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ሀ. የቀረቡ አቤቱታዎችን መሰረት አድርጎ የተካሄደ ምርመራና ግኝቶች

1.በፈተና ወቅት የተፈጠሩ የእርማት ስህተቶች በድጋሚ እንዲታይልን ቅሬታችንን ለፈተናዎች ኤጀንሲ ብናቀርብም ቅሬታችንን ተቀብሎ ሊያስተናግደን አልቻለም በማለት የቀረበውን ጥቆማ በተመለከተ ተቋሙ ባደረገው ምርመራ የፈተናዎች ኤጀንሲ የፈተና እርማትን አስመልክቶ ተማሪዎች ያቀረቡትን ቅሬታ በመቀበል ምላሽ መስጠቱን የገለጸ ቢሆንም የተቋሙ መርመሪዎች ለምርመራ ስራ በኤጀንሲው በተገኙበት ወቅት በርካታ ተማሪዎች ቅሬታቸውን ለማቅረብ በኤጀንሲው ቢገኙም ወደ ውስጥ ገብቶ ቅሬታን ለማቅረብም ሆነ ቅሬታቸውን ተቀብሎ ሊያስተናግዳቸው እንዳልቻለ ይልቁንም ቅሬታቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲያቀርቡ ተነግሯቸዋል፡፡

ቅሬታቸውን ይዘው ወደ በትምህርት ሚኒስቴር በመሄድ ለማቅረብ ጥረት ቢያደርጉም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ጉዳዩ የሚመለከተው የፈተናዎች ኤጀንሲ ነው በሚል ቅሬታቸውን ሳይቀበል የቀረ መሆኑን እና በዚህ ምክንያትም ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቅሬታቸውን ለማቅረብ መጥተው ለእንግልት እየተዳረጉ እንደሚገኙ የተቋሙ መርማሪዎች በቦታው በመገኘት አረጋግጠዋል፡፡

See also  "የሰው ልጅ የመብት ተከራካሪ ነን" የሚሉት የእነ ሂውማን ራይትስ ዎች የሐሰት ሪፖርት ገበና ሲጋለጥ

ማንኛውም ዜጋ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ ለሚመለከተው አገልግሎት ሰጪ ተቋም የማቅረብ መብት እንዳለውና ቅሬታ የቀረበለት አካልም ቅሬታውን ተቀብሎ ያለምንም ገደብ ምላሽ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት በፌደራል የአስተዳደር ስነ ስርዓትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አንቀጽ 20፣21፣22፣23 እና ተከታዮቹ መሰረት ግዴታ ያለበት መሆኑን በአዋጁ በግልጽ ተደንግጓል፡፡

ይሁን እንጂ የፈተናዎች ኤጀንሲ እና ትምህርት ሚኒስቴር በአዋጅ የተጣለባቸውን ሀላፊነት ከመወጣት ይልቅ ቅሬታዎችን አጣርተን ጨርሰናል እና ጉዳዩ እኛን አይመለከትም በሚሉ ተገቢ ባልሆኑ ምክንያቶች የተማሪዎችን ቅሬታ ለመቀበል ፍቃደኛ አለመሆናቸው ከአዋጅ ቁጥር 1183/2012 አኳያ አስተዳደራዊ በደል መሆኑን ተቋሙ አረጋግጧል፡፡

2.የሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ ለቀረቡለት ከ20,000 በላይ ቅሬታዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን ገልጿል፡፡ አብዛኛዎቹ ቅሬታዎች ደግሞ የቀረቡት በኦንላይ(online) ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህ አቤቱታዎች የተሰጠው ምላሽ እንደቀረበው ቅሬታ አይነት በመለየት ሳይሆን ለሁሉም ቅሬታዎች ተመሳሳይ ምላሽ ማለትም ቅሬታው የታየ መሆኑን ብቻ የሚገልጽ ምላሽ ነው የሚሰጠው፡፡ ይህ አሰራር ደግሞ በአቤታታ አቅራቢዎች ላይ ቅሬታን የፈጠረ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

3.የ2013 ዓ/ም የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በሁለት ዙር የተሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተለይ የሁለተኛ ዙር ፈተና እርማት ላይ ስህተቶች የተፈጠሩ መሆኑን የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ በምርመራ ሂደት ወቅት ለተቋሙ መርማሪዎች አረጋግጧል፡፡

በተጨባጭም የእርማት ስህተት አለ በሚል ቅሬታ ካቀረቡ ተፈታኝ ተማሪዎች መካካል ድጋሚ እርማት በተደረገ ወቅት ስህተት የተፈጠረ መሆኑን ማሳያ ወይም ማረጋገጫ መሆን የሚችሉ የማስተካካያ እርማቶች እና ውጤቶች መከሰታቸው በእርማት ሂደቱ ላይ ችግሮች መፈጠራቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መሆናቸውን ተቋሙ አረጋግጧል፡፡

4.ፈተናው በሚሰጥበት ወቅት የጦርነት እና የጸጥታ ችግሮች በነበረባቸው አካባቢዎች ፈተናውን የወሰድን ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ሊወሰንልን ይገባል በሚል የቀረበውን ጥቆማ በሚመለከት የትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ለሚዲያ አካላት በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ላይ በልዩ ሁኔታ ሊታይ የሚችል ጉዳይ እንደሌለ እና የመግቢያ ነጥቡ ላይ ማሻሻያ እንደማይደረግ አሳውቋል፡፡

See also  «አሸባሪውን ሕወሓት በአጭር ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ ፊታችንን ወደ ልማት እናዞራለን»አየር ኀይል

ተቋሙ ጉዳዩን አስመልክቶ ባደረገው ምርመራ መገንዘብ እንደቻለው ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በተሰጠበት ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተለይም በአፋር፣አማራ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጦርነት እና የጸጥታ ችግሮች የነበሩ መሆኑ በመንግስት በይፋ የሚታወቅ ነው፡፡ ጦርነቱ እና የጸጥታ መደፍረሱን ለመከላከል ሕዝብ እና መንግስት በጋራ በርካታ ስራዎችን ያከናወኑ መሆኑ የቅርብ ጊዜ እውነታ ነው፡፡

በዚህ እንቅስቃሴ ወቅትም የተፈታኝ ተማሪ ቤተሰቦች በተለያዩ አግባቦች በእነዚህ የመከላከል ስራዎች ላይ ሲሳተፉ የነበሩ መሆኑና እነዚህ ጦርነትን እና የጸጥታ ችግሮችን የመከላከል ስራዎች በተፈታኝ ተማሪዎች ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ይህንን ጉዳይ በአግባቡ እና በጥሞና ሳይታይና ሳይፈተሸ በጥቅሉ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አወሳሰን ላይ የሚታይ ነገር የለም በሚል በይፋ በሚዲያ ውሳኔውን ማሳወቁ ከመልካም አስተዳደር መርሆች አኳያ ተገቢ የሆነ ውሳኔ አለመሆኑን ተቋሙ አረጋግጧል፡፡

ለ. በተቋሙ የተሰጠ የመፍትሄ ሀሳብ

1.ሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ የፈተና እርማትን አስመልክቶ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ከተፈታኝ ተማሪዎች እና ወላጆች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ተገቢውን ጊዜ ሰጥቶ ያለምንም ገደብ በአካል ፣ኦንላይን(online) የአቤቱታ ማቅረቢያ ጨምሮ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅሞ አቤቱታዎች በመቀበል ተገቢውን የሰው ሀይል በመመደብ ለቅሬታዎቹ ግልጽ እና ምክንያታዊ ምላሽ እንዲሰጥ፡፡

በተለይ በኦን ላይን(online) ለቀረቡ አቤቱታዎች እየተሰጡ ያሉ ምላሾች በአግባቡ የታዩ እና ማጣራት የተደረገባቸው ስለመሆናቸው ተገቢው ቁጥጥር እንዲደረግባቸው፤

2.በ2013 ዓ/ም የትምህርት ዘመን በሁለተኛ ዙር የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች የፈተና እርማት ሂደት ላይ ስህተቶች የተፈጠሩ መሆኑ ይታወቃል ስለዚህ በሁለተኛው ዙር እርማት ተጨማሪ ስህተት አለመኖሩን ድርጅቱ በሚያረጋግጥበት ስርአት (verification) አረጋግጦ ለአቤት ባዮች አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል፤

3.የትምህርት ሚንስቴር በጦርነት ወይም የጸጥታ ችግር በነበረባቸው አከባቢዎች የተመዘገበውን የተማሪዎች ዉጤት በአንጻራዊነት ሰላም በነበረባቸው አካባቢዎች ከተፈኑ ተማሪዎች ዉጤት ጋር ያለውን ልዩነት (Variation) ወይም ተቀራራቢነት በማየት እና በሚያገኘው ግኝት መሰረት የተማሪዎች ወደ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚያስገባው መቁረጫ ዉጤት ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ዳግም ማየት የሚችልበት ሁኔታ ቢኖር ምክንያቱም ተቋማት የሚሰጡት ምላሽ በተማሪዎች ህመም ውስጥ ሆነው መሆን ስላለበት፡፡

See also  ለ"እጅ እንስጥ" የስልክ ጥያቄ መከላከያ " ምርጫው የእናንተ ነው" አለ፤ ሽሬ ነዋሪዎችና መከላከያ እየተነታረኩ ነው

“ዛሬ በዴሞክራሲያዊ ባህሪ ያላስተናገድነውን ትውልድ ነገ መብትህን በሰላማዊ ወይም
በዴሞክራሲያዊ መንገድ ጠይቅ የማለት የሞራል ልዕልና አይኖረንም”

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መጋቢት 14/2014 ዓ.ም

Leave a Reply