“…በሌብነት የሚጠረጠሩ አመራሮች ከእንግዲህ ቦታ የላቸውም”

ሕዝብን የሚያማርሩና በተለይም በሌብነትና ብልሹ አሠራሮች እጃቸው አለባቸው ተብለው በግምገማ ከኃላፊነታቸው የተነሱ አመራሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊና የማዕከላዊ ኮሚት አባል የሆኑት አቶ አብራሃም ማርሻሎ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በከተማም ሆነ በገጠር እስከ ቀበሌ መዋቅር ድረስ ሕዝብን በሚያማርሩ ጉዳዮች ዙሪያ ሕዝቡም ሆነ የፓርቲው አባላት ውይይት አካሂደዋል፡፡

በዚህም ሕዝብ በተደጋጋሚ ያነሳቸው እንዲስተካከሉለት ከጠየቃቸው ጉዳዮች ውስጥ ሌብነት፣ ሥራ አጥነት፣ አድሎአዊ አሠራር፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አልቀው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ አለማድረግ፣ የአመራሩ የሥነ ምግባር ችግሮችና የመሳሰሉት ጉዳዮች መሆቸውን አንስተዋል፡፡

“ሕዝብን የሚያጉላሉና በሌብነት የሚጠረጠሩ አመራሮችን ከዚህ በኋላ በጉያችን ይዘን ለመቀጠል እድል አንሰጥም’’ ያሉት አቶ አብራሃም፤ “በተደረገው ግምገማ በሌብነትና ብልሹ አሠራች ተጠርጥረው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉ አመራሮች ጉዳያቸው ተጣርቶ በሕግ አግባብ ተጠያቂ ይደረጋሉ’’ ብለዋል፡፡

በፓርቲው አንደኛ ድርጅታዊ ጉባዔም በእነዚህ አቅጣጫዎች ላይ አጽንኦት ተሰጥቶ ውይይት የተደረገና አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን፤ እንደ ክልል በተደረገው ውይይትም እስከ 2 ሺህ የሚደርሱ አመራሮች ተገምግመዋል ነው ያሉት፡፡

በየደረጃው ባለው መዋቅር በተደረገው ግምገማም ከሙስና፣ ከሌብነት፣ ከጎሰኝነትና አካባቢያዊነት በጸዳ መልኩ ሕዝቡን ከማገልገል አኳያም ሥር የሰደዱ ችግሮች እንዳሉ የተለየ ሲሆን በነዚህ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቀው የተገኙ አመራሮችን በመለየት ፖለቲካዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል፡፡

በዚሁ መሰረትም ከተገመገሙት 2ሺህ በላይ አመራሮች ውስጥ 238ቱ በከባድና ቀላል ማስጠንቀቂያ የታለፉ ሲሆን፤ 146ቱ ደግሞ ከአመራርነት ፑል እንዲወጡና እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡

በሌብነት የተጠረጠሩ አመራሮች እንደ ከዚህ ቀደሙ ከቦታ ቦታ በማዘዋወር በሠላም እንዲኖሩና ሕዝብና አገርን የሚጎዱ ድርጊታቸውን እየደጋገሙ እንዲፈጽሙ እድል ካለመሰጠቱም በላይ መረጃቸውና ጉዳያቸው ተጣርቶ በሕግ አግባብ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር ተጀምሯልም ብለዋል አቶ አብራሃም፡፡

በቀጣይም በሕዝቡ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችና ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግም ተጨማሪ ማጣራት በማድረግ ብልሹ አሠራሮች ውስጥ የተገኙ አመራሮችን የማጥራቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል፡፡

እንደ አቶ አብራሃም ገለጻ፤ በተለይ በመንግሥት የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ በሚገኙት በገቢዎች፣ በንግድና ገበያ ልማት፣ በመሬት አቅርቦትና መሰል ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ውስጥ በሙስና፣ በሌብነትና በእጅ መንሻ የሚሰጡ አገልግሎቶች ሕዝቡን በእጅጉ ለምሬት የዳረጉ መሆኑንና ከኃላፊነት እንዲነሱ ከተደረጉት አመራሮችም አብዛኞቹ ከነዚሁ ተቋማት ነው፡፡

See also  "የምንሰራው የሚገባቸው ጠላቶቻችን ናቸው"አብይ አሕመድ፤ የሩሲያ ባህር ኃይል ልዑክ የኢትዮጵያ የባህር ሃይልን ጎበኘ

እነዚህን ከሌብነትና ሙስና ጋር በተያያዘ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉ አመራሮችን ጉዳይ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ ከፖሊስና ሥነ ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን አጣሪ ቡድን በማዋቀር በተቋም ደረጃ ከስረ መሰረቱ ለማጣራትና ለሌሎችም ትምህርት በሚሆንበት አግባብ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ይደረጋልም ብለዋል፡፡

በቀጣይነትም በየደረጃው የሕዝብ መድረኮችን በማዘጋጀትና ሕዝቡን በማወያየት በፓርቲው ጉባዔ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች በአግባቡ ተፈጻሚ ለማድረግና በሕዝቡ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችንም በማሰባሰብ ለሕዝቡ ተስፋ በሚሰጥ መንገድ ብልሹ አሠራሮችን ለመቅረፍ እንደሚሠራም አክለው ገልጸዋል፡፡

አምሳሉ ፈለቀ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply