የኦነግ ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ውሳኔ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክቶ ውሳኔ ሰጥቷል።

ቦርዱ ፓርቲውን አሰመልክቶ የተሰጠው ውሳኔው እንደሚከተለው ቀርቧል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ውሳኔ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራር መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ ከፓርቲው አመራሮች ሲቀርቡለት የነበሩትን ክርክሮች በመመርመር ውሣኔ መስጠቱ ይታወሳል።

በውሳኔው ቅር በመሰኘት የእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ ቡድን ያቀረቡትን ይግባኝ መነሻ አድርጎ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦርዱ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም የተጠራውን ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት የለውም ሲል የሰጠውን ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ ሽሮታል፡፡ ከዚህ በሁዋላም ቦርዱ ቅሬታውን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ይግባኙ አያስቀርብም በማለት በአብላጫ ድምጽ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ በመጨረሻም ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ በነሃሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ሊጣሩ የሚገቧቸውን የሚከተሉትን ጭብጦች በመለየት እነ አቶ አራርሶ ቢቂላ እና እነ አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚያቀርቡትን ክርክርና ማስረጃ በመስማት አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 343/1/ መሰረት ጉዳዩን ለቦርዱ መልሶታል፡፡

ጭብጦቹም፤

  1. በህጉ እና በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በተቀመጠው አግባብ እንዲመራ የህግ የበላይነት ሰፍኖ የአባላቱ የመደራጀት መሰረታዊ መብታቸው ተከብሮ ተገቢውን ውክልና አግኝተው በተሳተፉበት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መተላለፍ/አለመተላለፉ፤
  2. ጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ያስተላለፈው በደንቡ ስለውሳኔ አሰጣጥ የተደነገገውን በሚያሟላ መልኩ መሆን/አለመሆኑን፤
  3. ደንቡን ያልተከተለ ከሆነ ምክንያቱ ተለይቶ የጠቅላላ ጉባኤ ህጋዊ ውሳኔ ውጤት ፓርቲው ካለበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የቦርዱ ሃላፊነት እስከምን ድረስ እንደሆነ ከፓርቲው የወደፊት እጣ ፋንታ ጋር ተገናዝቦ እና
  4. የጉባኤውን ውሳኔ አስመልክቶ ተጠሪ ለአመልካች ያቀረበው ሰነድ የተሟላ መሆን/አለመሆኑ፤ በጭብጥነት ተይዞ ከህጉ እና ከመተዳደሪያ ደንቡ አንጻር ተጣርቶ እንዲወሰን ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 343/1/ መሰረት መልሶታል፡፡

አቶ አራርሶ ቢቂላ የተጠራውን ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የመጨረሻውን ውሳኔ ነሃሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰጠ በኋላ በመስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት በውሳኔው ላይ በግልጽ ካመላከታቸው ነጥቦች ውጪ በጭብጥነት የሚያዙ ነጥቦች ካሉ በሚል ቦርዱ በጭብጥ አያያዝ ዙሪያ ፍርድ ቤቱን ማብራሪያ ጠይቋል፡፡ በጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ሰበር ሰሚ ችሎቱ በተጠየቀው ማብራሪያ ላይ ጭብጦቹ የፍርድ ሀተታው ላይ ስለተገለጹ ተጨማሪ ጭብጥ ይገለጽልን የተባለውን ጥያቄ ሳይቀበለው መቅረቱን አሳውቋል።

በመቀጠል ኅዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ቦርዱ በድጋሚ ጉዳዩን አይቶ እንዲወስን ፍ/ቤቱ በወሰነው መሰረት ለእነ አቶ ዳውድ ኢብሣ እና ለእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ በፍርድ ቤቱ የተያዙትን ጭብጦች አውቀው ሁለቱም ወገኖች ክርክራቸውን እና ማስረጃቸውን ጥያቄው በደብዳቤ ከደረሳቸው ጀምሮ ባሉት 3 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ለቦርዱ እንዲያቀርቡ ተገልፆላቸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት አቶ ዳውድ ኢብሳ በፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ውስጥ ስላልተካተቱ የክርክሩን ሂደት የሚያሳይ በድምሩ 82 ገጽ ሰነድ በህዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ ከቦርዱ በደረሳቸው ደብዳቤ መሰረትም አቶ ዳውድ ኢብሳ እኤአ ታህሳስ 19/2014 (በዲሴምበር 28/2022) የተጻፈ 07 ገጽ አስተያየት እና 22 ገጽ የሰነድ ማስረጃ ሲያቀርቡ በእነ አራርሶ ቢቂላ በኩል ደግሞ በታህሳስ 18 ቀን 2014 ዓ.ም የተጻፈ 06 ገጽ የጽሁፍ ክርክር አቅርበዋል፡፡

ቦርዱም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከተቀበለ በኃላ ጉዳዩ ሶስት አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን በመሰየም የግራ ቀኙ ክርክር አጠቃላይ ሂደት ተመርምሮ የውሳኔ ሃሳብ እንዲቀርብለት በጥር 3 ቀን 2014 ዓ.ም ወስኖ ቡድኑ ስራውን ጀመረ፡፡ በጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም የባለሙያ ቡድኑ ጉዳዩን በአግባቡ መርምሮ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ከያዘው እና ቦርዱ ለይቶ ለግራ ቀኙ ወገኖች ካሳወቃቸው ጭብጦች አንጻር እንዲሁም የግራ ቀኙን የመሰማት መብት በመጠበቅ ለጉዳዩ አግባብነት አላቸው ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎች እንዲቀርቡ ለግራ ቀኙ አሳወቀ፡፡

አቶ ዳውድ ኢብሳ እኤአ በጥር 15 2014 (ጃንዋሪ 23 ቀን 2022) እና አቶ አራርሶ ቢቂላ በጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጪ አለመግባባት የሚታይበት የውስጠ ደንብ ወይም የስነ-ስርዓት መመሪያ የሚመለከት እንደሌለ እና ሌሎች ምላሾችን በደብዳቤ ለቦርዱ ገለጹ፡፡ በየካቲት 01 ቀን 2014 ዓ.ም የባለሙያዎች ቡድኑም የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃዎች ከፈዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ጋር በማገናዘብ መርምሮ የውሳኔ ሃሳቡን ለቦርዱ አቀረበ፡፡

በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የተጠራውን ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተ ቦርዱ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም የሰጠውን ውሳኔ የባለሙያዎቹ ቡድን በድጋሜ ምርምሯል። በዚህም ምርመራ ጠቅላላ ጉባኤው በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ስልጣን ባለው አካል ህጋዊ ሂደቱን ተከትሎ አለመጠራቱን በድጋሚ አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም መጋቢት 04 ቀን 2013 ዓ.ም የተጠራው ጉባኤ ህጋዊ አካሄዱን ተከትሎ ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት ስልጣን ባለው አካል አልተጠራም በማለት ቦርዱ ቀደም ሲል የሰጠውን ውሳኔ አፅንቷል።

በሌላ በኩል ሰበር ሰሚ ችሎት ቦርዱ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ሊጫወት የሚችለውን ሚና እንደገና እንዲያየው በገለጸው መሰረት ጉዳዩን ለመፍታት የባለሙያዎቹ ቡድን ሁለት አማራጮችን የያዘ የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

አማራጭ አንድ ፓርቲው በአመራሩ መካካል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት፣ በአዋጅ ቁጥር 162/201 አንቀፅ 74/1/ሸ/ እና በመመሪያ ቁጥር 3/2012 አንቀፅ 154 ጠቅላላ ጉባኤ በሶስት አመት አንድ ጊዜ የሚጠራበት ወቅት ላይ በመሆኑና ቦርዱ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ አካሂደው መተዳደሪያ ደንባቸውን አሻሽለው እንዲቀርቡ መመሪያ ከተሰጣቸው ፓርቲዎች መካከል አንዱ በመሆኑ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ ይኖርበታል የሚል ሲሆን በተጨማሪም በሚጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ አባላት መስፈርት ትክክለኛ ሂደቱን ተከትሎ ቦርዱ የሚያስቀምጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልው ሊከናወን እንደሚገባ እና
ቅድመ ሁኔታዎቹ በፓርቲው ሳይሟሉ መቅረት ሊያስከትል የሚችለው የህግ ውጤት ለፓርቲው እንዲገለፅለት የሚል ነው።

ሁለተኛው አማራጭ ቦርዱ የፓርቲውን ውሳኔ የማስተላለፍ መብት ሳይነካ የፓርቲውን የውስጥ ህግ በመከተል ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ ከመስጠት አንጻር ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት ስልጣን ያለው የብሔራዊ ምክር ቤቱን 48 አባላት በአድራሻቸው ተፈልገው ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራበትን ሁኔታ ማመቻቸት የሚል ነው፡፡

ቦርዱም በውሳኔ ሀሳቡ የተገለጸውን ሁለተኛ አማራጭ መነሻ በማድረግ ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራበትን አማራጭ ከማየት አንጻር፣ ሁለቱም ወገኖች በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 19.5 መሠረት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ከሆኑት ውጭ እና የውጭ አገር ዜግነት ካላቸው ውጭ ያሉትን ማለትም የ38 ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር ከነሙሉ አድራሻቸው እንዲያቀርቡ ቦርዱ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡

በዚሁም መሰረት መጋቢት 09 ቀን 2014 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ እነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሰባት ግለሰቦች ዝርዝር አድራሻ ሲያቀርቡ መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ አቶ ዳውድ ኢብሳ ፓርቲው ካሉበት የተለያዩ ችግሮች አንጻር የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር ማቅረብ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ቦርዱ በባለሙያዎች ቡድን በቀረበው ሁለተኛ አማራጭ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት ስልጣን ያለው የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት በአድራሻቸው የስብሰባ ጥሪ እንዲደርሳቸው በማድረግ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ለማስቻል የቀረበው አማራጭ ሀሳብ በቦርዱ ሊፈጸም የማይችል ሆኖ በመገኘቱ በባለሞያ ቡድኑ የቀረበውን ሌላኛውን አማራጭ ወስዷል።

በዚህም መሰረት ቦርዱ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት እንደሚገባው ገልጾ ፓርቲው እስካሁን ካለበት የአመራር ችግር አንጻር፣ ጉባኤ ከመደረጉ በፊት የጉባኤው አጠራር ደንብ እና የምርጫ ህጉን የተከተለ መሆኑን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፣ የጉባኤ አጠራር ዝርዝር ዕቅድ፣ የጉባኤውን አጠራር በተመለከተ በተገቢው የፓርቲው አካል የተሰጠ ውሳኔ እና የውሳኔው ቃለጉባኤዎች ቦርዱ ይህን ውሳኔ ባሳወቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማለትም እስከ ሚያዚያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲቀርብ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply