ተሳፋሪ ሽጉጥ በመደቀን የሞባይል ስልኮች የወሰደውና ይህንኑ ስልክ የገዛው ተከሳሽ በእስራት ተቀጡ

የራይድ አገልግሎት እየሰጠ ካለ ሾፌር እና ተሳፋሪ ሽጉጥ በመደቀን የሞባይል ስልኮች የወሰደው ተከሳሽ እና ይህንኑ ስልክ የገዛው ተከሳሽ በውንብድና እና በመሸሸግ ወንጀል በእስራት ተቀጡ

ተከሳሽ አስማረ ገብሬ የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ሁለት ክሶች የቀረቡበት ሲሆን መስከረም 18 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡15 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክ/ከ/ወረዳ 15 ልዩ ቦታው 72 ካሬ አሜንስ ኮንስትራክሽን መታጠቢያ አካባቢ ተከሳሽ ካልተያዘ አባሪው ጋር በመሆን መንገድ ላይ ጠብቀው መኪናውን ካስቆሙ በኋላ ተከሳሽ የግል ተበዳይ እና የራይድ አገልግሎት እየሰጠ በነበረው ሱራፌል ታደሰ ላይ ሽጉጥ በመደቀን በኪሱ ውስጥ ይዞት የነበረውን 350 ብር እና ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ10+ ስልክ የዋጋ ግምቱ 30,000 ብር የሆነ እንዲሁም በ2ኛ ክስ በራይድ ተሳፋሪ የነበረውን የግል ተበዳይ ተስፋነህ መኮንን ብር አምጡ ብለዋቸው ብር የለኝም በማለት መልስ ሲሰጧቸው ተከሳሽ ያልተያዘው አባሪውን ሞባይሉን ተቀበለው በማለት አይፎን ኤስ6 ሞባይል የዋጋ ግምቱ 5,000 ብር የሚያወጣ ንብረት የወሰደ በመሆኑ የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 671/1/ለ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በፈፀመው ከባድ የውንብድና ወንጀል ዓቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበታል፡፡

በ2ኛ ተከሳሽ መኳንንት አለበል እቃው የተገኘው በአንድ ንብረት ላይ በተፈፀመ ወንጀል መሆኑን እያወቀ የግል ተበዳይ ሱራፌል ታደሰ ንብረት የሆነውን ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ 10+ የዋጋ ግምቱ 30,000 ብር የሚያወጣውን እና ዝርዝሩ ከላይ የተገለጸው ሁኔታ የተወሰደውን ሞባይል በቀን 23/1/2013 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክ/ከ/ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ሰሚት 30 ሜትር ከሚባለው አካባቢ ላይ ከ1ኛ ተከሳሽ ላይ ገዝቼው ነው በሚል እራሱ ይዞት እየተጠቀመበት የተገኘ በመሆኑ በፈፀመው መሸሸግ ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡

ተከሳሶች በችሎት ቀርበው የእምነት ክደት ቃላቸውን ሲሰጡ ክሱን አንቃወምም ነገር ግን ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሰረት ዐቃቢ ህግ የተለያዩ የሰው፣ የሰነድ እና የኤግዚቢት ማስረጃዎችን በማቅረብ ክሱን አስረድቷል፡፡ ሰለሆነም ችሎቱ ይህን ካየ እና ከመረመረ በኋላ ተከሳሾችን የመከላከል መብት ተጠብቆ ተከሳሾች የዓቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ እና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መጋቢት 14/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾችን ያርማል መሰል አጥፊዎችን ያስተምራል በማለት 1ኛ ተከሳሽ በሁለቱም ክሶች አራት የቅጣት ማቅለያ ተይዞለት በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ሁለት የቅጣት ማቅለያ ተይዞለት በፈጸመው የመሸሸግ ወንጀል በ 6 ወር ቀላል እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

ማስታወሻ፡- በወንጀል ድርጊት የተገኘን ንብረት ከመሸጫ ስፍራው ውጭ መግዛት ነፃነትን የሚያሳጣ የእስራ ቅጣት የሚያስከትል በመሆኑ ተዘርፈው እና ተሰርቀው በየመንገዱ የሚሸጡ የሞባይል ቀፎዎችን ባለመግዛት ወንጀልን እናዉግዝ መልዕክታችን ነው፡፡
ምስል ከ ጎግል

ministry of justice

You may also like...

Leave a Reply