የተካደው ሰሜን ዕዝ (የታፋኙ ወጥቶ አደር ማስታወሻ)

የተካደው ሰሜን ዕዝ የካሐዲዎቹን ዝግጅት ያስቃኘናል፡፡ ካሐዲዎቹ፡- ሁለት ዓመታት ተኩል 84000 ልዩ ሃይል አሠለጥነው፣ 52 ብርጌድ ሚኒሻ አደራጅተው፣ ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ በሕዝባቸው ዘንድ ሠርተው፣ በክልሉ ውስጥ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ፣ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ በውስጥም በየአምባውና ሸንተረሩ ምሽግ ቆፍረውና ገንብተው እስኪጨርሱ ድረስ የነበረውን ሂደት ያስቃኘናል፡፡ በዕዙ ውስጥ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሠራዊቱ አመራሮች ምን እያደረጉ እንደነበር ይተርክልናል፡፡


ክፍል ፩ by – Samson Michilovich

ደራሲ፡- ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ጤናው (ቻቻው)

(የመጽሐፍ ግብዣ) – ስለመጽሐፉ

በዚህ ዓመት በወርሃ መጋቢት ነው የታተመው፡፡ በዓስር ምዕራፎች ተከፋፍሏል፡፡ ዘለግ ያለ ነው-400 ገጾችን ሊደፍን ትንሽ ነው የቀረው፡፡ ትሕነግ ከነጓዙና ግሳንግስ ደጋፊው ጋር ሆኖ የሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ክሀደት ይተርካል፡፡ መጽሐፉ የሚሸፍነው ጊዜ በዋናነት አንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት (ከጥቅምት 24 እስከ ታሕሳስ 9/2013) ይሁን እንጂ፣ በምልሰት እየሳበ ረዘም ያለ ጊዜን ሸፍኗል፡፡ ፀሐፊው፣ በሰሜን ዕዝ ሥር፣አዲግራት ነበረው የ20ኛው ክፍለ ጦር አባል ስለነበረ ከጥቅምት 24 አስቀድሞ የነበረውን ድባብና የካሐዲዎቹን ዝግጅት፣ በዕለቱ የተፈጸመውን፣ ከጥቅምት 24 በኋላም የኾነውን ያየውን፣የሰማውን የተረዳውን ታሪክ ይተርክልናል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከሦስት መቶ የሚበልጡ ሰዎችንም ቃለ መጠይቅ ማድረጉን በመጽሐፉ አስታውቆናል፡፡

ስለፀሐፊው

ከመጽሑፉ እንደምናገኘው፣ፀሐፊው ወታደር ነው፤የሃምሳ አለቃነት ማዕረግ አለው፡፡ መከላከያ ሠራዊቱን ከመቀላቀሉ በፊት ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪውን ይዟል፡፡ ወታደር ቤት ከገባ በኋላም በወታደራዊ መሳሪያ ጥገና በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ ደራሲም ነው፤ “ኢትዮጵያ ትሙት” የሚል ልብወለድ እና “ውሸታም” የሚል የግጥም መጽሐፍትን አሳትሟል፡፡ (የልብወለዱንም ሆነ የግጥሙን ሥራዎች እንዳሉት ያወቅኩት በተካደው ሰሜን ዕዝ ውስጥ በመገለጻቸው ነው፡፡

የደራሲው የትምሕርት ዝግጅትና በሠራዊቱ ውስጥ የነበረው ቆይታና ልምድ፣ የሥነጽሑፍ ዝንባሌውና ችሎታው፣ እንዲሁም ለንባብ ያለው ፍቅር (ለመጽሐፎቹ ያለው ክብርና ፍቅር አስገራሚ መሆኑን ከመጽሐፉ ይታዘቧል) ለመጽሐፉ ይዘትና ኪናዊ ውበት አስተወጽኦዋቸው የጎላ መሆኑን መጽሐፉ ራሱ ይመሰክራል፡፡

ከይዘቱ በጥቂቱ

የተካደው ሰሜን ዕዝ የካሐዲዎቹን ዝግጅት ያስቃኘናል፡፡ ካሐዲዎቹ፡- ሁለት ዓመታት ተኩል 84000 ልዩ ሃይል አሠለጥነው፣ 52 ብርጌድ ሚኒሻ አደራጅተው፣ ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ በሕዝባቸው ዘንድ ሠርተው፣ በክልሉ ውስጥ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ፣ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ በውስጥም በየአምባውና ሸንተረሩ ምሽግ ቆፍረውና ገንብተው እስኪጨርሱ ድረስ የነበረውን ሂደት ያስቃኘናል፡፡ በዕዙ ውስጥ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሠራዊቱ አመራሮች ምን እያደረጉ እንደነበር ይተርክልናል፡፡ የመካላከያ ሠራዊቱን የሪፎርም ሂደት ያስከፈለውን ዋጋ ይነግረናል፡፡ (ከልዩ ኃይሉ ባለፈ 52 ብርጌድ ሚኒሻ የተደራጀውና የተመራው በእነዚህ አይደል?) የሰሜን ዕዝን የጦር መሣሪያዎች፣ ተሸከርካሪዎች፣ ተተኳሽና ዴፖዎች ለመዝረፍና ለመውሰድ የተጠቀሙበትን አካሔድ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡

የሰሜን ዕዝን ማጥቃት ማለት ሊያስከትል የሚችለውን የከሐዲዎቹን ስሌት መጽሐፉ ያሳየናል፤ አንባቢም ብዙ ነገር እንዲያውጠነጥን፣ እንዲገነዘብ ያደርጋል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት 18 ክፍለ ጦሮች (12 እግረኛ፣6 መካናይዝድ) ብቻ ነው፡፡ በአራት ዕዝ ነው የተዋቀረው፡፡ ሰሜን፣ደቡብ፣ምሥራቅና ምዕራብ ዕዞች፡፡ የሰሜን ዕዝ 9 ክፍለ ጦሮች አሉት-ከጠቅላላው ግማሹ፡፡ ከ6ቱ መካናይዝድ ክፍለ ጦሮች 4ቱ የሚገኙት በሰሜን ዕዝ ሥር ነው፡፡ (ገጽ- 113)

አብዝሃኛው ሚሳኤል ያለውም ትግራይ ውስጥ ነው፡፡ በፀሀፊው ስሌት መሠረት ሦስቱ ዕዞች የነበራቸው ሠራዊት እግረኛም መከናይዝድም ተደምሮ 32 ሺ ገደማ ነው፡፡ ከስድስቱ አራቱ መካናይዝድ ክፍለ ጦሮች፣ ሠራዊቱን ደምስሶ መሣሪያዎቹን መረከብ የሚያስከትለውን የኃይል መበላለጥ ልብ ይሏል፡፡ ከሁሉም የከፋው ደግሞ ከጥቅምት 24 ሌሊት ጀምሮ ጦርነቱ ሕዝባዊ መሆኑ ነው፡፡ ከልዩ ኃይሉ፣ ሚኒሻው ክፋትና ጭካኔ፣ ከሚኒሻው ይልቅ የሕዝቡን ጭካኔ (ለምሳሌ ገብረ ሰናይ፣እዳጋ ሐሙስ፣ እንትጮ…. የሆነው) ይዘረዝራል፡፡ ግጥሚያው እንዲህ ነበር እያለን ነው መጽሐፉ፡፡ (ለምሳሌ ገጽ 73፣ 94፣ 100፣154 ፣169….)

የማያልቅ በደል፣ የክፋት ጥግ፣ እኩይነት፣ ክህደት ይዘረዝራል፡፡ ሚስት ባሏን፣ልጅ አባቷን በከሃዲዎቹ የማስያዝ ክህደት (ገጽ 79-80)፣ ጡት ቆርጦ ዛፍ ላይ ማንጠልጠል (ገጽ 154) ፣ አንዲትን ሴት ወታደር በአንድ ጊዜ ለሦስት አስገድዶ መድፈር…. ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል? በእንዲህ ዓይነቱ የዕኩይት ዐውድና ድባብ ውስጥ ሆነውም ከኅሊናቸው፣ከሰብአዊነታቸው ዝንፍ ያላሉ የትግራይ ተወላጆችንን (ከሠራዊቱም ከሕዝቡም) መኖራቸውንም “የተካደው ሰሜን ዕዝ” ሳይክድ ሐቁን ይዘክራል፡፡

ጥቅምት 24 ሌሊት ጀምሮ የሰሜን ዕዝ ያደረገው ተዓምራዊ ተጋድሎ፣ ጀግንነት፣ የከፈለው መስዋዕትነት ከዓይነ ኅሊናችን እንዳይጠፋ አድርጎ አቅርቦልናል፡፡ ወደ ኤርትራ ለመውጣት የተደረገው ተጋድሎ፣ ተተኳሽና ከባድ መሣሪያ የማውደም፣ የሚሳኤል ኮድ ላለመስጠት የተከፈለ መስዋዕትነት፣ ለብዙ ቀናት ያለምግብና ውሃ መዋጋት…. ገድሎቹ ብዙ ናቸው፡፡ ገድለኞቹም እንዲሁ!

“የተካደው ሰሜን ዕዝ” መነበብ ያለበት መጽሐፍ ነው፡፡ አንድም ታሪክ ነው፡፡ አንድም የሕዝብና የመከላከያ ሠራዊቱን ግንኙነት ምን መመሰል እንዳለበት ይጠቁመናል፡፡ ወዲያም ሕዝብ ለሕዝብ የሚኖረንን ግንኙነት ማጤን እና ማስተካከል እንዳለብን ሳንወድ በግድ ያስገነዝበናል፡፡ በተለይ ደግሞ ማንኛውም የሠራዊቱ አባል ሊያነበው ይገባል፤ ከታሪክነቱ ይልቅ የሠራዊቱ የአሠፋፈር፣ የመሣሪያ አያያዝ፣ የዋርዲያ አመዳደብ፣ የአመራር ስብጥር…. ከጠላት አንጻር ምን ሊሆን እንደሚገባ ማወቅ፣መጠንቀቅና መዘጋጀት አስፈላጊ ነውና! ሁልጊዜም ክፉ ቀን ቢመጣስ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል! ሌላውም ሰው ሊያነበው የሚገባ መጽሐፍ ነው፡፡
…..
የደራሲው ሞባይል አገራዊ ቅርስ ናት- ሞባይሉን ከገዳዮች አዟዊ መንጋጋ ደብቆ፣ ይኽን መጽሐፍ በእሷው ጽፎ አድርሶናል፡፡

ሌሎች የሠራዊቱ አባላትም በተለያዩ ግንባሮች ወይም ክፍለ ጦሮች ዘንድ የነበረውንና የሆነውን ያጋሩናል የሚል ተስፋ አለኝ፤የሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ጤናው መጽሐፍም በዚህ ረገድ አነሳሺም ፈር ቀዳጅም ነው፡፡

Leave a Reply