የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች የተጨፈጨፉባቸው በርካታ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናት አጋለጠ

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች ላይ የዘር ፍጅት የፈጸመበት “ሀለዋ ወያነ” በመባል የሚታወቁ የጅምላ እስር እና የጅምላ ቀብር የሚፈጸምባቸው ቦታዎችን ማግኘቱን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን አጋልጧል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን “ገሃነም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ በርካታ የሽብር ቡድኑ የጉድጓድና የዋሻ ድብቅ እስር ቤቶች ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ ከተጠቆሙት የጅምላ መቃብሮች መካከል ለሙከራ አምስቱን አስቆፍሮ ጭካኔ በተሞላበት ግፍ የተረሸኑ ንጹሃንን አፅም አስወጥቷል።

አካባቢውን የጀርመኑ ናዚ እስራኤላውያንን ከጨፈጨፈበት “ኦሽዊዝ” የተባለ ማጎሪያ ጋር አነጻጽረው “የኢትዮጵያዊው ኦሽዊዝ” ሲሉ የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን አባላት “ገሃነም” በተባለው የሽብር ቡድኑ የድብቅ እስር ቤት በርካታ ሺህ ንጹሃን ማለቃቸውን በወቅቱ በእስር ላይ የነበሩና ከሞት የተረፉ የወራሪ ቡድኑ የጥቃት ሰለባዎችን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን ይህን ድብቅ እስር ቤት የመረጠበት ምክንያት አካባቢው ሰው ከሚኖርበት ርቆ የሚገኝ ዙሪያው በከፍተኛ ሰንሰለታማ ተራራ የተከበበ ከመሆኑም ባሻገር በኀይል ይዟቸው የነበሩትን የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎች አማካኝ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከሁሉም አካባቢዎች ንጹሃንን እያፈነ ወስዶ ለማጎርና ለመጨፍጨፍ ምቹ በመሆኑ ነው ተብሏል።

በዚህ አሰቃቂ እስር ቤት የታሰሩ ንጹሃን በሚደርስባቸው ሰቆቃ ምክንያት ራሳቸውን ማጥፋታቸውን፣ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በየቀኑ ታሳሪዎችን እየወሰዱ ይገድሉ እንደነበርና የብዙዎቹ አስከሬን በአካባቢው የሚገኝ ቃሌማ ወንዝ ላይ ይጣል እንደነበር ከሞት የተረፉት አዛውንቶች ለጥናት ቡድኑ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የድብቅ እስር ቤቱ ውስጥ በበሽታና በርሃብ፣ በድብደባ ተሰቃይተው እንዲሁም በአሸባሪው የትግራይ ቡድን ታጣቂዎች ለሚገደሉት እስረኞች ቀብር ይቆፍሩ የነበሩት እስረኞች እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል።

ባለቤቷ “ከፋኝ” የተባለ በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ህዝብና መሬት ላይ የተቃጣውን ወረራ ለመቀልበስ የተቋቋመ ታጣቂ ኀይልን ተቀላቅሎ የሽብር ቡድኑን በመታገሉ የታሰረችው የወልቃይት አማራ እናት ለጥናት ቡድኑ እንዳስረዳችው እስር ቤቱ እጅግ አሰቃቂ ከመሆኑ ባሻገር የትህነግ ታጣቂዎች ይፈፅሙት የነበረው ወንጀል አስከፊ እንደነበር ገልፃለች።
“በላይ ድንጋይ የተረበረበበት ጉድጓድ ዉስጥ ነበር የሚያስሩን፡፡” የምትለው የአይን እሟኛ በአንድ ጉድጓድ ቢያንስ 10 ሰዎች ይታሰሩ እንደነበር ትናገራለች። “ገሃነም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በርካታ ጉድጓዶች እና ዋሻዎችም የንጹሃን ማሰሪያ የነበሩ ሲሆን ምግብና ውሃ በ24 ስዓት አንዴ ብቻ ይቀርብ እንደነበር እማኞቹ አስረድተዋል።

የጥናቱ እማኝ ሆና የቀረበችው ሌላ እስረኛም “ሁሌም ማታ ማታ ከመካከላችን ስም ይጠሩና ይዘዋቸዉ ይወጣሉ፣ ከዚያ በኋላ በግምት ግማሽ ሰዓት ገደማ ይቆዩና ብዙ ጥይት ይተኮሳል፡፡ ከእኛ ራቅ አድርገዉ ነዉ የሚረሽኗቸዉ፡፡ በቃ ሁሌም እንደ መልአከ ሞት ማታ ይጠሩሃል፣ ትሄዳለህ ጥይት ይተኮሳል ከወጣህ መመለስ የለም፡፡ በተገደሉት እስረኞች ምትክ አዲስ እስረኛ ይመጣል፡፡” ስትል በ”ገሃነም” እስር ቤት የነበረውን ሁኔታ ትገልጸዋለች።

አሸባሪው የትግራይ ቡድን ወልቃይት ጠገዴን ከያዘ በኋላ ለቡድኑ እገዛ ሲያደርግ የነበረና በአካባቢው የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ቆይቶ መረዳቱን የገለጸው የአካባቢው ተወላጅ ወንጀሉ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ይፈጸም እንደነበር ለጥናት ቡድኑ አስረድቷል።

“ከፋኝ” በሚል ለወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ማንነት ሲታገል የነበረውን ቡድን አመራሮች፣ አባላትና የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላትም በአካባቢው ታስረው በነበረበት ወቅት አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ከፍተኛ የሽብር ቡድኑ አመራሮች ትዕዛዝ ይሰጡ እንደነበር ለጥናት ቡድኑ እማኝነቱን ሰጥቷል።

የአካባቢው ተወላጅ በመሆኑ ወደ ድብቅ እስር ቤቶቹ እንደማያስጠጉት የገለጸው ግለሰብ አቶ ስብሃት በራዲዮ መገናኛ ስንት ሰው እንዳለ ጠይቆ ከ59 ሺህ በላይ ታሳሪ መኖሩን እንደተገለጸለትና አቶ ስብሃት ነጋም “ሬሽን የለንም፣ መረጃ ተቀብላችሁ ቶሎ ቶሎ አስወግዷቸው” ማለቱን እንደሚያስታውስ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ተናግሯል።

በወቅቱ የሽብር ቡድኑን ይደግፍ የነበረ ሌላኛው ግለሰብ ሀምሌ 7 ቀን 1982 ዓ.ም. በአካባቢው የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ለአብነት በመጥቀስ ለጥናት ቡድኑ እንደሚከተለው አስረድቷል።

“በቅርብ ርቀት በርካታ ጊዜ አውቶማቲክ ጥይት ተተኮሰ፡፡ ጨለማ ስለነበር ለማጣራት ጠጋ ብየ ቁጭ አልኩ፡፡ ባሩድ ይሸታል፣ የሚያወሩት ትግርኛ ነው፡፡ ትህነጎች መሆናቸውን አረጋገጥኩ፡፡ መጀመሪያ የእርስ በርስ ጠብ መስሎኝ ነበር፡፡ ቀስ ብዬ ስጠጋ የተወሰኑት መሳሪያ ይዘው ቆመው ይታያሉ። ሌሎች ጉድጓድ አፈር ይሞላሉ፣ ፈርስና ባሩድ በጣም ይሸታል፡፡ በመጨረሻ ጉድጓዱን ከመሬቱ ጋር አስተካክለው በአፈር ጠቀጠቁት፡፡ ድንጋይ ስር ቁጭ ብዬ በጨለማ ጆሮየን ተክዬ የተወሰነውን አዳምጣለሁ። በትግርኛ ቋንቋ ‘አስማማው በለጠ 36 ራሱን ተሸኘ’ ሲል ሰማሁት፡፡ አስማማው ደግሞ በጣም ታዋቂ ጀግና እንደነበርና እንደወሰዱት አውቃለሁ፡፡”

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ለረዥም ጊዜ መረጃ ከሰበሰበ በኋላ ገሃነም በተባለ አካባቢ በሚገኙ በርካታ እስር ቤቶች ጭፍጨፋ ከተፈጸመባቸው መካከል የተወሰኑት ሃይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሟች ቤተሰቦችና የአካባቢው ፀጥታ ኃላፊዎች በተገኙበት አፅማቸው እንዲወጣ ተደርጓል።

የጅምላ መቃብሮች በመቆፈር የወጣው የንጹሃን አፅም መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. አዲስ ዓለም ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተቀበረ ሲኾን በአካባቢው ካሉት በርካታ ድብቅ እስር ቤቶችና የጅምላ መቃብሮች በቀጣይ የበርካታ ንጹሃን አፅምን ለማውጣት እቅድ መያዙም ተገልጿል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን “ገሃነም” በተሰኘው አካባቢ በነበሩት ድብቅ እስር ቤቶች የተፈፀመውን ጨምሮ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ላይ የተፈፀመውን የዘር ፍጅት ወንጀል የሚያሳይ መረጃ አሰናድቶ ለማቅረብ በመሥራት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
መረጃው የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ነው።

ሑመራ: መጋቢት 25/2014 ዓ.ም. (አሚኮ)

Leave a Reply