የሚኒስትሮች ግብረኃይል በአፋርና በአማራ ክልል ለተሰማራው የምርመራ ቡድን የተጠናከረ ድጋፍ እያደረገ ነው

የሚኒስትሮች ግብረኃይል ጽ/ቤት በአፋር እና በአማራ ክልል ለተሰማራው የምርመራ ቡድን የተጠናከረ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ

በሚኒስትሮች ግብረኃይል ጽ/ቤት ስር ከተቋቋሙ 4 ኮሚቴዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የወንጀል ምርመራ እና ማስቀጣት ኮሚቴ በአፋር እና በአማራ ክልል ለተሰማራው የምርመራ ቡድን የተጠናከረ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የጽ/ቤቱ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ካሳ ገለጹ፡፡ ቡድኑን ለማጠናከር እየተሰሩ ካሉ ስራዎች ጋር በተያያዘ ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር ታደሰ በሚኒስትሮች ግብረኃይል ጽ/ቤት ስር ከተቋቋሙት 4 ኮሚቴዎች ውስጥ የምርመራና ማስቀጣት ኮሚቴ አንዱ መሆኑን አስታውሰው የምርመራ ሂደቱንም በበላይነት እየመራ ይገኛል ብለዋል፤ እንደመንግስት የምንወስናቸው ስራዎች ወይም ኃላፊነቶች በጣም ሰፊ ናቸው ያሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አንዱም ከምርመራ ጋር የተያያዙ ስራዎችን ማከናዎንና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡

ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ጋር በተያያዘ የጋራ ጥምር የምርመራ ሪፖርቱ እንዲሟሉ ያስቀመጣቸው ስታንዳርዶች አሉ ያሉት ዶ/ር ታደሰ በዋናነትም ምርመራው ገለልተኛ እና ከአድሎ የጸዳ እንዲሆን ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በተግባርም ገለልተኛነት ባላቸው ሰዎች በኩል እንዲከናወን ይጠበቃል፤ ለዚህም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር የዝግጅት ስራዎችን ስናከናውን ቆይተን ወደስራ ገብተናል ሲሉም አክለዋል፡፡

በአለማቀፍ ደረጃ በዚህ አይነት ሁኔታ የሚካሄዱ ሁሉም ምርመራዎች የሚያሟሏቸው ስታንዳርዶች እና የአለማቀፍ ስታንደርዶችን ያሟሉ የምርመራ ሂደቶችስ ሁነቶችንና ሁኔታዎችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል? የሚለውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማጤን ለምርመራ ቡድኑ ከየካቲት 14 እስከ 17/2014 ለተከታታይ አራት ቀናት የቆየ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በቀጣይም በተመረጡ ጉዳዮች ላይ የአቅም ማጎልበት ስራው ቀጥሎ የሚካሄድ ሞሆን የገለጹ ዶ/ር ታደሰ ለአብት ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ስለሚመረመሩበት ሁኔታ ተከታታይ ስልጠናዎች ወደፊትም የሚሰጡ ይሆናል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ የስልጠናዎቹ ዓላማ በስራው ላይ ለተሰማሩ ከ158 በላይ ለሚሆኑ ዋና የምርመራ ቡድን አባላቶቻችን ስታንዳርዱን በጠበቀ መልኩ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመርና በማጣጣም አቅማቸው በመገንባትና የምርመራ ስራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ለማስቻል ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ከሎጀስቲክስ ድጋፍ ጋር በተያያዘ በ9 አካባቢዎች ለተሰማራው የምርመራ ቡድን ከፍተኛ የሆነ የሎጀስቲክስ እገዛ እንደሚያስፈልገው በመረዳት በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን የመጨረሻው የጋራ ጥምር የምርመራ ሪፖርት ላይ እንደተመላከተው በዋናነት ከምርመራ ጋር ተያይዞ ተጠያቂነትን ማረጋገጡ የመንግስት ይሁን እንጂ አለማቀፉ ማህበረሰብም የራሱን የሆነ ድርሻ እንዲወጣ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ሴክሬታሪያት ኃላፊው ስልጠናዎች አንድ የዕገዛ ትብብር መገለጫዎች ይሁኑ እንጂ አለማቀፍ ስታንዳርዱን የጠበቀ ምርመራ ለማካሄድ እን በፎረንሲክ፣ በሳይካትሪ፣ ሜዲካል ፕርሶኔል ያሉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ማሰማራት የሚጠይቅ ስራ ከመሆኑ አንጻር እንዳሰብነው ከአለማቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቀው የቴክኒክና የፋይናንስ ዕርዳታ ባይገኝም መንግስት ግን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ መድቦ ሁሉንም ስራዎች በቅንጅትና በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለምርመራ ቡድኑ የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ ምን ይመስላል ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም ክትትልና ድጋፉ እንደጉዳዩ እንደሚለያይ ገልጸው መንግስትም ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ባላፈ በዋናነት ልዩልዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ማረጋገጫ መስጠቱንም አንስተው የጥምር ምርመራ ቡድኑ ሪፖርትም ይህንኑ በግልጽ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ምርመራውን በቅንጅት ከማከናወን ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ እንድታከናውን የሚጠበቁ እርምጃዎችም በአንድ ወይም በሁለት ተቋማት ብቻ የሚሰሩ ወይም የሚመለሱ አለመሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መንግስት በሪፖርቱ ላይ የተቀመጡትን ምክረ ሃሳቦች ለመመለስ በሚስችለ ሁኔታ በብዙ የተቋማት ስብስብ በቅንጅት የሚመራ ግብረኃይል እንዲመሰረት የወሰነውም በዚሁ አግባብ ነው ብለዋል፡፡

የተለያዩ ተቋሞች በግብረኃይሉ ስር ተደራጅተው የተለያዩ የተሳትፎ ምሰሶዎች ተለይተው ስራዎች እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈለገበት ዋናው ምክኒያት ከዚህ የሚመነጭ መሆኑን አንስተው ግብረሃይሉ እስካሁን ባለው ሂደትም በአብዛኛው በቅንጅት አሰራር ግልጽ በሆኑ የድርጊት መርሃ ግብር እና ስትራቴጅዎችን አማካኝነት እየተንቀሳቀሰ ነው ያለው ብለዋል፤ እነኚህን እርምጃዎች በተሟላ ደረጃ ለማስፈጸም በቂ የሆነ ግብዓት ካለመኖሩ በስተቀር የተቋማቱ ተነሳሽነት እና እንደ መንግስት የተያዘው የፖለቲካ አቋም የሚበረታታ ነው ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

እንደሚታወቀው የምርመራና አጥፊን የማስቀጣት ስራውን የሚሰራው ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖችና የፍትህ ቢሮዎች የተውጣጡ ባለሚያዎችን ያቀፈ ግብረኃይል ነው፡፡ በዚህም መሰረት በቅንጅት ከመስራት አንጻር የተፈጠረ ችግር እንደሌለም ገምግመናል፡፡ በመሆኑም ስራው በተጀመረው በቅንጅት የመስራት ጠንካራ መንፈስ እና የተናጠል እና የወል ተነሳሽነት ከቀጠለ ውጤታማ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ አጥፊዎችም የሚጠየቁበት ሁኔታ እንደሚኖር ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በስተመጨረሻም ምርመራው ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ ዶ/ር ታደሰ በሰጡት ማብራሪያ ምርመራው አለም ዐቀፍ ስታንዳርዱን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን መታሰቡን አውስተው ከዚህ አንጻር ለምርመራ ቡድኑ አባላት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ጎን ለጎን እየሰጠን አለማቀፍ ስታንደርዱን የጠበቀና ገለልተኛና ከአድሎ ጸዳ እንዲሁም ግልጸኝነት የተሞላበት ምርመራ እንዲካሄድ ተገቢው ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Via task force Fb

Leave a Reply