ለትግራይ ሕዝብ የሚላኩ ሰብዓዊ ድጋፎች ለጥፋት ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳይውሉ ይደረግ!

የሕዝብን ካባ ደርቦ፣ ነገር ግን ሕዝብን እንደ ማስያዣ ተጠቅሞ ፖለቲካዊ ግብን ለማስፈጸም መስራት እንደ ሕወሓት ያሉ ራስ ወዳድ ፖለቲከኞች ሁነኛ ስትራቴጂ ነው።አሸባሪው ሕወሓትም የሕዝብን ካባ ደርቦና የውጭ ተልዕኮን ተቀብሎ ለ“ትግል” ጫካ ከገባ ማግስት ጀምሮ ዛሬም ድረስ አርባ የሚሆኑ ዓመታት ተግባሮቹ ይሄንኑ ባህሪውን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።

የሕዝብን ችግር ተጠግቶ፣ የሕዝብን ስም ጠርቶና የሕዝብ ተቆርቋሪ መስሎ የድጋፍ ሀብት መሰብሰብ፤ ኋላ ላይ በሕዝብ ሥም ተለምኖ የተገኘን ሀብትና ድጋፍን ለግል ጥቅም የማዋል እኩይ መንገዱ ዛሬም ድረስ የትግራይ ሕዝብን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡ 

የዚህ አንዱ ማሳያ የሆነው የ 1977ቱ ድርቅ ለሕወሓት እንደ ትልቅ በለስ (ዕድል) የመምጣቱ አጋጣሚ ነበር። በወቅቱ ሕወሓት ከደርግ ጋር ግጭት ውስጥ የነበረበት እና የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለመነጠል እየሰራበት ወቅት ነበር።በወቅቱ የተከሰተው ድርቅ ደግሞ በትግራይ አካባቢዎች ከፍ ያለ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር።ይሄን አጋጣሚም ሕወሓት ማሳለፍ አልፈለገም።እናም ከማዕከላዊ መንግሥት ድጋፍ ወደትግራይ እንዳይደርስ እክል በመፍጠር እና ሕዝቡም ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ተጉዞ ድጋፍ እንዳያገኝ በማለት ወደ ሱዳን እንዲሰደድ አደረገ፡፡ 

ከዚያም ቡድኑ እኔ የምታገልለት ሕዝብ ከማዕከላዊው መንግሥት ድጋፍ ተከልክሎ እንዲህ በረሃብ እየረገፈ፤ በስደት እየተንገላታ ይገኛል፤ እናም እባካችሁ ለሕዝቤ ሕልውና ድረሱለት ሲል በአዞ እንባው ታጅቦ አስተጋባ።ይሄም የውጭ ተልዕኮ አቀባዩቹ የሚፈልጉት ነበርና ተቀባበሉት፤ የእርዳታ ጎርፍም አወረዱለት።ይሁን እንጂ የድጋፍ ጥሪውም ሆነ የድጋፍ ልገሳው ሂደት ሕዝብን ሳይሆን ተልዕኮ ሰጪነትና ተቀባይነትን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ድጋፉ ለሕዝብ ሳይሆን ለሕወሓት ጉዳይ ማስፈጸሚያ እንዲውል ተደረገ።ምክንያቱም በወቅቱ ድጋፉ ለሕዝብ ታስቦ የተለመነ፤ ሕዝብን ማዕከል አድርጎ የተሰጠ ቢሆን ኖሮ በሱዳን ገበያ አየር በአየር ለሽያጭ ሲውል ለምን ብሎ መጠየቅ የተገባ ነበር። 

በዚህ ቅኝት ውስጥ ተወልዶ ያደገው ሕወሓትም ሆነ በዚህ ቁርኝት ውስጥ ለአርባ ዓመታት ተከትለውት የኖሩት “ግብረ ሰናይ” አካላት ታዲያ የትግራይ ሕዝብን ከችግር ማውጣት ላይ ሳይሆን፤ የትግራይ ሕዝብ ዘወትር የእነሱን እጅ ጠባቂ ሆኖ እንዲኖር፤ ወደሌላ እንዳያማትርም በውስጡ መረጋጋትን ነፍገው፣ ከወንድም ሕዘቦች ጋር መተማመን እንዳይኖረው እና በጠላት የተከበበ መስሎ እንዲሰማው አድርገውን ነው የኖሩት።ይሄን ያልተቀበለ  መስሎ ሲሰማቸውም በአንድ በኩል የምግብ ድጋፉን ሲነፍጉት፤ በሌላ በኩል እጁ ከነፍጥ እንዳይላቀቅ ሲቀሰቅሱት ቆይተዋል፡፡ 

ይህ ደግሞ ሕዝቡ በኢኮኖሚ ከጠነከረና ቢያንስ በምግብ ራሱን ከቻለ ለሕወሓትም ሆነ ሕወሓት ጉዳይ ለሚያስፈጸምላቸው ኃይሎች በጅ እንደማይል በመገንዘባቸው ሲሆን፤ በዚህም ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በመሰረታዊ ፍላጎቶቹ ሳይቀር የእነሱ ጥገኛና እጅ ተመልካች እንዲሆን ፈርደውበት ነው።ዛሬም እየሆነ ያለው ይሄው ነው፤ ሕዝቡ ግፋችሁ በዛብኝ፤ ጭቆናችሁ አንገሸገሸኝ፤ ሰርቼ መኖርን፣ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ጋር ተደጋግፌ መሻገርን እሻለሁ ብሎ ሲነሳ፤ ጦር አውጀው ወደ ጦርነት ማገዱት።ምግብ ነፍገው ለረሃብ ዳረጉት።ይሄንንም ሌላ በሕዝብ ስም የሚለምኑበት፤ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን የሚያስፈጽሙበት አጋጣሚ አድርገው ተጠቀሙበት፡፡ 

በተለይም ሕወሓት ከማዕከላዊ ሥልጣኑ ተገፍቶ ወደ ትግራይ ክልል ሄዶ መወሸቁን ተከትሎ፤ በአንድ በኩል ሕዝቡ ሰላምና ደህንነት እንዳይሰማው በማድረግ፣ በሌላ በኩል የቡድኑን እጅ ተመልካችነትና በቡድኑ ላይ ያለውን ጥገኝነት ከፍ የማድረግ ሥራ በስፋት ተሰርቶበታል።

ይሄ ፍላጎቱ መሟላቱንና ሕዝቡን በቁጥጥሩ ሥር ማዋሉን ሲገነዘብ በቀሰቀሰው ጦርነት ደግሞ የበለጠ ሕዝቡን ለስጋትና ለረሃብ እንዲዳደረግ በማድረግ የተለመደውን በሕዝብ ረሃብ የመቆመር የ77ቱን የተቀናበረ ድራማ ለድጋሚ እይታ ወደ አደባባይ አወጣ።እናም የማዕከላዊ መንግሥቱ ድጋፍ በመከልከሉ የትግራይ ሕዝብ ለከፋ ረሃብ ተዳርጓል፤ የመድሃኒት አቅርቦት በመቋረጡም በርካቶች የሞት አደጋ አንዣቦባቸዋል፤ ወዘተ የሚለውን የኖረ ትርክት በሕዝብ ስም ማሰማት፤ ግብራበሮቹም ይሄንኑ ማስተጋባት የዘወትር ስራቸው ሆነ፡፡ 

እውነቱ ግን ይሄ አልነበረም።ምክንያቱም መንግሥት ለሕዝቡ የምግብና መድሃኒት ብቻ ሳይሆን፤ በዘላቂነት ከጥገኝነት እንዲላቀቅ የሚያስችለውን የግብርና ግብዓቶች (ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ) ጭምር ተደራሽ እያደረገ ነበር።ሆኖም ሕወሓት ድጋፉ ወደ ክልሉ እንዳይገባ፤ ከገባም ለሕዝቡ እንዳይደርስ በማድረግ የኖረ መሰሪነቱን አሳየ። 

ሕዝቡን እንደ ማስያዣ ተጠቅሞ በመጮኸ የሚገኘውን እርዳታም ለሕዝቡ ረሃብ ማስታገሻ ሳይሆን ለቡድኑ ተዋጊዎች እንዲውል፤ ከዚህ የተረፈውን ደግሞ ለጦርነት ልጁን ለሚያዋጣ ግለሰብ ብቻ እንደ ዳረጎት መስጠትን አቅጣጫው አደረገ።ይህ የኖረው የሕወሓት ስሪት ታዲያ ከሰሞኑ በመንግሥት ከፍተኛ ፍላጎትና ትግል በየብስና በአየር ወደ ክልሉ እንዲገቡ በተደረጉ የምግብ፣ መድሃኒትና ሌሎችም ሰብዓዊ ድጋፎች ላይ እየተገለጠ ስለመሆኑ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል፡፡ 

ወደትግራይ የሚላኩ የሰብዓዊ ድጋፎች በረሃብ ለሚሰቃየው የትግራይ ሕዝብ ለረሃቡ ማስታገሻ እንጂ፤ ከሕዝብ ጉሮሮ ነጥቆ ራሱን ላጠገበ የሽብር ቡድን የበለጠ ጠግቦ እንዲያገሳ ድጋሚ እድል የሚሰጥ መሆን የለበትም።አሁን እየታየና እየተሰማ ያለው ግን ድጋፉ መቐሌ ቢገባም ሕብረተሰቡ ጋር እየደረሰ እንዳልሆነ ነው።በመሆኑም የሰብዓዊነትን ካባ ተከናንበው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሰብዓዊነታቸው የሚለካው ድጋፉን መቐሌ አስገብተው የሽብር ቡድኑ ተረክቦ ለፖለቲካ መጠቀሚያ እንዲውል በማገዛቸው ሳይሆን፤ በረሃብ ለሚሰቃየው ሕዝብ በማድረሳቸው በመሆኑ ይህንኑ ተገንዝበው በመስራት የሰብዓዊም ሆነ የሞራል ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል!

EPA

Leave a Reply