ጆ ባይደን ፑቲን በጦር ወንጀለኝነት እንዲከሰሱ ጠየቁ

በዩክሬን ርዕሰ መዲና ኪዬቭ አቅራቢያ በምትገኘው ቡቻ በተባለች አካባቢ ንጹሃን ዜጎች ላይ በሩሲያ ጦር ግድያ ተፈፅሟል መባሉን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሩስያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በጦር ወንጀለኝነት እንዲከሰሱ ጠየቁ።

Advertisements

ዩክሬን በአካባቢው የ410 ንፁሃን ዜጎችን አስከሬን መገኘቱንና የጦር ወንጀል ምርመራ መጀመሩን ብታስታውቅም ሩስያ በበኩሏ በቡቻ ተፈጸመ የተባለው ድርጊትና የቀረቡት ምስሎች በዩክሬን የተቀናበሩ ናቸው ስትል አስተባብላለች፡፡

ቡቻ የተሰኘችውን የዩክሬን ከተማ የሩሲያ ወታደሮች መጋቢት 21 2014 ዓ.ም መልቀቃቸውን ተከትሎ ከተማዋ በዩክሬን ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባቷን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የከተማዋ ከንቲባ ስለተባለው የጅምላ ግድያ በእለቱ ያሉት ነገር አለመኖሩን ሩሲያ ውንጀላው የተቀነባበረ ለመሆኑ ማሳያ ነው ስትል መከራከሪያ ሀሳብ አቅርባለች፡፡

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ የሩሲያ ጦር የወደብ ከተማዋ ማሪዩፖልን ጨምሮ በሌሎች የዩክሬን ክፍሎች ሩሲያ ፈጽማዋለች ያሏቸውን የጅምላ ጭፍጨፋዎችን ለመሸፈን ማስረጃዎችን በመደበቅ ላይ ተጠምዷል ሲሉ ወንጅለዋል፡፡

የሩስያ ጦር ላደረሰው እያንዳንዱ የጦር ወንጀል ለፍትህ ሊቀርብ እንደሚገባም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

ቡቻ በተባለችው የዩክሬን ከተማ ንጹሃን ዜጎች በሩስያ ጦር ግድያ ተፈፅሟል መባሉን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በጦር ወንጀለኝነት እንዲከሰሱ ጠይቀዋል። ፑቲን የጦር ወንጀለኛ ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ቡቻ በሩስያ ጦር በተወረረችበት ወቅት በመንገዶቿ ላይ አስከሬኖችን የሚያሳዩ ምስሎች ማክሳር በተሰኘ የሳተላይት ምስል አቅራቢ ድርጅት ይፋ ሆነዋል።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካው ጋዜጣ ኒውዮርክ ታይምስ ይዞት በወጣው የፎቶ ትንተና መሠረት የሩሽያ ጦር አካባቢውን በያዘበት የፈረንጆቹ መጋቢት 11 ቢያንስ 11 አስከሬኖች መንገድ ዳር ታይተዋል ሲል አስፍሯል፡፡

ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ ፑቲንን የወነጀሉት ባይደን “ፑቲንን የጦር ወንጀለኛ በማለቴ ትችት እንደደረሰብኝ ታስታውሳላችሁ። ቡቻ ውስጥ የሆነውን አይታችኋል። ይህም የጦር ወንጀል ነው፡፡ ይህ በጦር ወንጀል እንዲታይ ሁሉንም ዝርዝር ማስረጃዎች መሰብሰብ አለብን።” ነው ያሉት።

አስተዳደራቸው በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ለመጣል መዘጋጀቱንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የሩስያ አምባሳደር የሆኑት ቫሲሊ ኔቤንዚያ ሩሲያ ለፀጥታው ምክር ቤት በቡቻ በተፈፀሙ ክስተቶች ዙሪያ ሀገራቸው የምዕራባዊያን መግለጫዎችን ውድቅ የሚያደርጉ ተጨባጭ ማስረጃዎችን እንደምታቀርብ ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በዛሬው ዕለት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል፡፡

በዚህ ስብሰባ ላይ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪም መልዕክታቸውን እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል፡፡

እንደ ዩክሬን ገለፃ ከሆነ አንዳንዶቹ አስክሬኖች በጅምላ መቃብር የተገኙ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ እጃቸው ታስሮ በቅርብ ርቀት በጥይት ተመተው የተገደሉ ናቸው፡፡

በዩክሬን ጥያቄ አቅራቢነት ዓለም ዐቀፍ የህግ ባለሙያዎች ለዩክሬን የጦር ወንጀል መርማሪዎች ድጋፍ እንደሚሰጡ ተጠቅሷል፡፡

ፈረንሳይ እና ጀርመን በቡቻ ተፈጸመ በተባለው ወንጀል መነሾ የሩስያ ዲፕሎማቶችን ከአገራቸው ማባረራቸውን አስታውቀዋል። ሉቴኒያም የሩስያን አምባሳደርን እንዳባረረች ገልጻለች።

በሳሙኤል ሓጎስ (walta)

Leave a Reply