“ባለፉት 6 ወራት ብቻ 231 ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃዎች ተይዘዋል”


ባለፉት ስድስት ወራት 231 ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃዎች መያዛቸውን የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ሀሰተኛ መታወቂያ፣ የጋብቻ ምስክር ወረቀትና የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መምጣት ለአገልግሎት አሰጣጡ ፈተና እንደሆነበትም አብራርቷል።

ወንጀሉ አድማሱን እያሰፋ ሀሰተኛ የቦታ ካርታ ሁሉ እየተዘጋጀ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ክልሎችም ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴና የአገልግሎት አሰጣጥ ጎብኝተዋል።

አገልግሎቱ ከተቋቋመበት 1938 ዓ.ም ጀምሮ የተለያየ ስያሜ እየተሰጠው እዚህ ቢደርስም እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ የማስተናገድ አቅሙ በቀን ከ30 ሰው እንደማይበልጥ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ለረዥም ዓመታት መልካም ስም የሌለው አገልግሎት መስጫ ተቋም ተምሳሌት ሆኖ የዘለቀውን ስሙን በማደስ በ15 ቅርንጫፎቹ በ50 ልዩ ልዩ አገልግሎቶች በቀን እስከ 6 ሺህ ባለጉዳዮችን ማስተናገድ መጀመሩም ተነስቷል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃ እየተባባሰ በመምጣቱ በስራቸው ላይ ጫና መፍጠሩን አክለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ በክፍያ ስርዓት ላይ ያለው የሰዎች መጉላላት መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ገልጸው፤ የሀሰተኛ ሰነድ ማስረጃዎችን ለመከላከል ከክልሎች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You may also like...

Leave a Reply