80 በመቶ የሚሆነውን የኮንስትራክሽን ግብዓት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሠራ ነው

በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን ዋና ዋና ግብዓት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የኮንስትራክሽን ማኔጅመነት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ታምራት ሙሉ በዘርፉ የአሥር ዓመት እቅድ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን ዋና ዋና የኮንስትራክሽን ግብዓት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት መታቀዱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እስከ 60 በመቶ የሚሆኑ መሠረታዊ የግንባታ ግብዓቶች ከውጭ የሚገቡ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ በዚህ መጠን ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመገንባት አስቸጋሪ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም በሚፈለገውና በሚገባው ልክ ያላደገው እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የዕድሜው ቆይታን ያህል ተወዳዳሪ መሆን ያልቻለው ዘርፉ በውጭ ግንባታ ግብዓቶችና መሣሪያዎች ላይ ጥገኛ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ውስብስብ የሆኑ ሕንፃዎች፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እና የባቡር መንገድ ግባታዎች በአመዛኙ እየተከናወኑ ያሉት በውጭ የሥራ ተቋራጮች መሆኑንም ለዘርፉ የውጭ ጥገኝነት በአብነት አንስተዋል።

በዚህም ምክንያት አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ገፅታ ተፅዕኖው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ በቀጥታ እንዲንፀባረቅ እንዳደረገ ይገልፃሉ።

ሀገሪቱ ከጥገኝነት ለማላቀቅም መንግሥት አገር በቀል የግንባታ ግብዓቶችን ማምረት የሚያስችሉ የፈጠራ ሥራዎችን እያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

አገሪቱ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የምትጠቀማቸው ቴክኖሎጂዎች፣ የግንባታ ግብዓቶች በአብዛኛው በውጭ ምርት ላይ ጥገኛ መሆናቸውን ለመቅረፍ አገር በቀል ዕውቀቶችና የፈጠራ ሥራዎች ላይ በትኩረት እየሠራን ነው ሲሉም አክለዋል።

የዘርፉን ችግሮች በአገር በቀል ዕውቀትና ፈጠራ ሥራዎች ለመፍታት የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ከተረፈ ምርቶች ሠርተው ያቀረቡ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆች እና ግለሰቦች እንዳሉ ገልጸው በርካታ የፈጠራ ሥራዎች ወደ ሽግግርና ስርጸት እንዲያመሩ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሳተፉና ፈጠራዎችን እንዲመለከቱ እያደረግን ነውም ብለዋል።

እንደዚህ ዓይነት ምርትቶች አካባቢን ከብክለት የሚከላከሉ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን የሚቀርፉ ከመሆናቸውም በላይ የዘርፉን ግብዓቶች በአገር በቀል ምርት ለመተካት ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

የኮንስትራክሽን ማኔጅመነት ኢንስቲትዩት በተለይ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በዘርፉ የሚወጡ የፈጠራ ሥራዎችን በፋይናንስ እየደገፈ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ የኮንስትራክሽ ግብዓት አምራቾችን በቀጥታና ሙሉ በሙሉ በፋይናንስ በመደገፍ ብቻ ሳይሆን በፋይናንስ ከሚደግፉዋቸው ጋር በማገናኘት እና የገበያ ዕድሎችን በመፍጠርም ሚናውን እየተወጣ መሆኑም ጠቁመዋል።

እንደ ኢንጂነር ታምራት ገለጻ በተጨማሪ ከዚህ በፊት ይደረግ የነበረው በተለይ በኮንስትራክሽን ዕቃዎች ግዢ ላይ የሚወጡ ደረጃዎች የአገሪቱን ምርት ሳይሆን የውጭ ምርቶችን እንዲገዙ የሚያደርጉ ናቸው። ለወደፊት አሁን በሙከራ ደረጃ የተጀማመሩት የገበያ ዕድላቸው እንዲሠፋ የጨረታ ሰነዶችና የመሳሰሉት የግዢ ሂደቶች የአገር ውስጥ ምርቶችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ይደረጋል።

ይህም አገር በቀል ዕቀውቀቶችንና ፈጠራዎችን በማበረታታት የግንባታ ግብዓቶችንና የማምረቻ መሣሪዎችን ለመተካት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ እንደሆነ ኢንጅነር ታምራት ተናግረዋል።

ሙሉውን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ
https://www.press.et/?p=70623

Leave a Reply