የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እኩለ ሌሊት በተደረገ ምርጫ ከሥልጣናቸው ተነሱ

የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን ያለመተማመን ድምፅ ከተሰጠባቸው በኋላ ከሥልጣናቸው ተነሱ። የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ሌሊት አልፎ ነው የተካሄደው። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢምራን ካንን ከሥልጣን ለማንሳት ቀናት ያስቆጠረና ብዙ ድራማ የታከለበት ሂደት ውስጥ ነበሩ።

ተቃዋሚዎቹ ያለመተማመን ድምፅ አሰጣጡ ባለፈው ሳምንት ነበር እንዲካሄድ የፈለጉት። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማውን በመበተን የድምፅ አሰጣጡ እንዲዘገይ አድርገዋል።

የእሑድ ድምፅ አሰጣጥ ሊካሄድ የቻለው የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ-መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ፓርላማው በትነዋል ብሎ በመበየኑ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ካን ባለመተማመን ድምፅ ከሥልጣን የወረዱ የመጀመሪያው የፓኪስታን መሪ ይሆናሉ።

የፓኪስታን እንደራሴዎች ሰኞ ዕለት ተገናኝተው አዲስ መሪ ይመርጣሉ። አዲስ የሚመረጡት መሪ በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ጥቅምት ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ አገሪቱን ይመራሉ። 342 መቀመጫዎች ካሉት የፓኪስታን ፓርላማ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 174 ድምፅ በመስጠት ያለመተማመን ሂደቱን ደግፈዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ሼህባዝ ሻሪፍ ፓኪስታንና ፓርላማዋ “በስተመጨረሻ ከከፋ አደጋ ተገላገሉ” ሲሉ ትዊተር ላይ ለጥፈዋል።

ዓለም አቀፍ ሤራ ምንም እንኳ ማስረጃ ባይኖራቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ካን፤ በሩሲያና ቻይና ጉዳይ ድጋፍ ባለማሳየቴ አሜሪካ ከሥልጣን እንድነሳ ትፈልጋለች ይላሉ። ኢምራን ካን በተደጋጋሚ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከውጭ ኃይሎች ጋር አብረው እየሠሩ ነው ሲሉ ይከሳሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ክስ ውሃ አያነሳም ትላለች። ካን፤ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወታደራዊ

 ጥቃት ባደረሰችበት ወቅት ሞስኮው ሄደው ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋር ተገናኝተዋል። አልፎም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆርጅ ቡሽ ሽብር ላይ የሚደረግ ጦርነት ያሉትን ዘመቻም በግልፅ ይቃወማሉ።

ያለመተማመን ድምፅ መስጠት ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የኢምራን ካን ወዳድና የታችኛቸው ፓርላማ አፈ-ጉባዔ የሆኑት አሳድ ቃይሰር ሥልጣን መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል። ፒቲአይ የተባለው የኢምራን ካን ፓርቲ አባላትም ጠቅላይ ሚኒስትራቸው የዓለም አቀፍ ሤራ ተጠቂ ሆኗል በማለት ሕንፃውን ቀለው ወጥተዋል።

ኢምራን ካን ማናቸው?

ኢምራን ካን የቀድሞው የፓኪስታን ክሪኬት ብሔራዊ ቡድን አምበል ነበሩ። ወደ ሥልጣን የመጡት በፈረንጆቹ 2018 ሲሆን ሙስናን ለመታገል፤ ምጣኔ ሀብቱን ለማስተካከል ቃል ገብተው ነበር። ነገር ግን ፓኪስታን ከገባችበት የፋይናንስ ቀውስ እስካሁን መውጣት አልቻለችም።

ኢምራን ካን በብዙዎች ዘንድ ቢወደዱም ባለፈው ወር በተነሳባቸው ተቃውሞ ምክንያት መንበራቸው መንገዳገድ ያዘ። የፓርቲያቸው ሴናተር የሆኑት ፋይሳል ጃቬድ ካን እንደሚሉት “ኢምራን ካን ወደ ቤተ- መንግሥቱ ያቀኑት በክብር ነው ሲወጡም አላጎበደዱም። “የጠቅላይ ሚኒስትር ካን ፓርቲ “መሪያችን አገራችንን ከፍ ከፍ አድርጓል” ይላሉ። ምንጭ ቢቢሲ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2014

Leave a Reply