ሮማን አብራሞቪች፡ ከማደጎ እስከ ቢሊየነርነት

ገና በሦስት ዓመቱ ወላጆቹን በሞት የተነጠቀው ዛሬ ላይ ከዓለማችን እጅግ ከናጠጡ ባለጸጎች መካከል ተጠቃሹ ነው፤ ሮማን አብራሞቪች።

ሮማን አብራሞቪች ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ያለው የጠበቀ ግንኙነት የገነባውን ገናና ስምና ንግድ እያሳጣው ይገኛል።

”እርግጠኛ ሰዎች ለሦስት ወይም አራት ቀናት እኔ ላይ ትኩረት ያደርጉ እና ከዛ ያልፋል። እኔ ላይ ትኩረት አያደርጉም። ማን እንደሆንኩኝ ቶሎ ይረሳሉ። እኔ ደግሞ ይሄ በጣም ነው የሚስማማኝ” ብሎ ነበር ቢሊየነሩ የለንደኑን የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቡድን ቼልሲን በገዛ ወቅት።

ነገር ግን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ዓለም ሁሉ የሚያወራው ስለዚህ ቢሊየነር ሆኗል። የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በአብራሞቪች ንብረት ላይ እግድ ጥሏል።

ይህ እግድ ቼልሲ እግር ኳስ ክለብ እና መኖሪያ ቤቶቹን ይጨምራል። ከንብረት እግዱ በተጨማሪ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ)መንግሥት የጉዞ እገዳም ጥሎበታል።

የዩኬ መንግሥት ይህንን ያደረግኩት አብራሞቪች በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸሙት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የቀረበ ትስስር ስላለው ነው ብሏል።

አብራሞቪች ስመ ጥር የንግድ ሰው ለመሆን ብዙ ፈተናዎችን አልፏል። ገና ከጨቅላ እድሜው ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ነው ዓለማችን ላይ ተጽእኖ መፍጠር ከሚችሉ ቢሊየነሮች መካከል ተጠቃሽ መሆን የቻለው።

ከወላጅ አልባነት ወደ ቢሊየነርነት

ሮማን አብራሞቪች እአአ 1966 በደቡብ ምዕራባዊ ሩሲያ ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ሳራቶቭ በተባለች ከተማ ነበር የተወለደው።

አብራሞቪች ገና የአንድ ዓመት ልጅ ሳለ ነበር ወላጅ እናቱ ኤእሪ በደም መመረዝ ምክንያት ሕይወቷ ያለፈው። ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ አባቱ በግንባታ ሥራ ላይ ባጋጠመው አደጋ ሕይወቱ አለፈ። ከዚህ በኋላ አብራሞቪች እድገቱ የአየሩ ሁኔታ እጅግ ቀዝቃዛ እና ሕይወት ከባድ በሆነች የሩሲያ ክፍል ውስጥ በዘመዶች እጅ ሆነ።

“እውነቱን ለመናገር ልጅነቴ በጣም መጥፎ ነበር አልልም። በልጅነታችን ነገሮችን መለየት ላይ እስከዚህም ነን። አንዱ ህጻን ካሮት ይበላል፤ ሌላኛው ደግሞ ከረሜላ ይበላል። ሁለቱም ለልጆች ጣፋጭ ናቸው። በልጅነታችን እነዚህን ልዩነቶች አናስተውላቸውም” ብሎ ነበር አብራሞቪች ከጋርዲያን ጋር ቆይታ ባደረገ ወቅት።

ሮማን አብራሞቪች በወጣትነቱ
የምስሉ መግለጫ, ሮማን አብራሞቪች በወጣትነቱ

በ16 ዓመቱ ትምህርቱን በማቋረጥ በመካኒክነት የሥራ ሲሆን ሞስኮ ውስጥ ደግሞ ከፕላስቲክ የተሰሩ የህጻናት መጫወቻዎችን ይሸጥ ነበር። የሶቪየት ሕብረት መከላከያ ኃይልንም ተቀላቅሎ ነበር።

የወቅቱ የሶቪየት ሕብረት መሪ የነበሩት ሚኻኤል ጎርባቾቭ ለሥራ ፈጣሪዎች የሚመች አስተዳደር መዘርጋታቸውን ተከትሎ አብራሞቪች ሽቶ በመሸጥ ጠቀም ያለ ገንዘብ መሰብሰብ ጀመረ።

የሶቪየት ሕብረት መበተንን ተከትሎ የነዳጅ ኩባንያዎች ከመንግሥት እጅ ወጥተው ለባለሀብቶች መሸጥ ተጀመረ። ገና በሀያዎቹ አጋማሽ የእድሜ ክልል ውስጥ የነበረው አብራሞቪች አጋጣሚውን ከመጠቀም አልቦዘነም።

በተጭበረበረ ነው በተባለ የጨረታ ሂደት አብራሞቪች ‘ሲብኔፍት’ የተባለውን የነዳጅ ኩባንያ በአውሮፓውያኑ 1995 ላይ ከመንግሥት በ250 ሚሊየን ዶላር ገዛ። ከአስር ዓመታት በኋላ ማለትም እአአ 2005 ላይ መልሶ ይህንኑ ኩባንያ ለመንግሥት በ13 ቢሊየን ዶላር ሸጠው።

ምንም እንኳን የአብራሞቪች ጠበቆች ቢሊየነሩ የነዳጅ ድርጅቱን በሚገዛበት ወቅት ምንም አይነት ሕገ ወጥ ነገር አልፈጸመም ብለው ቢከራከሩም፤ 2012 ላይ በአንድ የዩኬ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ግን አብራሞቪች እራሱ የኩባንያውን ግዢ ለማቀላጠፍ ክፍያ መፈጸሙን አምኗል።

በ1990ዎቹ አካባቢ ደግሞ በሩሲያ የአልሙኒየም ንግድ ዘርፍን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፍትጊያ ነበር። ”በየሦስት ቀኑ የሆነ ሰው ይገደል ነበር” ይላል አብራሞቪች። ግድያው የሚፈጸመው በተፎካካሪ የአልሙኒየም ነጋዴዎች ላይ ነበር።

ይህንን ያስተዋለው አብራሞቪች የራሱንና የቤተሰቦቹን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲል ከዚህ ንግድ እራሱን በሂደት አግልሏል። ይሁን እንጂ ባልተረጋጋ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ሆኖ እንኳ አብራሞቪች ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን መሰብሰብ ችሏል።

ጉዞ ወደ ፖለቲካ

የሩሲያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ቦሪስ ዬልሲን ጥሩ ወዳጁ ነበሩ። እንዲያውም በአንድ ወቅት በሞስኮ የፖለቲካ ዓለም ውስጥ ተሳትፎው ጠንክሮ በክሬምሊን መኖሪያ ቤት እንዲሰጠው ተደርጎም ነበር።

1999 ላይ ፕሬዝዳንት ቦሪስ ዬልሲን ከሥልጣናቸው ሲወርዱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትና የቀድሞው የሩሲያ የስለላ ተቋም ኬጂቢ ሰላይ ቭላድሚር ፑቲን ቦሪስ ዬልሲንን እንዲተኩ ከደገፏቸው ሰዎች መካከል አብራሞቪች አንዱ ነበሩ።

ፑቲን ሥልጣን በያዙ በመጀመሪያዎቹ ወራት የሶቪየት ሕብረት መፍረስን ተከትሎ ቢሊየኖችን መሰብሰብ የቻሉ ባለሃብቶች ላይ ትኩረት አድርገው ነበር።

ለፑፒን አጋርነታቸውን ማሳየት ያልቻሉት ከአገር የወጡ ሲሆን ገሚሶቹ ደግሞ ወደ እስር ቤት እንዲወረወሩ ተደርጓል።

ሮማን አብራሞቪች ከቭላድሚር ፑቲን ጋር
የምስሉ መግለጫ, ሮማን አብራሞቪች ከቭላድሚር ፑቲን ጋር

አብራሞቪች ከፑቲን ጎን መሰለፍን መርጧል።

እንደውም እአአ 2000 ላይ አብራሞቪች በሰሜን ምሥራቃዊ ሩሲያ የተጎዳ የሚባለው ቹኮትካ ግዛት አስተዳዳሪ ሆኖ ተሹሞ ነበር።

አብራሞቪች የራሱን ገንዘብ በመጠቀም ዜጎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማድረጉን ተከትሎ ከፍተኛ ተቀባይነት ቢያገኝም፣ በ2008 ላይ በገዛ ፈቃዱ ከሥስልጣኑ ወርዷል።

ሥልጣን ይበቃኝ ቢልም፤ የንግድ ሥራውን ግን አቀላጥፎ ቀጥሏል። መኪኖችን፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ውድ የጥበብ ሥራዎችን በመሰብሰብም ይታወቃል።

እግር ኳስና አብራሞቪች

በአውሮፓውያኑ 2003 ዝምተኛውና አይናፋር ነው የሚባለው አብራሞቪች የእንግሊዙን ቼልሲ የእግር ኳስ ክለብ በ140 ሚሊዮን ፓዎንድ በመግዛት በእግር ኳስ ወዳጆች ዘንድ ዝናው ናኘ።

አብራሞቪች ቼልሲን ከገዛ በኋላ ቡድኑ አምስት ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መሆን የቻለ ሲሆን፣ ሁለት ቻምፒየንስ ሊግ እንዲሁም አምስት የኤፍኤ ዋንጫዎችን አሸንፏል።

የዩኬ መንግሥት ማዕቀብ ከመጣሉ 8 ቀናት አስቀድሞ አብራሞቪች ቼልሲን ለሽያጭ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

“አንድ ቀን በአካል በስታምፎርድ ብሪጅ ተገኝቼ እሰናበታችኋለሁ” ሲል መልዕክቱን ለቼልሲ ደጋፊዎች አስተላልፏል።

አብራሞቪች በለንድን የእግር ኳስ ክለብ ብቻ ሳይሆን ከ150 ሚሊዮን ፓዎንድ በላይ የሚገመት ባለ15 ክፍል የተንጣለለ መኖሪያ ቤት አለው።

ሦስት ጊዜ ትዳሩን የፈታው አብራሞቪች፤ በዓለማችን ግዙፍ ከሚባሉ ቅንጡ የመዝናኛ መርከቦች መካከል የሚዘረዘሩት ሶላሪስ እና ኢክሊፕስ የተባሉት የግሉ ናቸው።

የአብራሞቪች አጠቃላይ ሀብት 13.7 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሲሆን፣ በዓለማችን 128ኛው ሀብታም ሰውም ነው ሲል ብሉምበርግ ብሏል።

ፎርብስ ግን የአብራሞቪች አጠቃላይ ሀብት ከ12.3 ቢሊየን እንደማይበልጥና በዓለማችን ካሉ ባለሀብቶች አንጻር 142ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።

BBC Amharic

Leave a Reply