የሶማሊያ ድርቅ፡ “አሁኑኑ እርምጃ ካልተወሰደ 350 ሺህ ሕፃናት ይሞታሉ”

ሶማሊያ በዐሥር ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ ድርቅ እያስተናገደች ባለችበት በዚህ ወቅት ሕፃናት ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በባሰ መከራ ላይ ወድቀዋል።

በአገሪቱ ከሚገኙ ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሕፃናት ግማሽ ያህሉ በመጪዎቹ ወራት በከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊሰቃዩ እንደሚችሉ ተተንብዮዋል።

ኒምኮ አብዲ የስድስት ወር ልጇን በገመድ በሚንጠለጠለው እና ክብደት ለመለካት በሚረዳው የፕላስቲክ ከረጢት ላይ አስቀምጣው የሚነበበው ውጤት እጅግ ያልተለመደ ነው።

የክብደት መለኪያው 4 ኪሎ ግራም ያመላክታል። ይህ ቁጥር ልጇ መሆን ከሚገባው ትክክለኛ ክብደት በግማሽ አከባቢ ያነሰ ነው።

ከዕድሜዋ አንጻር በክብደት በጣም ትንሽ ነች። ዐይኖቿ ሊወድቁ የደረሱ ይመስላሉ። አጥንቶቿ ይቆጠራሉ።

ቆዳዋም የተሸበሸበ እና የገረጣ ነው። እናቷ ከተቀመጠችበት ሚዛን ስታነሳት በምግብ ማጣት የገጠማት ዐቅም ያነሰው ለቅሶዋ ይሰማ ነበር።

“ጡት እያጠባኋት ነበር። ነገር ግን በምግብ እጦት በጣም ታምሜያለሁ። እሷም በጣም ስለከሳች ወደዚህ ላመጣት ወሰንኩ። ቢያንስ ወተት እና መድኃኒት ማግኘት ትችላለች” ስትል የምታስረዳው ኒምኮ በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ከሞቃዲሾ 500 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መቅረቢያ ማእከል ደርሳለች።

ኒምኮ በማእከሉ ውስጥ አልጋ የሚቀርብላት ሲሆን አልጋውን እንደሷ ችግር ላይ የወደቀ ልጅ ካላት ሌላ እናት ጋር ትጋራዋለች።

ይህ የኒምኮ ፈተና በሶማሊያ ልጆቻቸው በምግብ እጦት ሊሞቱ የሚችሉ በርካታ እናቶች ያሉበትን እውነታ የሚያንጸባርቅ ነው።

“ምንም ካልተደረገ በመጪው ክረምት በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ 1.4 ሚሊዮን ሕፃናት መካከል 350 ሺህ የሚሆኑት ሞት እንደተጋረጠባቸው ተገምቷል” ሲል የሚያስጠነቅቀው በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ወይም ኦቻ ውስጥ የሚሠራው አደም አብደልሙላ ነው።

“በዚህች አገር 70 በመቶ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ አይደለም። በአንድ ግዛት ወይም በጁባ ላንድ ብቻ ድርቁ 40 ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል። ተመሳሳይ ነገር በድርቁ በተጠቁ አካባቢዎች እየተለመደ ነው” የሚለው አደም አንዳንድ ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን መመገብ ስላልቻሉ ያለዕድሜያቸው እየዳሯቸው እንደሚገኙም አስረድተዋል።

የተራቆቱ መንደሮች

በሉቃ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ማእከል ውስጥ ነርስ የሆነችው ፋጡማ መሐመድ የማእከሉ አልጋ ማስተናገድ የሚችለው 18 ሕፃናት ቢሆንም ከ50 በላይ ሕፃናት እና እናቶቻቸው በማእከሉ እንደሚኖሩ ትናገራለች።

“እያስጨነቀን ያለው የቁጥሩ እያደረገ መሄደ ነው። እየሠራን ያለነው ከዐቅማችን በላይ ነው። የሕክምና ቁሳቁስ እጥረትም ገጥሞናል” ትላለች።

አንዳንዶቹ ልጆች በጣም በመዳከማቸው በመንገድ ላይ ይሞታሉ።

“እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እጅግ የተጎዱ ልጆቻቸውን ይዘው ይመጣሉ። አብዛኛዎቹም ደግሞ አጣዳፊ ተቅማጥ እና ኩፍኝ አለባቸው” ስትል ትናገራለች።

ይህ ማእከል በመላው ሶማሊያ ያለውን ሁኔታ እጅግ በጥቂቱ ያመላክታል። ድርቁ 4.5 ሚሊዮን ሰዎችን የጎዳ ሲሆን በሶማሊያ ትልቁን የጁባ ወንዝ ውሃ አልባ አድርጎታል።

ድርቁ 4.5 ሚሊዮን ሰዎችን የጎዳ ሲሆን በሶማሊያ ትልቁን የጁባ ወንዝ ውሃ አልባ አድርጎታል
የምስሉ መግለጫ, ድርቁ 4.5 ሚሊዮን ሰዎችን የጎዳ ሲሆን በሶማሊያ ትልቁን የጁባ ወንዝ ውሃ አልባ አድርጎታል

የተባበሩት መንግሥታት እንዳወጣው መረጃ ወደ 700,000 የሚጠጉ ሰዎች ለራሳቸው እና ለሚያረቧቸው እንስሳት ምግብና ውሃ ፍለጋ ከቤታቸው እየተፈናቀሉ ሲሆን ይህ ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

በሶማሊያ ለተከታታይ አራት ወቅቶች በሚጠበቀው የዝናብ ወቅት ጠብ ያለ ነገር የለም። ሙቀቱም እጅግ ያየለ ሲሆን 90 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ክፍል ደረቅ ሆኗል።

በአገሪቱ የገጠር መንገዶች ላይ የእንስሳት ሬሳ በየቦታው ወድቆ ይታያል። የሞቱ ፍየሎች፣ አህዮች እና ግመሎች መንገዶቹን ሞልተውታል።

ይህ በእንስሳት እርባታና ሽያጭ ኑሯቸው ለተመሠረተው በርካታ የሶማሌ አርብቶ አደሮች ከባድ ጉዳት ነው።

የምግብ እና የውሃ ዋጋ እየናረ ሲሆን ሰዎች ችግሩን ሽሽተው ከተማ ወደሚገኙ ማእከላት ሲተሙ የገጠር መንደሮች ተራቁተው ይታያሉ።

በነዚህ መንደሮች የቀሩት አዛውንቶች ብቻ ሲሆኑ እነሱም ሁለት ነገሮችን ይጠብቃሉ። ከሶማሊያ ምድር የራቀው ዝናብ እስኪመጣ ወይም ልጆቻቸው ውሃ ይዘው እስኪመለሱ።

ድርቁ በሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በተቀረው የአፍሪካ ቀንድ እና ሌሎች በርካታ የአህጉሪቱን ክፍሎች ላይ በትሩን እያሳረፈ ነው።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ቢያንስ አንድ አራተኛ የሚሆነው የአፍሪካ ክፍል የምግብ ዋስትና ችግር እንዳለበት አሳውቋል። የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።

ይህ አስከፊ ሁኔታ ግን በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ ትኩረት አጥቷል። ርብርቡ፣ እርዳታ እና ድጋፉ ወደ ዩክሬን ሲዞር ይህን ከባድ የረሃብ ቀውስጥ ‘ጉዳዬ’ ያለው አካል ተመናምኗል።

የተፈናቃይ መጠለያዎች በመላው ሶማሊያ ያሉ ሲሆን አዳዲሶችም እየመጡ ነው።

ይህ የዘንድሮ ድርቅ ከመከሰቱ በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 በተከሰተው እና ብሔራዊ አደጋ ተብሎ በታወጀው ድርቅ ምክንያት መጠለያ የገቡ አንዳንድ ሰዎች እስካሁን አላገገሙም።

‘መጪው ጊዜ ከዚህም ይከፋል’

ከሉቁ የተመጣጠነ የምግብ ማእከል በስተሰሜን አቅጣጫ በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኘው ጋካዮ በተባለው መጠለያ ውስጥ የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ሃዋ ፋርጎድ ከሁለት ልጆቿ ጋር ተቀምጣለች።

ጎጆዋ በማእከሉ እንደሚገኙት በመቶች እንደሚቆጠሩ ቤቶች ከእንጨት የተሠራ ሲሆን በማዳበሪያ ከረጢት የተሸፈነ ነው።

ከሃዋ ፋርጎድ አጠገብ ደግሞ ሃዋ ሻሪፍ ትገኛለች። ሃዋ ሻሪፍ በአህያ ጋሪ ተሳፍራ ከአምስት ልጆቿ ጋር ወዲዚህ መጠለያ የሦስት ቀን ጉዞ አድርጋ መድረሷን ትናገራለች። ወደ መጠሊያው ስትደርስ አህያዋ ሞታለች።

“ያቺ አህያ በሕይወት የተረፈች የመጨረሻዋ እንስሳችን ነበረች። የተቀሩት በሙሉ ሞተዋል” ስትል ታስረዳለች።

ሃዋ ካለባት የኩላሊት ሕመም እና ከታመሙት ልጆቿ ጋር አስከፊውን እውነታ እየተጋፈጠች ሲሆን መጪው ጊዜ ላይ ያላት ተስፋ ተሟጧል
የምስሉ መግለጫ, ሃዋ ካለባት የኩላሊት ሕመም እና ከታመሙት ልጆቿ ጋር አስከፊውን እውነታ እየተጋፈጠች ሲሆን መጪው ጊዜ ላይ ያላት ተስፋ ተሟጧል

ይህ ድርቅ ቤተሰቦች እንዲለያዩ ሰበብም እየሆነ ነው። ወንዶቹ ኑሯቸውን ለመግፋት ወደ ከተሞች ሲጓዙ ሴቶችና ሕፃናት ደግሞ እርዳታ ወደሚያገኙበት ስፍራ ያቀናሉ።

የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት ከፍተኛ የገንዘብ ችግር አለብን የሚሉ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ችግር ለማቃለል ከሚያስፈልጋቸው የገንዘብ መጠን ውስጥ 3 በመቶ ብቻ እንዳላቸው ይናገራሉ።

ተቋማቱ የውሃ መኪኖችን፣ የምግብ አቅርቦትን እና የሕክምና ቁሳቁሶችን ለማዳረስ እየጣሩ ቢሆንም ከእርዳታ ፈላጊው ቁጥር ጋር የሚራራቅ ነው።

በቀጣዩች ሳምንታት ተጫማሪ የገንዘብ አቅርቦት እና እርዳታ የማይቀርብ ከሆነ ደግሞ የነዚህ ተቋማት ድጋፍም ጥያቄ ውስጥ ይገባል።

በያዝነው ወር ያለው የዝናብ መጠን አማካይ ወይም ከአማካይ በታች ሊሆን እንደሚችል የተተነበየ ሲሆን መጪው ጊዜ ግን ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ተፈርቷል።

እያንዣበበ ያለውን አደጋ ሃዋ ፋርጎድ በሚገባ ተረድታዋለች።

ካለባት የኩላሊት ሕመም እና ከታመሙት ልጆቿ ጋር አስከፊውን እውነታ እየተጋፈጠች ሲሆን መጪው ጊዜ ላይ ያላት ተስፋ ተሟጧል።

በመጪው ጊዜ ተስፋ በቆረጠ ስሜት “የምፈራው ለልጆቼ ነው” ብላለች።

Source BBC

Leave a Reply