ለህብረተሰቡ የቀረበ ጥሪና ጥቆማ

ማህበረሰቡ በማህበራዊ ሚዲያና በገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎች ተታሎ የባንክ ሂሳቡን ለአጭበርባሪዎች ባለማስተላለፍና ገቢ ባለማድረግ ወንጀልን አንዲከላከል የቀረበ ጥሪና ጥቆማ

በማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም ሞባይል ባንኪንግን ጨምሮ በሌሎች የንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎች የሚፈፀሙ የማጭበርበር ወንጀሎች ውጤታማ እንዳይሆኑ የህብረተሰቡ ተሳትፎ የግድ አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም ህብተረሰቡ ከአታላይ ወንጀለኞች እራሱን እንዲጠብቅ ጥሪና ጥቆማ ቀርቧል ።

ጥሪና ጥቆማውን የሰጠው ከፍተኛ ቁጥርና ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው አቤቱታዎችና ጥቆማዎች በተበዳዮች በተደጋጋሚ እየደረሰኝ ነው ያለው በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ነው።

የወንጀል ድርጊቶቹን ጥቆማና አቤቱታ መነሻ በማድረግ ከሚመለከተው የፖሊስ ምርመራ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በድርጊቱ ፈፃሚዎች ላይ በርካታ ምርመራዎችን በማድረግ ላይ እገኛለሁ ከእነዚህ ውስጥ ምርመራቸው በተጠናቀቁት ላይ ደግሞ ስልጣን ወዳለው ፍርድቤት ጉዳዮቹን በመውሰድ በአጥፊዎቹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ እንዲሰጥና ተገቢው ቅጣት እንዲወሰንባቸው ማድረግ ተችሏል ብሏል።

የተወሰኑ የክስ መዛግብት ደግሞ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ እንደሚገኙ አሳውቋል ።
ዳይሬክቶሬቱ በምርመራ ሂደት ተጠርጣሪ ሆነው ካገኛቸው እንዲሁም ክስ በቀረበባቸው ጉዳዮች ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የተወሰኑ የውጭ ሀገር ዜጎችም በድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው እንደተገኙ ገልጿል፡፡

የወንጀል አይነቶቹ ተደጋጋሚና ተመሳሳይ ሆነው ከተገኙ ወንጀሎች አፈፃፀም ለመረዳት እንደተቻለው ፦
1.በማህበራዊ ሚዲያ (በፌስ ቡክ፤ ዋትስ አፕ፤ ቴሌግራም ወዘተ) በመጠቀም ኢትዮጵያዊ ወይም የውጭ ሀገር ግለሰቦች ስም አካውንት ወይም የፌስ ቡክ ስም በመክፈት በከፈቷቸው አካውንቶች ግለሰቦችን ጓደኛ በማድረግ መልዕክት ሲለዋወጡ ይቆያሉ የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀምና በማግባባት የውጭ ሀገር ነዋሪ ወይም ዜጋ መሆናቸውን በመግለፅ ግንኙነታቸውን ካጠናከሩ በኋላ የትዳር አጋር እንደሚያደርጓቸውና ወደፊት ጋብቻ መስርተው በመረጡት ሀገር አብረው እንደሚኖሩ ቃል በመግባት ወይም የንግድ ስራ አጋር በመሆን ዕቃዎችን የመላክና የማስመጣት ሥራን አብሮ ለመስራት እንደሚፈልጉ በመግለጽ እንዲሁም በውጭ ሀገር ሲኖሩ ያገኙትን ሀብትና ገንዘብ በመላክ ኢንቨስት ለማድረግ እንደሚፈልጉ በመናገር እና ሌሎች አሳሳች ድርጊቶችን በመፈፀም ተበዳዮች የተሳሳተ እምነት እንዲያድርባቸው ካደረጉ በኋላ፡-
የማህበራዊ ሚዲያ ጓደኝነታቸው ሲጠናከር ውድ የሆኑ ስጦታዎችን ወደ ኢትዮጵያ የላኩላቸው መሆኑን በመግለፅ የተላከውን ስጦታም እንዲቀበሉ ይነግሯቸዋል የወንጀል ፈፃሚዎቹ ግብረ አበሮች ለግል ተበዳዮች ስልክ በመደወል ከዴሊቨሪ (ከኤርፖርት ካርጎ) እንደተደወለ በማስመሰል “ የስጦታ ዕቃ መጥቷል መውሰድ ትችላላችሁ ነገር ግን የመላኪያ ብር ስለሚያስከፍል ገንዘብ አስገቡ ” በማለት በሃሰተኛ መታወቂያ የተከፈተ የባንክ አካውንት ቁጥር በመላክ ተበዳዮችም ለመላኪያ ተብለው የተነገራቸውን የገንዘብ መጠን ካስገቡ በኋላ በአታላዮች በኩል ዕቃው ውድ ߹ ከውጭ የመጣና ህጋዊ ስላልሆነ አልያም ብዛት ያለው የውጭ አገር ገንዘብ አብሮ ስለተገኘ ለማስለቀቂያ ወይም ህጋዊ ስለመሆኑ የሰርተፍኬት ማስወጫና መሰል አሳማኝ ተጨማሪ ምክንያቶችን እየተጠቀሙ ተበዳዮች “አተርፍ ባይ አጉዳይ” አንዲሉ በግል አካውንታቸው የተቀመጠ ገንዘባቸውን ወይም በብድር ወይም በሌላ መንገድ ያገኙት ገንዘብ እስከሚያልቅ ድረስ በተደጋጋሚ ገቢ እንዲያደርጉ ተታለው ገንዘባቸው በአታላዮች እየተወሰደባቸው ነው ብሏል ።

See also  በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረታዊ ነጥቦች

2.ዳይሬክቶሬቱ እንዳስታወቀዉ ከማታለያ ዘዴዎች መካከል በተጨማሪነት የሚጠቀሰው አታላዮች የተለያዩ ህጋዊ ያልሆኑ ዌብሳይቶች ከፍተው ህጋዊ በማስመሰል ለትምህርትና ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የሚልኩ በመምሰል በውጭ ሀገር የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ወይም አሠሪ ድርጅቶች በሃሰት የተቀበሏቸው መሆኑን በመግለፅ የማረጋገጫ ኮዶችን ወደ ተበዳዮች ስልክ ወይም ኢሜል በመላክ በረጅም ጊዜ የሚመለስ ወይም ቅድሚያ ክፍያ ገንዘብ አስገቡ በማለት በብዙ መቶ ሺዎች የሚገመት ገንዘብ በሃሰተኛ መታወቂያ በተከፈተ የባንክ አካውንት የተበዳዮች ገንዘብ እንደተወሰደባቸው ለማረጋገጥ ተችሏል ።

  1. በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ደንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል በተለይም እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና በባንክ ስራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት በደንበኞች አገልግሎት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርጉበት ይገባል የሚለው ግለሰቦች በስልካቸው የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶች ተጠቃሚ የሆኑትን ዘመናዊ የግብይት ማሳለጫ ስርዓት (የሞባይል ባንኪንግና ሌሎች የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን) እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የማታለል ወንጀል ድርጊት እየተፈፀመ መሆኑን አረጋግጫለሁ የሚል ነው ከእነዚህ መካከል ፦
    ባንኮች የደንበኞቻቸውን ማንነት እንዲያጣሩ የሚያዘውን የባንክ መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ባንኮቹ ለደንበኞቻቸው ያደረጉትን የሚዲያ ጥሪ ተከትሎ ወንጀል አድራጊዎች ለግለሰቦች በመደወልና ጥሪው ከባንኩ እንደሆነ በማስመሰል የደንበኞች ማጣሪያ ሂደት መሆኑን በመግለፅ ተበዳዮች የሚነገራቸውን ኮድ በስልካቸው እንዲያስገቡ በማዘዝ ተበዳዮችም የተባሉትን በሚፈፅሙ ጊዜ ወደ ወንጀል አድራጊዎቹ ሂሳብ ወይም የስልክ ቁጥር ወይም በስልክ ገንዘብ ሊተላለፍባቸው በሚችሉ እንደ ቴሌ ብር ያሉ የክፍያ ዘዴዎች ላይ ገንዘብ እንዲተላለፍላቸው በማድረግ እየወሰዱ መሆኑ ነው፡፡

በሌላ በኩል የግለሰቦች ስልክ በቀማኞች ወይም በሌላ ምክንያት ከተወሰደ በኋላ ወንጀል አድራጊዎች የይለፍ ቃል ( pass word ) ከማን እና ከየት እንዳገኙት ለጊዜው ባልተወቀ ሁኔታ ግለሰቦቹ ስልካቸውን ብቻ ሳይሆን በባንክ አካውንታቸው ያለው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ እየተወሰደባቸው ነው ብሏል ።

በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችለው ደግሞ የግለሰቦች የስልክ ቁጥር ከሳምንቱ በአንዱ ቀን በተለይም ቅዳሜ ቀን ድንገት ይዘጋል የስልክ ቁጥሩ አይደውልም አይቀበልም በዚህ ጊዜ ተበዳዮች ሰኞና ማክሰኞን ጠብቀውወይም በአንደኛው ቀን ወደ ኢትዮ ቴሌኮም በመሄድ ሲምካርዳቸውን አንደ አዲስ በድጋሚ በማውጣት አገልግሎት ላይ ሲያውሉ ከግልየባንክ አካውንታቸው ወደ ሌላ የባንክ አካውንት ገንዘብ የተላለፈበት የማሳወቂያ መልዕክት ይገባላቸዋል ሂሳቡ የተላለፈበት የባንክ አካውነት በባንክ ባለሙያዎች ሲረጋገጥ በሃሰተኛ መታወቂያ ከመከፈቱ በተጨማሪ የባንክ አካውነቱ ቀሪ ሒሳብ ባዶ ሆኖና ተዘግቶ ይገኛል በዚህም ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የተወሰደባቸው ግለሰቦች ገጥመውኛል ብሏል ።

  1. በበይነ መረብ የሚደረጉ የመስመር ግብይቶችን (online market) ጋር በተያያዘ ደግሞ አታላዮች ዕቃውን ለሚሸጡና ለሚገዙ ነጋዴዎች ወይም ግለሰቦች ገንዘብ ማስተላለፋቸውን የሚገልፅ ሃሰተኛ የባንክ መልዕክት እንዲደርሳቸው በማድረግ የሚፈልጉትን ዕቃ ከወሰዱ በኋላ ተበዳዮቹ የግል አካውንታቸውን ሲያዩና ሲያረጋግጡ ምንም አይነት ገንዘብ ወደ አካውንታቸው እንዳልገባና በሃሰት ወደ ስልካቸው የገባውን የባንክ ማሳወቂያ መልዕክትም በድጋሚ እንደማያገኙት የተበዳዮች አቤቱታ ያሳያል ።
  2. ሌላው ቴሌግራም ነው የግለሰቦችን ስልክ ቁጥር በመጠቀም ቴሌግራም የተባለውን ማህበራዊ ሚዲያ ከግል ተበዳዮቹ እውቅና ውጭ አካውንት በመክፈት ማረጋገጫ (Confirmation) ኮዱን በተመለከተም ከቴሌግራም የተላከውን የጽሁፍ መልእክት ለማግኘት ወደ ግል ተበዳዮች በመደወል በስህተት ኮድ ወደ እነሱ ስልክ ቁጥር እንደገባና አሳሳች ነገር በመናገር እንዲልኩላቸው ካደረጉ በኋላ ከግለሰቦች ፍቃድ ውጭ በቴሌግራም አካውንታቸው በመግባት የግለሰቦችን የግል ሚስጥር (የተቀረፁ ድምፆች߹ ፎቶ እና ቪዲዮ ) የመሳሰሉትን በመያዝ በማህበራዊ ሚዲያ እንደሚለቁባቸው በማስፈራራት ከግል ተበዳዮች ገንዘብ ይቀበላሉ ወይም ከግል ተበዳዮች የቅርብ ሰዎች በተበዳዮች ስም ጓደኛና ዘመድ በመምሰል ገንዘብ እንዲላክላቸው በማድረግ በብዛት የማታለል ወንጀሉ እየተፈፀመ ነው ብሏል ፡፡
See also  “ከኛ ጋር ታስረው የነበሩ እስረኞች ተፈተው እኛ የምንታሰርበት ምክንያት የለም“

በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ አቤቱታን በመቀበል߹ ምርመራን በማጣራት እና ክስ በማቅረብ የህግ የበላይነት እንዲከበር መስራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከላይ በተጠቀሱት ወንጀሎች ጉዳይ ደግሞ የአታላይነት ድርጊቱ ፈፃሚዎች የመጨረሻ ግብ የሆነው የግለሰቦችን ገንዘብ በተለያየ መንገድ አታሎ የመውሰድ ተግባር ፍፃሜው ውጤታማ እንዳይሆን ለማስቻል ማህበረሰቡና ተቋማት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል ካላቸው ነጥቦች በጥቂቱ ፦
• ገንዘብ ገቢ ከማድረግዎ ወይም ከማስተላለፍዎ በፊት እርስዎ የፈለጉት ትክክለኛው ተጠቃሚ መሆኑን ማረጋገጥ߹ለማያውቁት ማንኛውም ግለሰብ አለማስተላለፍ߹አንዴ ካስተላለፉም በድጋሚ እንዲያስገቡ ለሚቀርብልዎት ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ለሕግ አስከባሪ አካል ጥቆማ መስጠት።
• ከባንክ የተደረጉ ጥሪዎችን ከትክክለኛው ባንክ መሆኑን ማረጋገጥ ወይም የተፈለጉበትን የማጣሪያ ጉዳይ በአካል በባንኮች በመገኘት ማስተካከል።
• በስልክ መልዕክት የገቡ የማህበራዊ ሚዲያ ማረጋገጫ ኮድ ጠያቂዎች ሲኖሩ ምላሽ አለመስጠት።
• የማህበራዊ ሚዲያ ግብይቶች ላይ ከክፍያ ወይም ከዕቃ ርክክብ በፊት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ።
• ተቋማትም አገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ እየተከተሉት ያለውን አሰራር እንዲሁም ደንበኞች ሊውስዱት ስለሚገባው የጥንቃቄ እርምጃ ለደንበኞቻቸው ማሳወቅ߹ የደንበኞቻቸውን ሚስጥር በሥራ ምክንያት ሊያውቁ የሚችሉ ሰራተኞቻቸው በጥብቅ ዲሲፒሊን እንዲመሩ ማድረግ።
• በቅርቡ የተጀመረው እና እየተሰራበት ያለው ባንኮች የደንበኞቻቸውን ማንነት በማጣራት መረጃ የመያዝ ሂደት ለህግ ማስከበር ጭምር ጠቃሚ ስለሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል ።

ቅንብር በወንድም ሰማህኝ

Leave a Reply