መንግስት ትህነግ በሰላም ስም መዋሸቱን አስታወቀ፤ አፋሮች እየተዋጋን ነው አሉ

ፎቶ- በኢሬብቲ መስጂድ ላይ የደረሰ ጥቃት መሆኑ ተጠቅሶ የቀረበ

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ) የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ቀደሞ ታጣቂዎቹ በሃይል ከወረሩት ኢሬብቲ ከተማና አካባቢው ለቀው መውጣታቸውን ቢገልጽም በተግባር ግን ስህተት እንደሆነና የአፋር ሃይሎች የተጠናከረ ጥቃት በማድረግ እየመከቱ እንደሆነ ተሰማ። የክልሉ ተጎጂዎች ስቃይና ረሃብ ዓለም ዘንግቶታል የሚል ከፍተኛ የሚዲያ ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።

የፌደራል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ደኤታ ከበደ ዲሳሳ ለጀርመን ድምጽ እንዳሉት ሕወሓት አሁንም አፋር ክልል ዉስጥ 6 ወረዳዎችን እንደተቆጣጠረ መሆኑን አመልክተዋል።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ቀደም ሲል ጀምሮ ትህነግን እንደማያምን አመልክቶ መንግስት የወሰደውን የሰላም አማራጭ ቢደግፍም የአፋር ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ግፍና እየተፈጸመ ስላለው ሁሉ ጥንቃቄ እንዲወሰድ ጠይቆ እንደነበር ይታወሳል።

መንግስት ለሰላምና ለዕርዳታ ማስተላለፍ ሲባል ግጭት ማቆሙን በይፋ ሲያውጅ የትህነግ ሃይሎች ከወረሩት አካባቢ ሁሉ እንዲለቁ አሳስቦ ነበር። ይህንኑ ተከትሎ ከትናንት በስቲያ ትህነግ ኤረብቲን ለቆ መውጣቱን አስታውቆ ነበር። የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አዲስ አበባ ከመግባታቸው ሰዓታት በፊት ትህነግ ይፋ ያደረገው መግለጫ ሃሰት መሆኑንን መንግስት ብቻ ሳይሆን የአፋር አክቲቪስቶችም አመልክተዋል።

በኪልበቲ ረሱ ዞን በህወሓት ቁጥጥር ሥር ገብተዋል ተብለው ከነበሩት 5 ወረዳዎች መካከል አብአላ፣ መጋሌ፣ ኤሬብቲና በራህሌን ይካተታሉ። እነዚህ ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ከትህነግ ወራሪ ሃይል እንዳልጸዱ የሚያመለክቱት አክቲቪስቶች ” አልሃምዱሊላህ በዚህ በተባረከ ወር በአላህ እዝነት እና ፍቃድ የአፋር ህዝባዊ ሃይል የህወሀትን ሰራዊት ከኤረብቲ ከተማና አከባቢዋ ማስለቀቅ ችሏል። ነገር ግን የህወሓት ሃይሎች አሁንም በወረዳው አንዳንድ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ” እነዚህ አካሎች እንደሚሉትና በምስል አስደግፈው ባሰራጩት መረጃ በአፋር ቀውሱ፣ ረሃቡና ስደቱ ” መንግስት ሆይ የት ነህ” የሚያሰኝ ነው።

መንግስት “የተሳሳተ” ሲል ባስታወቀበት የጀርመን ድምጽ ዜና ሰፊ ማብራሪያ ባይቀርብም ዓለም ዓቀፍ ታዛቢዎችም የትህነግ ሃይሎች እንዳሉት ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ አልወጡም።

የአፋር ሃይል አሁን ላይ ራሱን አደራጅቶና ገዢ ስፍራዎችን ይዞ አካባቢውን በሃይል እያስለቀቀ መሆኑንን የሚገልጹ መረጃዎችም እየወጡ ነው። ትህነግ ለትግራይ ህዝብ በትግርኛ ቋንቋ አስቀድሞ ከአፋር መልቀቁን፣ ይህንንም ያደረገው ለሰላምና እርዳታ ያለገደብ እንዲገባ ለማስቻል እንደሆነ ከማስታወቁ ሌላ “ውሸታም ነህ” የሚል ክስ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

የአፋር ሕዝብ ለምንና በምን መነሻ በትህነግ እንደሚመታ ምክንያት አጥጋቢ ምላሽ መስጠት ባይቻልም፣ ትህነግ አምስት ወረዳ በመውረሩ የትግራይ ህዝብም ያገኘው ጥቅም እንደሌለ እየተገለጸ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ትህነግ ለትግራይ ህዝብ ተጨማሪ ጠላትና ቅርሾ ከማከማቸት የዘለለ አፋርን ወሮ ምንም አያተርፍም። አሁን ከያዘው ቦታ መግፋትም አይችልም።

ከሃያ አራት ሰዓት በፊት የአፋር አክቲቪስትና ቅርብ ሰዎች በቲውተር ” በአፋር ህዝባዊ ሃይል እና በትህነግ ሃይሎች መካከል ለአጭር ጊዜ ከባድ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ አካባቢውን ማስለቀቃቸውን አምለክተዋል። በተለቀቁት አካባቢዎች መሰረተ ልማት መውደሙንና ንጽሃን ላይ አስከፊ ጥቃት መሰንዘሩንም አመልክተዋል። ይህንን ቢሉም ዛሬ አረፋፋዱ ላይ ” የአፋር ጂኖሳይድ ይቁም” በሚሉ ባነሮች ስር አሁንም የትህነግ ወራሪ ሃይል ጥቃት እየሰነዘረ መሆኑንን አመላካች ሆነዋል። ይህ እስከታተመ ድረስ ትህነግ ያለው ነገር የለም።

ከሰብአዊ ቀውሱ በተጨማሪ ” በአፋር ክልል በሶስት ዞኖች በተሰበሰበ መረጃ በትራንስፖርት አገልግሎት መሰጫ ተቋማትና መሰረተ ልማት ላይ በድምሩ 406 ሚሊየን 069 ሺህ 625 ብር የሚገመት ንብረት መድሟል፣ የተቀረውም ተዘርፏል” ሲል በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተደረገ ጥናት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በተመሳሳይ በአፋር ክልል ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ደራሽ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ዛሬ አስታውቋል።

የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዛሬ እንደገለጹት፤ በክልሉ ከሚገኙ 21 ወረዳዎች ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ደራሽ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ወረራ ምክንያት ከ645 ሺህ በላይ ዜጎች ከትውልድ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል።

በክልሉ ለጉዳት ከተጋለጡት አንዱ በሆነው ኪልባቲ ዞን ሁለት ሥር የሚገኙ ስድስት ወረዳዎች አባአላ፣ መጋሌ፣ ኮነቫ፣ ዳሎል፣ ኢረብቲ እና በርሃሌ በወረራው ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሉት ኃላፊው በተለይም አባአላ እና ኢረብቲ ወረዳዎች አልፎ አልፎ የሚነሱ ግጭቶች ለተፈናቃይ ወገኖች እርዳታ በበቂ ሁኔታ ማድረስ እንዳልተቻለም ገልጸዋል።

በንብረት፣ በሰዎች ህይወት እንዲሁም በአጠቃላይ መፈናቀል አፋር ይህን ያህል ጉዳት ቢደርስበትም አምነስቲም ሆነ ሂውማን ራይትስ ዎች በሪፖርታቸው አለማካተታቸው አስተዛዛቢ መሆኑንን ታዛቢዎችና ለህሊናቸው ያደሩ እየሞገቱ ነው።

ከአፋር የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመልክቱት አሁን ላይ የአፋር ልዩ ሃይል በካባድ መሳሪያ ታግዞ በትህነግ ሃይሎች ላይ ማጥቃት እያካሄደ ነው። ከትህነግ በኩል የተባለ ተጨማሪ መረጃ የለም።

አሜሪካ አዲስ የሰየመቻቸው የምስራቅ አፍሪቃ ልዩ መልዕክተኛ የትህነግ ሃይል በሃይል የያዛቸውን አካባቢዎች በሙሉ ለቆ እንዲወጣ ያስገድዳሉ ወይም ያዛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እየገለጹ ነው።

Leave a Reply