ከ12 ሰዎች በላይ የመጫን አቅም ያላቸውና ጂፒኤስ ያስገጠሙ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ባወጡባቸው አካባቢ በሚመጣው የመረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) መሠረት የነዳጅ ድጎማው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የነዳጅ ድጎማውን ለማግኘት እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም እያንዳንዱ ተሽከርካሪ ጂፒኤስ ማስገጠም እንደሚኖርበት ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት አቶ አረጋዊ ማሩ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የነዳጅ ድጎማው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ያስችላል። ድጎማውም ከሐምሌ አንድ 2014ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል።
በድጎማ ሥርዓቱ ተሽከርካሪዎች ጂፒኤስ ማስገጠም የመጀመሪያው መስፈርት መሆኑን የገለጹት አቶ አረጋዊ፤ ይህም የትራንስፖርት ስምሪቱን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ቁጥጥሩን ለማሳለጥ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
እንደ አቶ አረጋዊ ገለጻ፤ በአዲስ አበባ ነባራዊ ሁኔታ የሰሌዳ ቁጥር ያላቸው፤ 12 ሰዎችንና ከዚያ በላይ የመጫን አቅም ያላቸው ኮድ አንድ ብዙኃን ትራንስፖርት የነዳጅ ድጎማው ተጠቃሚዎች ናቸው። እንዲሁም ኮድ ሦስት የሆኑና ጂፒኤስ የተገጠመላቸው ከ12 ሰዎች በላይ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማው በቀጥታ ይመለከታቸዋል።
ከሌሎች ክልሎች ሰሌዳ አውጥተው በከተማዋ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የሚስተናገዱት ሰሌዳው በወጣበት ክልል ትራንስፖርት ቢሮ በኩል ሆኖ ለክልሉ መንገድና ትራንስፖርት እንዲሁም ለትራንስፖርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።ይህን ሲያደርጉ የድጎማ ተጠቃሚነት ኩፖን በማውጣት አገልግሎቱን የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ድጋፍ እየሰጡ የሚገኙ ኦሮ ኮድ-3 ድጋፍ ሰጪ ተሽከርካሪዎች ሰሌዳቸውን ያወጡት ኦሮሚያ ሆኖ እያለ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በአዲስ አበባ ቢሰጡም የድጎማ ኩፖኑን የሚያገኙት በኦሮሚያ ክልል በኩል መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ አገልግሎቱን ሲሰጡ ያንን ኩፖን ይዘው የሚሠሩበት አሠራር እንደሚኖር ይጠበቃል ያሉት አቶ አረጋዊ፤ ከድጎማው ጋር የተያያዙ መረጃዎች ተፈጻሚ የሚሆኑት በመጡበት ክልል እና አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል።
የነዳጅ ድጎማው ከ12 ሰዎች በታች የሚጭኑ ባጃጆችን፣ ላዳዎችን፣ ሜትር ታክሲዎችን፣ እንዲሁም በመተግበሪያዎች ተጠቅመው አገልግሎት የሚሰጡ ራይድ፣ ፈረስና የመሳሰሉ ተሽከርካሪዎችን አይመለከትም ብለዋል።
እንደ አቶ አረጋዊ አገላለጽ፤ እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ድረስ በኢትዮጵያ ያለው የተሽከርካሪዎች አጠቃላይ መረጃ ወደ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የመረጃ ቋት እንዲገባ ይደረጋል። ከዚያ በኋላ እስከ ሚያዝያ 30 ሁሉም ተሽከርካሪዎች የተመለከተው የመረጃ ቋት ሥራ ተጠናቅቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ ዝግጁ ይሆናል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው መመሪያ መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚደገው መመሪያው በከተማና በመላው ኢትዮጵያ ያለውን የተሽከርካሪ ቁጥር ለማወቅ የሚያስችል ምዝገባ ይካሄዳል፣ እንዲሁም የጂፒኤስ ገጠማ እና ተሽከርካሪዎችን የሚመለከት ማንኛውንም መረጃ ወደ ዳታ ቤዝ የማስገባት ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል።
በኃይሉ አበራ አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2014
https://www.press.et/?p=70839