አስመስሎ በመፈረም ከ12 ሚሊየን ብር የዘረፉ ተከሰሱ


የባለቤቱን ፊርማ አስመስለው በመፈረም ከ12 ሚሊየን ብር በላይ ወጪና ገቢ በማድረግ መንግስታዊ ሰነዶችን በሀሰት አስመስሎ በማዘጋጀትና በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል በፈፀሙ ተከሳሾች ላይ ክስ ተመስርቷል።

ተከሳሾቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዋሽ 7 ቅርንጫፍ ደንበኛ በሆኑት መዲና ሔንኬብ የውሃ ስራዎች ድርጅት ከተንቀሳቃሽ ሂሳብ ቁጥራቸው ላይ የሂሳቡ ባለቤቱ ቼክ ፈርመው ባልሰጡበት የባለቤቱን ፊርማ አስመስለው በመፈረም ከ12 ሚሊየን ብር በላይ ወጪና ገቢ አድርገዋል።

በተጨማሪም ሀሰተኛ ቼኮችን በማቅረብ የወሰዱትን ገንዘብ ለመደበቅና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ የሞባይል ባንኪንግን ተጠቅመው በተለያዩ ግለሰቦች ወደተከፈተ አካውንት ያስተላለፉ በመሆኑ ተከሳሾች በፈፀሙት መንግስታዊ ሰነዶችን በሀሰት አስመስሎ ማዘጋጀትና በሀሰት ሰነድ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

ተከሳሽ ሹክረዲን ሙሃመድ፣ ሳሙዔል ዳምጤ እና መሳይ ታደሰ የተባሉ ግለሰቦች የሙስና ወንጀል ለመደንገግ የወጣውን አንቀፅ 23 /1/ለ እና 2/ሀ/ ߹ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 /1/ሀ/ እንዲሁም በወንጀል የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 29/1/ሀ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፋቸው ክስ የተመሰረተባቸው።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ቸሎት በህግ ጥላ ስር ላለው 1ኛ ተከሳሽ የክስ ቻርጁ አንዲደርሰው ተደርጎ የክስ መቃወሚያ ካለውና ያልተያዙት 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሽን ደግሞ ፖሊስ አፈላልጎ አንዲያቀርብ ለሚያዝያ 10/2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን የፍትህ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ጠቅሶ ኢፕድ አስታውቋል።

Leave a Reply