የስንዴ ምርት በመጪዎቹ ሁለትና ሶስት ዓመታት ወደ ውጭ መላክ እንደሚጅመር ተገለጸ። በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለከፍተኛ የጦር መኮንኖቻቸው የስራ መመሪያ ሲሰጡ ነበር ይህን ያሉት። በዛው ንግግራቸው “ሌባ፣ አጭበርባሪ” ያሉዋቸውን ካድሬዎች ተጠየፏቸው ሲሉ አተንክረው አሳስበዋል። መክረዋል። ተማጽነዋል።

በሚቀጥሉት አስር አመታት ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ያላት፣ የምግብ ዋስትናዋን ያረጋገጠች ፣ ምግብ የምትሸጥ እንጂ የማትለምን ሀገር ማድረግ እንደሚቻል ለጦር መኮንኖቻቸው ሲያስታውቁ ሃያ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ መመረቱን ጠቁመዋል። በቀጣይ በአገሪቱ በሺህ የሚቆጠሩ አነስተኛ ግድቦች እንደሚሰሩ አመልክተው በምግብ ራስን መቻል ለነገ የሚባል እንዳልሆነ ለከፍተኛ የጦር መኮንኖቻቸው አስረግጠው ነገረዋል።

ሰፌ የሚታረስ መሬት፣ ውሃና ሰፊ የሰው ሃይል ያላት ኢትዮጵያ ይህንን ሃብቷን አዋህዳ ከልመና እንደምትወጣ በርግጠኛነት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ስኬት ጀርባ የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ግንባር ቀደም ሊሆን እንደሚገባው ገልጸዋል።

ዛሬ በአምራ ክልል ጉብኝት ካደረጉ በሁዋላ፣ “በአማራ ክልል የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ከፍተኛ ጥረት አደንቃለሁ። በመላዉ ክልል ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ ሲያለሙ በሰሜን ሸዋ ዞን ብቻ ከ2 ሺህ 800 ሄክታር በላይ ለምቷል። ምርታማነቱ አበረታች ነው። በክላስተር የግብርና አካሄዳችን በአንድነት የምግብ ዋስትናና የሀገር ልማትን እንደምናሳካ ማሳያ ነው” ሲሉ በማህበራዊ ገጻቸው አስፍረዋል።

ከከፍተኛ የአገሪቱ የጦር መሪዎች ጋር የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ” የዘር ጠርሙስ ውስጥ እንዳትገቡ” ሲሉ ምክር ሲለገሱ ” ተመልሳችሁ የዘር ብልቃጥ ውስጥ ከገባችሁ ከትህነግ ጋር መዋጋቱ አስፈላጊ አልነበረም” ሲሉ በብሄር ተለይቶ የመከላከያ ሃይል ላይ የተፈጸመውን ዘርን መሰረት ያደረገ ክህደት አስታውሰዋቸዋል።

የጦር ልብስ ተላብሰው አመራሮቻቸውን የሰበሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር ዐቢይ “ሌባ ካድሬ ዘርፎ ሲያበቃ ይመጣና በብሄር ስም እናንተ ጋር ይቀረቀራል” ካሉ በሁዋላ ” ሌባ፣ አጭበርባሪና በችግር ጊዜ የሚሸሽ” ሲሉ የጠሩትን ካድሬ አምርረው በማውገዝ የመከላከያ ሃይላት እንዲጠየፏቸው አሳስበዋል።

የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ ለጀነራል መኮንኖቹ የሥራ መመሪያ ዋና ሲሰጡ ህዝብ እንዲሰማ ተደርጓል። ለህዝብ ይፋ በሆነው በዚህ ቪዲዮ “የራዕያችን መንገደኛ እንጂ የችግርቻችን እስርኛ መሆን የለብንም ” ሲሉ ሁሉም ከተቀመጠው ግብ ለመድረስ ኢትዮጵያዊ መንፈስ ተላብሶ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የተጀመረው ለውጥ በስርዓትና በጥንቃቄ ካልተመራ ልማትና አገራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያጠፋ አመልክተው “የሰዎች ችግርና ድካማቸው ግን ግን የማይቀረውን ለውጥ ተገንዝቦ አብሮ ለመሄድ አለመቻላቸው ነው” ሲሉ ለውጡን አስቀጥሎ አንድ ታላቅ አገር መገንባት አማራጭ ሳይሆን ግድ እንደሆነ አሳስበዋል።

ጠንካራ አገር፣ የደረጀ መከላከያ፣ የተስተካከለ ኢኮኖሚ ያለው አገር በዲፕሎማሲ እንደሚያሸንፍ ያመለከቱት አብይ አሕመድ፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮችን “ሌባና አጭበርባሪ” ካሉዋቸው ካድሬዎች ጋር ሲመዛዝኑ ” አለመታደል ሆኖ እንጂ” ብለው ነው የጀመሩት። ግንባራቸውን ከስክሰው አገር ነጻ ያወጣው፣ የተጣሉትን አወያይተው ለሰላም የሰሩ፣ ውሃ በቦቴ እያመላለሱ ያጠጡ፣ የመከላከያ ሰራዊት መሆኑንን ጠቁመዋል። ቀጥለውም በጭግር ጊዜ የሸሸ ካድሬ ዛሬ ግምጋሚ መሆኑንን በመጠቆም የመከላከያ አመራሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑንን አመልክተዋል።

“ወታደር የሀገር የመጨረሻ መሸሸጊያ እንጂ የብልፅግንና ፓርቲ አገልጋይ አይደለም፤ መከላከያ ሰራዊት ሀገር በተለያዩ ፈተናዎቸ ውስጥ በነበረችበት ወቅት መስዋእት ሲከፍል የነበረ የኢትዮጵያ ዘብ ነው ” ሲሉ በገሃድ መከላከያ ሰራዊትን አግነዋል። አያይዘውም “ወታደር በሰላም ጊዜ የሚያደርገው ዝግጅት በችግር ወቅት ውጤታማ እንዲሆን ያደርገዋል” ሲሉ መዘናጋት ሊኖር እንደማይገባ ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያ ዘመናዊ አድረጃጀት ያለው ታላቅ የመከላከያ ሃይል እንድትገነባ ፍላጎት እንዳላቸውና በዚሁ ረገድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ሰፊ ስራ እንዲሰራ ማድረጋቸው ይታወቃል። በቅርቡም ተመናምኖና እንዲፈርስ ተፈርዶበት የነበረውን ተቋም በማቃናት የማያንስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት እንደተገነባ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይናጋራሉ።

ሰራዊቱ በዘመናዊ መሳሪያና ቴክኖሎጂ የሚታገዝ፣ ለአዳዲስ ግንኝቶች ክፍት የሆነ እንዲሆን ተደርጎ መሰራቱንና በወታደራዊ ክህሎት ዘመናዊ ትምህርት የሚከታተሉ በሺህ የሚቆጠሩ ባለሙያ መኮንኖች እየተዘጋጁ እንደሆነም ታውቋል።


Leave a Reply