በኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የመጋዝን ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ ድንገት በተደረገ ፍተሻ የዋጋ ግምታቸው ከ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ በሀገር ውስጥ በቀላሉ የማይገኙና አጅግ ውድ የሆኑ መድሐኒቶች ጎድለት የተገኙበት ግለሰብ በፅኑ እስራና በገንዘብ ቅጣት አንዲቀጣ ተወሰነበት።

ሚካዔል ዘውገ ተሰማ የተባለው ተከሳሽ የሙስና ወንጀል ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ በመተላለፉ ነው በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ክስ የተመሰረተበት ።

የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት ነው ።
ተከሳሹ በኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ውስጥ የመጋዝን ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ ታህሰስ 06/2014 ዓ.ም ከቀኑ 3፡00 ሰዓት ላይ በተደረገበት ድንገተኛ ኦዲት ወይም ፍተሻና ቆጠራ ሲካሄድ ከተረከበው መድሐኒት ውስጥ ለኩላሊት እና ለሾተላይ ህክምና አገልግሎት የሚውሉ የዋጋ ግምታቸው 5‚643‚997‚35 ( አምስት ሚሊየን ስድት መቶ አርባ ሶስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሰባት ብር ከሰላሳ አምስት ሳንቲም ) የሚያወጡ Anti-Rho(D) Immune Globvilin 300 Mcg in 2ml vital injection የተባሉ መድሐኒቶችን አጉድሎ በመገኘቱ በፈፀመው ከባድ የአምነት ማጉደል ወንጀል ነው በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ክስ የተመሰረተበት ።ተከሳሽ በችሎት ቀርቦ ክሱ ደርሶትና ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ” እኔ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም ”ሲል ቃሉን ሰጥቷል ።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ዝርዝር ሰባት የምስክሮች ቃል እና የሰነድ ማስረጃዎች በማቅረብ በበቂ ሁኔታ ለችሎቱ በማስረዳቱ ተከሳሽ ዐቃቤ ህግ ያቀረበበትን ክስ መከላከልና ማስተባበል ባለመቻሉ ግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል ።

በዚህም መሰረት ተከሳሽ ከዚህ በፊት የጥፋተኝነት ሪከርድ የሌለበት ߹የቤተሰብ አስተዳዳሪ ߹ የጤና እክል ያለበት መሆኑ በማስረጃዎች የተረጋገጠ ስለሆነ አራት የቅጣት ማቅለያዎች ተይዘውለት በ8 ዓመት ፅኑ እስራትና በ15 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኖበታል ።

ከዚህ በተጨማሪ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ጄነራል በተቋም ላይ ሌሎች መሰል ወንጀሎች ተፈፅመው ከሆነና አንዳይፈፀሙ በማሰብ ከኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑ ታውቋል ።

Leave a Reply