ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ – ኤሌክትሪክ ለማሰራጨት ርዥም ጊዜ ይፈጃል

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ነዋሪዎች የመብራት ያለህ እያሉ ነው። አገለግሎቱን ካጡም ድፍን ኃይል አንድ ዓመት በላይ ሆኗል። የአማራ ክልል ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች ነን የሚሉ የችግሩን ምንጭ ከመግለጽ ይልቅ መንግስትን ሲተቹና ሲያወግዙ ይሰማል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ባለስልጣን እንቅጩን ተናግሯል።

ዋናው ምክንያት ለካባቢዎቹ ሃይል የሚያቀረበው ማስተላለፊያ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ሃይል በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ውስጥ መሆናቸው ነው። በዚህ ምክንያት ነው ተቋሙ “እትጨቅጭቁኝ” በሚል ይመስላል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አካባቢ ኤሌክትሪክ በአጭር ጊዜ እንዲያገኝ ለማድረግ መቸገሩን ያስታወቀው።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ ገልጾ አላይን እንዳለው በትህነግ አዋኪነት ሳቢይ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ኃይል ከተቋረጠ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። በተመሳሳይ የላሊበላና የዋግ ኽምራ ዞን በርካታ አካባቢዎችም ለወራት የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ አለመሆኑንን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

እንደ አቶ አሸብር ገለፃ የላሊበላ፣ ሰቆጣ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ሰቲት ሑመራ አካባቢዎች ኃይል ያገኙ የነበሩት በትሀነግ ሃይሎች በተያዙ አካባቢዎች ከሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከተዘረጉ መሥመሮች ነበር። በዚህ የተነሳ የተቋረጡትን መሥመሮች ለመጠገንና አካባቢዎቹ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ ተቋሙ መቸገሩን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለአላይን አስታውቀዋል።

ለላሊበላና አካባቢው ሌሎች አማራጮችን እየታዩ በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ሊፈቱ እንደሚችሉ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ለወልቃይት ጠገዴ አካባቢ መፍትሔ ለመስጠት ከጎንደር ወይም ከመተማ ኃይል መዘርጋት ግድ ስለሚል ረጅም ጊዜ እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል።

በወልቃይት ጠገዴን ያለው ችግር ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ከዓመት በላይ የቆየው በአካባቢው አማራጭ መስመር ባለመኖሩና የአዲስ መስመር ዝርጋታው ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅና ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ይሁንና በአጭር ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት የክልሉ መንግስት፣ የፌደራል መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሊሳተፉበት እንደሚገባ አቶ አሸብር ጠቁመዋል። የአጭር ጊዜ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ኦፍ ግሪድ የሆኑ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ እንደሆነ አሳስበዋል።

እንግዲህ የአማራ ክልል ያገባኛል ባዮች ይህን ሁሉ ችግር ተሸክመው ነው እርስ በርስ ወደ መጠፋፋትና መተራመስ ለማምራት የውክልና፣ የተላላኪነት፣ ከዚህም በላይ የስልጣን ጥም ሽኩቻ ውስጥ የገቡት ሲሉ ገለልተኛ ወገኖች የሚወቅሱት። ስልጣን ላይ ያሉትንም ሆነ ተቃዋሚ ነን የሚሉት ቅኔና አሽሙር አቁመው በራቸውን ዘገተው ከመምከር ይልቅ ሕዝቡን ለመከራና ለዳግም አደጋ በሚያጋልጥ አዙሪት ውስጥ መገኘታቸው እጅግ እንደሚያሳዝን ሰሞኑንን በተካሄዱ መድረኮች ከሕዝብ መነሳቱን የክልሉ ሚዲያ መዘገቡ ይታወሳል።

Leave a Reply