አማራ ረሳ?

– በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ በአስመሳይና ተላላኪዎች ላይ አደብ የሚያስገዛ እርምጃ እንዲወሰደ ሕዝብ እየተየቀ ነው

የአማራ ክልል አልዳነም። የአማራ ክልል ብዙ ፈተናዎች አሉበት። የአምራ ክልል ወድሟል። የአማራ ሕዝብ የሚፎክርበትና እርስ በርስ የሚጋጭበት ወቅት አይደለም።ፋኖ ለመከላከያ ደጀን ነው። መከላከያም ለፋኖ እንደዛው። አማራ የጅምላ መቃብሮቹን ለቅሞና ልጆቹን በክብር ሳያሳርፍ በዚህ መልኩ እንዲተራመስ የሚሰሩ እንግዴዎች ናቸው። ዛሬ በአማራ ክልል ለስልጣንና ለግል ኪስ ማሰብ ውርደት ነው። ገና ዓመት ያልሞላው ያ ሁሉ የግፍ ዓይነት እንዴት ይረሳል?

አማራ ክልልን ለመናጥ የፋኖን ስምና አደረጃጀት ተገን አድርገው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሃይሎችንና አስመሳይ “አማራ ነን” ባዮችን ያሳፈረ ተግባር መፈጸሙን ያዩ “ርብርቡ ከሸፈ” ነው ያሉት። አሁን ከክልሉ እንደሚሰማው በፋኖ ስም የሚነገዱና እውነተኛውን ፋኖ ለራሳቸው የተላላኪነት ፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ እየሰሩ ያሉት ተለይተው ህጋዊ ገደብ እንደሚበጅላቸው ነው። “አማራ ረሳ?” የሚሉ በቁጭት በሚሰሙትና በሚያዩት ልባቸው መድማቱን ይገልጻሉ።

በየትኛውም መድረክና አግባብ ከፋኖ ጋር ግንኙነት ያልነበራቸውና በአቋራጭ በተላላኪነት ክልሉን ለማተራመስ ሃይል እያደራጁ “የፋኖ ወኪል ነን” በሚሉት ላይ ሕዝብ እርምጃ እንዲወሰድ በየአካብቢው ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል። አርበኝነትና ፋኖነትን ማንም ሊያጠቃውና ሊገፋ የሚችል ጉዳይ እንዳልሆነ ክልሉ ግልጽ አቋም መያዙን ካስታወቀ በሁዋላና ከአርበኛ የፋኖ ወኪሎች ጋር ውይይት ካደረገ በሁዋላ ” የንግዴ ልጅ” የተባሉት ላይ ሀጋዊ አደብ እንዲበጅላቸው ከስምምነት መደረሱ ተሰምቷል።

የክልሉ መንግስት “እሸልማለሁ፣ እውቅና እሰጣለሁ። እረዳለሁ” ሲል ለፋኖ ትክክለኛው አደረጃጀትና አባላት በአደባባይ ማረጋገጫ በመስጠት የአማራን ክልል ለማተራመስና የጠላት መሳቂያ ለማድረግ የሚሰሩትን ለመለየት በጋር ሲሰራ ነበር። ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ እንዳሉት በተላላኪነት የሚንቀሳቀሱ ” የከተማ አረቄ አንቃራሪዎችና በጀት የሚሰጡዋቸው ጥቂት ሃብታም ተብዬዎች ጉዳያቸው እያከተመ ነው” ብለዋል።

በየሚዲያው ብር እየረጩ ሴራ ተቀብለው የሚያራቡትን በዕዳ የተነከሩ ሃብታም ተብዬዎችና ጀሌዎችቸውን ክልሉ መታገስ የማይችልበት ደረጃ የደረሰው፣ ክልሉ ከደረሰበት ከፍተኛ ውድመትና ኪሳራ እንዲያገገም ሙሉ ትኩረቱን እዛው ላይ አድርጎ እንዳይሰራ አቅምና ጉልበቱን እየፈተኑት በመሆኑ ነው ተብሏል።

አማራ አንድ ሆኖ ችግሩን በጥበብ መፍታት ሲገባው በየስርቻው ሴራና መመሪያ እየተቀበሉ የሚያሰራጩትን የማምከን ስራ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ በሕዝባዊ ስብሰባዎች በገሃድ መጠየቁን በማስታወስ፣ ክልሉ ከልክ በላይ የታገሰውን መረን የወጣ እንቅስቃሴ በቅርቡ መላ እንደሚለው ምንጮች አስታውቀዋል። በተመሳሳይ በትክክል ችግር ያለባቸውን ሊታረሙ የሚገባቸውን ጉዳዮች በመመካከር አብሮ ያገባናል ከሚሉ እውነተኛ የክልሉ ተቆርቋሪዎች ጋር ለማከናወን ሃሳቡና ፍላጎቱም እንዳለ ተመልክቷል።

ከታች የቢቢሲን ዘገባ በወልደያ አካባቢ በፋኖና በመከላከያ መካከል ተነሳ ተብሎ በነበረው ግጭት የዘገበውን አስፈረናል። ለመሆኑ ይህ ግጭት ይፋ ከመሆኑ በፊት ከውስጥና ከውጭ ተናበው ጉዳዩን እንዴት ያራግቡት እንደነበር ለሚያስታወሱ ድርጊቱና የመናበብ ዘመቻ ለወደፊቱ ትልቅ ልምድ ይሆናቸዋል። ፓርላማ ሆነው አቅጣጫ ለሚሰጡት ባለቅኔ ጭምር።

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን፣ ወልዲያ ከተማና አካባቢዎቹ በመከላከያ እና በፋኖ መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት በእርቅ መፈታቱ ተገለጸ። የዞኑ የኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ ኃብተማርያም አሰፋ ትናንት ምሽት በወልዲያ ተከስቶ በነበረው ግጭት አንድ ታጣቂ እና አንድ ሰላማዊ ሰው ሕይወታቸው ማለፉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የዞኑ የጸጥታ ኃላፊ ኮሎኔል ኃይለማርያም አምባዬ በበኩላቸው ግጭቱ የተነሳው በመከላከያ እና ፋኖ መካከል “ኬላ ላይ ተፈተሹ፣ አልፈተሽም” በሚል ምክንያት መሆኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወልዲያ ከተማ ነዋሪ ትናንት ማታ ምሽት 1፡00 አካባቢ የከባድ መሳሪያ ተኩስ እንደነበር ገልፀው፣ በዚህም አንድ ሰላማዊ ሰው ሕይወታቸው ማለፉንና ዛሬ የቀብር ሥነ ስርዓታቸውን እንደፈፀሙ ተናግረዋል።

የዞኑ የጸጥታ ኃላፊ ኮሎኔል ኃይለማርያም በወቅቱ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር አረጋግጠው “መነሻው በፌስቡክ በሚናፈስ አሉባልታ ‘አንድ አመራር ታሰረብን’ በሚል ከሌላ ቦታ የመጡ ታጣቂዎች” ተኩሱን በመክፈታቸው የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ይኹን እንጂ ግጭቱን ብዙም ሳይቆይ ማስቆም ተችሏል ብለዋል።

ኃላፊው ትናንት ምሽት በወልዲያ ከተማ በነበረው የተኩስ ልውውጥም የተጎዱ ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጠው፣ ስለደረሰው ጉዳት ግን አጣርተው እንደሚገልጹ ተናግረዋል።

የዞኑ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃብተማርያም አሰፋ ” ‘መከላከያ፣ ልዩ ኃይልና ፋኖ ግጭት ፈጠሩ’ በሚል እኩይ ሥራ የሚሰሩ ይኖራሉ፤ የተፈጠረው ግን በአሰራር ክፍተት ነው” ብለዋል።

ትናንት በዞኑ ጎብዬ እና ሮቢት አካባቢ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኃብተማርያም “ግጭቱ የተፈጠረው በአካባቢው የነበረ የፋኖ መሪ ታስሯል በሚል እዚያ ያለው ፋኖ ሲመጣ መከላከያ ለማረጋጋት ሲሞክር ነበር” በማለት አስረድተዋል።

እንደ ኃላፊው ከሆነ በሁለቱ አካባቢዎች በነበረው ግጭት የደረሰ ጉዳት የለም።

ይኹን እንጂ ትናንት ምሽት በወልዲያ ተከስቶ በነበረው ግጭት አንድ ታጣቂ እና አንድ ሰላማዊ ሰው ሕይወታቸው ማለፉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወልዲያ ከተማ ነዋሪ እንደሚያስረዱት፣ “በከተማዋ ፋኖዎች የሚኖሩበት ህንጻ የተኩስ ምልልስ ነበር፤ የጉዳት መጠን አላየንም። አንድ ቄስ ሞተዋል በአካባቢው ሲያልፉ የነበሩ ናቸው ተብሏል፤ እርሳቸውን ቀብረናል” ብለዋል።

ይሰማ የነበረው የተኩስ ድምጽ ብዙም ሳይቆይ መቆሙን የገለጹት ነዋሪው የግጭቱ መንስኤ ግን ምን እንደሆነ በውል እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ዛሬ ወልዲያም፣ ሮቢትም፣ ጎብየም ሰላም መሆናቸውንና በአካባቢዎቹ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩንም ነዋሪው አክለዋል።

የኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ ኃብተማርያም ደግሞ “በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችንና ጠላትን ለመመከት እንዲሁም ተላላኪዎችን ለመለየት የተለያዩ አሰራሮች ተዘርግተዋል፤ ያንን ለማጥራት የተጀመሩ ስራዎች ስለነበሩ፤ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ ኃይሎች የራሳቸውን ሥራ ሰርተውበታል፤ ነገር ግን መከላከያ እና ፋኖ እንደተለያዩ ተደርጎ የሚወራው ፍፁም ሐሰት ነው” ብለዋል።

“ፋኖ ለመከላከያ ደጀን ነው። መከላከያም ለፋኖ በግብዓትም በሬሽንም ግብዓት የሚያቀርብ ነው” በማለትም የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት መፈታቱን ተናግረዋል።

Leave a Reply