«በትግራይ መንግሥት እርዳታ በትክክል ለተጠቃሚዎች እንደሚደርስ ይቆጣጠራል»

ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች በትግራይ ክልል የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን በተረጂዎች ዝርዝር መሠረት እንደሚያከፋፍሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። 

የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ ወደ ትግራይ ክልል ድጋፍ እያቀረቡ ያሉ ድርጅቶች መብትና ግዴታ ያላቸው ናቸው ። መብትና ግዴታቸው መሠረት አድርገውም ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በየብስ አጓጉዞ ትግራይ ክልል የማድረስና በተጠቃሚዎች ዝርዝር መሠረት ምግብ የማከፋፈል ሥራ ይሠራሉ።

በትግራይ ክልል ምግብ በማቅረብ ረገድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ ኬቬ ኢንተርናሽናል፣ ሲአር ኤስ፣ ወርልድ ቪዥንና የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሥራቸውን እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ዩኒሴፍ፣ የዓለም የጤና ድርጅትና መሰል ድጋፍ አድራጊ ተቋሞች ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን የሚያቀርቡ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውል ገብተው እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ድርጅቶች ለተጠቃሚዎች ያከፋፈሉትን ምግብም ይሁን ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ለኢትዮጵያ መንግሥት ሪፖርት እንደሚያደርጉ ኮሚሽነሩ አመልክተው፤ በሪፖርቱ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታው በትክክል ለተጠቃሚዎች እንደሚደርስ ይቆጣጠራል ብለዋል።

ረጂ ድርጅቶች እርዳታ የሚያደርጉት ገለልተኛ በመሆን፣ ባለማዳላትና መሰል ዓለም አቀፍ መርሆችን መሠረት አድርገው ኃላፊነቱን ሙሉ ለሙሉ ወስደው ይሠራሉ ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅት በሚፈለገው ልክ እርዳታ አቅርቦት የለም ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ትኩረታቸው በትግራይ ክልል ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የአፋርና የአማራ አካባቢዎች ተዘግተው መቆየታቸውን አውስተው፤ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ትኩረታቸውን በአማራና በአፋር ክልልም እንዲያደርጉ በተደረገው ጥረትም መሻሻሎች መኖራቸውን ገልጸዋል። 

አሁንም በሚፈለገውና በእርዳታ ፈላጊዎች ልክ ባይሆንም በአማራና በአፋር ክልል እርዳታ እየሰጡ መሆኑን ገልጸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ትኩረታው ወደ ዩክሬን በመሆኑ በኢትዮጵያ የሚደረገው ድጋፍ አመርቂ ነው ብሎ መናገር እንደማይቻል ገልጸዋል። 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፣ ባለፉት ሁለት ቀናት 47 የምግብ ድጋፍ የያዙ እና 3 ነዳጅ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች በድምሩ 50 የጭነት መኪኖች ከሰመራ ተነስተው ወደ መቀሌ ጉዞ እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል።

See also  ወረራ በተፈፀሙባቸው አካባቢዎች ከ1 ሺሕ በላይ የጤና ተቋማት መውደማቸው ተገለጸ

ተጨማሪ 10 የምግብ እርዳታን የያዙ የጭነት ተሽከርካሪዎችም ከሰመራ ጉዞ መጀመራቸውም ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም በየብስ ትራንስፖርት በመጀመሪያው ዙር የምግብ ድጋፍን የያዙ 21 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ መግባታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ የገባውን ቃል በማክበር ምቹ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማጓጓዣ ሁኔታን ለመፍጠር እየሠራ እንደሚገኝ ይታወቃል።

ሞገስ ጸጋዬ 

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014

Leave a Reply