አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች የቅጥፈት ሪፖርት ማውጣታቸውን በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች እይጋለጡ ነው

“አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች በወልቃይት ዙሪያ ያወጡት የጋራ ሪፖርት ፍጹም ሐሰት መሆኑን በቦታው ላይ ተገኝቼ ለማየት ችያለሁ ስትል” በቨርጂኒያ ግዛት የምትኖረው የፑሽ ስታርት ሚዲያ ጋዜጠኛ ቤቲ ተከስተ ከአሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን እንዲሁም አሜሪካዊው የፎቶ ጋዜጠኛ ጀማል ካውንተስ ጋር በመሆን ምስክርነቷን ሰጠች።

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጋዜጠኛ ቤቲ ተከስተ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የተገኙትን የጅምላ መቃብሮች መመልከቷንና አሁንም ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግራለች።

በቨርጂኒያ ግዛት የምትኖረው የፑሽ ስታርት ሚዲያ ጋዜጠኛ ቤቲ ተከስተ ከአሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን እንዲሁም አሜሪካዊው የፎቶ ጋዜጠኛ ጀማል ካውንተስ ጋር በመሆን በአማራ ክልል በጦርነቱ የደረሰውን የጉዳት መጠንና ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ለማየት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መጓዟን ገልጻለች።

አን ጋሪሰንና የፎቶ ጋዜጠኛ ጀማል ካውንተስ

በጉዟቸውም ‘በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያወጣው ሪፖርት አለ’ የሚል መረጃ ደርሷቸው ወደ ሥፍራው እንዳቀኑ ተናግራለች።

በአካባቢው የተገኙትን የጅምላ መቃብሮች በአካል እየተመለከቱ እንዲሁም ሕዝቡን እያናገሩ በነበሩበት ወቅት የአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች የጋራ ሪፖርት መውጣቱን አመልክታለች።

“በትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰ ጥቃት” በሚል ሐሳብ የወጣው ይህ ሪፖርት ቦታው ላይ ካየሁት ሁኔታ ጋር ፍጹም የተቃረነ ነው ብላለች ጋዜጠኛ ቤቲ።

ምዕራባውያን ጋዜጠኞችም በሥፍራው በመገኘት እውነታውን መመልከታቸውንና፤ ሁለቱ ተቋማት ያወጡት ሪፖርት ሐሰተኛ መሆኑን ማረጋገጣቸውን አብራርታለች።

በወልቃይትና አካባቢው የሚኖሩና የጥቃቱ ቀጥተኛ ሰለባ የሆኑ የአማራ ተወላጆች የደረሰባቸውን እሥራት፣ በደልና ስለ ጅምላ መቃብሮቹ ገለጻ እንዳደረጉላቸው አመልክታለች።

“ከአይን እማኞችና ግፉ ከተፈጸመባቸው ሰዎች መረጃ እየተቀበልን ባለንበት ሰዓት የጋራ ሪፖርቱ ይህ በደል በሌላ አካል ተፈጽሟል የሚል ነገር ማውጣቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰራጩ መረጃዎች ከእውነታ ፍጹም የራቁ መሆናቸውን ያሳያል” ብላለች።

የጅምላ መቃብሮቹን አስመልክቶ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ማብራሪያ እንዳገኙም ነው ጋዜጠኛ ቤቲ የገለጸችው።

ጥናቱ ባለመጠናቀቁ የጅምላ መቃብሮቹ ቁጥር ከዚህም በላይ እንደሚጨምርና ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደረግ ከጥናት ቡድኑ መረዳት መቻሏንም እንዲሁ።

See also  አማራ ክልል "የህግ ማስከበሩ ይቀጥላል"

የጅምላ መቃብሮቹን በተመለከተ የፎረንሲክ ምርመራን ጨምሮ ሌሎች ሳይንሳዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ዝርዝር ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመልክታለች።

“ከብዙ ዓመታት በፊት ግድያ የተፈጸመባቸው ዜጎች ታሪክ ዛሬ በሌላ አካል እንደተፈጸመ ተደርጎ ነው የሚወራው፤ አሁን ላይ የደረሰው ጉዳት ትክክለኛ መረጃና እውነት እየወጣ ይገኛል” ነው ያለችው ትውልደ- ኢትዮጵያዊቷ ጋዜጠኛ።

“እንደ ጋዜጠኛ ሁልጊዜም እውነትን መናገር አለብን” ያለችው ጋዜጠኛ ቤቲ፤ በወልቃይትና አካባቢው በነበራት ቆይታ የተፈጠረውን ትክክለኛ ነገር መረዳቷን ገልጻለች።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ቀጣይ ለሚያደርገው ጥናት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸውን ባለሙያዎችን በማገናኘት ድጋፍ እንደምታደርግም ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply