«በወልቃይት ጠገዴ ያልተነገረ ካልሆነ በስተቀር ያልተፈጸመ የግፍ አይነት የለም›› ኮ. ደመቀ

አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ በተለይም በወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ሕዝብ ላይ ሳይነገር የቆየ ካልሆነ በስተቀር የግፍና የጭካኔ አይነቶችን ሁሉ መፈፀሙን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ተናገሩ፡፡

ቡድኑ አንዱን ከፍ፤ ሌላውን ዝቅ በማድረግ የቅኝ ገዢዎችን የአገዛዝ ስርዓት ሲከተል እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

ኮሎኔል ደመቀ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ቃለምልልስ እንደገለፁት፣ ቡድኑ የውጭ ወራሪዎችን ተልዕኮና ማኒፌስቶ ይዞ ሲሰራ የመጣ ኃይል በመሆኑ ስልጣን ከያዘ በኋላ ህዝቡን በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት እና በአካባቢ እየከፋፈለ እርስ በእርሱ እንዲባላ ሲሰራ የኖረና አሁንም ያንኑ ካላስቀጠልኩ እያለ የሚዋጋ ኃይል ነው። ሕወሓት ኢትዮጵያን ለማጥፋት በቅድሚያ አማራን ማጥፋት ነው የሚል ትርክት በመያዝም በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ግፍና መከራ መፈጸሙንም ተናግረዋል።

ይህ ቡድን በይፋ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስም ቢሆን እንሄዳለን ያለ ኃይል ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ፤ ይህ ደግሞ ትልቁ የጥፋት ኃይል መሆኑን ምስክር እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሕወሓት የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላት የሆኑት የውጭ ኃይሎች ታዛዥና ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆኑም በዚህ ኃይል ነጮቹም ሲጠቀሙ ኖረዋል፣እየተጠቀሙም ናቸው ብለዋል ኮሎኔል ደመቀ፤ አሁንም በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለው ተጽዕኖ እና ጫና ይህን ለማስቀጠል ያለመ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የወልቃይት ሕዝብ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ከሕወሓት ጋር ሲዋጋ ነበር ያሉት ኮሎኔል ደመቀ፤ በወቅቱ በተለይ ታሪክ የሚያውቁ ትላልቅ የወልቃይት ሰዎችን በግፍ እንደጨፈጨፈና በወልቃይት ጠገዴ ቀዝቃዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀሙንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተገኙት የጅምላ መቃብሮች ምስክር መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በመሆኑም ሕወሓት ባለፉት አርባ ዓመታት የፈፀማቸውን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የዓለም ማህበረሰብ እና ሚዲያዎች በስፍራው በመገኘት ሊያዩት እና እውነታውን ሊረዱ ይገባል ብለዋል።

ኮሎኔል ደመቀ እንዳሉት፣ ባለፉት አርባ ዓመታት በርካታ የወልቃይት ሕዝብ ከቤቱ እንደወጣ ቀርቷል፤ ብዙዎቹ በእስር ቤት ተጉላልተዋል፤ ሌሎች ደግሞ ከፍተኛ ስቃይና መከራ ተቀብለዋል። የብዙዎቹ አስከሬንም የት እንደተቀበረ እንኳን አይታወቅም።

እንደ ኮሎኔል ደመቀ ገለጻ፤ ሕወሓት ማንም በማይገምተው ሁኔታ በአየር ማረፊያ ጭምር ሰዎችን በድብቅ በማገትና በጅምላ በመጨፍጨፍ ከፍተኛ ኢሰብዓዊ እና ዘግናኝ ተግባር ሲፈጽም ነበር:: በዚህም በሁመራ አየር ማረፊያ ብቻ ከ90 በላይ የጅምላ መቃብር ተገኝቷል።

ሕወሓት በወልቃይት ማህበረሰብ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ በመፈፀም እና አብዛኛውም እንዲሰደድ በማድረግ በምትኩ ቀደም ሲል ከደርግ ጋር ሲዋጉ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን አስፍሯል ያሉት ኮለኔል ደመቀ፤ የአካባቢውን የስነ ሕዝብ አሰፋፈር ስርዓት ለመለወጥም ስም እስከመቀየር ደርሷልም ብለዋል።

በወልቃይት የተፈፀመው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በከፍተኛ ተንኮልና በስውር የተፈፀመ በመሆኑ አብዛኛው ህዝብ ወጥቶ ከመቅረት ውጭ እንዴት እንደተገደለ፤ የት እንደተቀበረ እና መቼ እንደሞተ እንደማይታወቅም ጠቁመዋል:: በዚህ የተነሳ እስካሁን ድረስ በርካታ ሰዎች ልጆቻቸው፤ አልያም የተለያዩ የቤተሰብ አባላት የት እንደገቡ ሳያውቁና እርማቸውንም ሳያወጡ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።

በሌላ በኩል የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄዎችን ሲያነሳ መኖሩን የጠቆሙት ኮሎኔል ደመቀ፤ ለዚህ ጥያቄ ግን ምላሹ መገደልና መሰደድ ሆኖ ኖሯል ብለዋል:: በመሆኑም አሁንም መንግሥት ለጥያቄያቸው ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በተለይ የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከአሸባሪው ሕወሓት ነጻ ቢወጣም እስካሁን ድረስ በመንግሥት በጀት የማይመደብለት በመሆኑና በአካባቢውም ያለው መሰረተ ልማት በአሸባሪው ሕወሓት በመውደሙ በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ በችግር ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ የመብራት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ በመቋረጡ የህክምና አገልግሎትና ሌሎች የልማት ሥራዎች በከፍተኛ ሁኔታ መስተጓጎላቸውንና በዚህም ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳቶች እየደረሱ መሆኑን ኮሎኔል ደመቀ ተናግረዋል::

የውጭ ኃይሎችም ለሽብር ቡድኑ ድጋፍ እንዲደረግ እየጮሁ፤ ላለፉት አርባ ዓመታት መከራ የደረሰበትን የወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ሕዝብ ዝም ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑን ኮሎኔል ደመቀ ተናግረዋል።

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የወልቃይት ጠገዴ አማራ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ጉዳያቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ በ2007 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በሄዱበት ወቅት በወቅቱ በሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ተይዘው ከፍተኛ እንግልት የደረሰባቸው ሲሆን በ2008 ዓ.ም ደግሞ በጎንደር ከመኖሪያ ቤታቸው አፍነው ሊወስዷቸው ከመጡ የወያኔ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመፋለም ከፍተኛ ትግል ማድረጋቸው ይታወሳል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ጥናት እንዳመለከተው በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎች ሕወሓት በፈጸመው ግፍና መከራ የተነሳ ከእያንዳንዱ ቤተሰብ 26 ነጥብ 5 ከመቶ ለስደት ተዳርጓል፤ 19 ነጥብ 5 ከመቶ ታፍኖ የት እንደገባ አይታወቅም፣ እንዲሁም 29 ከመቶው ደግሞ ለሞት ተዳርጓል። መረጃው የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ነው።

Leave a Reply