በወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የተሰጠ መግለጫ

በወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

በወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የሰጠው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የደረሰችው በየዘመናቱ የገጠሟትን ፈተናዎች በድል እየተሻገረች ነው። እንድትጠፋ የሚፈልጉ ኃይሎች ሊያጠፏት ሲነሡ ምንጊዜም ሦስት ኃይሎችን እንደሚጠቀሙ እሙን ነው።

የመጀመሪያዎቹ ምንጊዜም የማይተኙት ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው። እነዚህ ጠላቶቻችን ጠላትነታቸውን የሚያቆሙት ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ከምድር ገጽ ስትጠፋ ብቻ ነው። ይኼ ምኞታቸው እንዲሳካ ብቻቸውን አይሠሩም። ተላላኪ አላቸው። እነዚህም ሁለተኛዎቹ ናቸው። ለገንዘብና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ወገናቸውን እንደ ይሁዳ የሚሸጡ፣ ሀገር የጣለባቸውን እምነት በሽርፍራፊ ሳንቲም የሚለውጡ ሀገር አልባ ባይተዋሮች ሞልተዋል። የተናገሩትን ሆነው የማይገኙ፣ ቀን ቀን በአደባባይ ስለ ሕዝብ ፍቅር እና ስለ ሀገር አንድነት የሚደሰኩሩ፤ ማታ ማታ ከጠላት ጋር እያሴሩ ወገንን የሚክዱና ሀገር ለማፍረስ ጉድጓድ የሚቆፍሩ ናቸው።

ሦስተኛዎቹ የኢትዮጰያ ጠላቶች ደግሞ ባለማወቅ የእነዚህ የሁለቱ አካላት ተባባሪ የሚሆኑት ናቸው። ግዴለሽ ስለሆኑ፣
የሚያደርጉት ነገር የሚያስከትለውን ውጤት ሳይገምቱ እንዲሁ በነሲብ የጠላትን ተልዕኮ የሚፈጽሙ ውል አልባ ኢትዮጵያውያን ናቸው። እነዚህ ኢትዮጵያውያን አንድን ነገር ተቀብለው ማውራታቸውን፤ ወይም አድርጉ የተባሉትን ነገር ማድረጋቸውን፤ ወይም ሳይመረምሩ የሰጧቸውን መረጃ ሁሉ ማስተላለፋቸውን እንጂ በሀገራቸውና በሕዝባቸው ላይ የሚያስከትለውን ጣጣ አይመረምሩትም። ከመረመሩም ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ ብቻ የሚፀፀቱ ናቸው።

ኢትዮጵያ ይበልጥ እየተፈተነች ያለችው በእነዚህ በሁለቱ ነው። ታሪካዊ ጠላቶቻችን በአንድ ስሙ ቁርጣቸው የታወቀ ጠላቶቻችን ናቸው። ባይተዋሮችና ውል አልባ ኢትዮጵያውያን ግን በወቅቱ ልብ ሳንላቸው ደጋግመው ዋጋ ያስከፍሉናል። በዚህ መልኩ እስከመቼ? ለዚህ ጥያቄ ሁላችንም ቆም ብለን ምላሽ ልንሰጥ ይገባል።

ለውጡ ከመጣ ጀምሮ እንኳን እንደ ሀገር በብዙ ተፈትነናል፤ የሰነቅነውን ተስፋ እንዳናይ የሚከልሉ ስንት ጋሬጣዎች ገጠሙን? ስንቱን ተሻገርን? በስንቱ ወደቅን? አንድ በአንድ ብንዘረዝረው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። እነዚህ ፈተናዎች የመጡት ከላይ ከተጠቀሱት የኢትዮጵያ ጠላቶች ነው። ለውጡ እንዳይሳካና ኢትዮጵያ ጠንካራ የአፍሪካ ኃይል ሆና እንዳትወጣ ለማድረግ ዐቅማቸው የፈቀደውን አድርገዋል። ኢትዮጵያውያን በዘር ተከፋፍለው እርስ በርስ እንዲጋጩ፣ ሀገር በኢኮኖሚ እንድትዳከም፣ ሀገር ተሸክመው የኖሩ ተቋሞቻችን እንዲፈራርሱ በብርቱ ሲሠሩ ነበር።

See also  ትህነግ ከትግራይ አስተዳደር ጋር መሳሪያ አስረክቦና ጦሩን በትኖ እንዲደራደር ታስቧል፤ መንግስ የተረፈውን ሃይል ሊያጸዳ ነው

ሚዲያና የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎችን በመጠቀም ማህበራዊ እሴቶቻችንን ለመበጣጠስ፣ የእምነትና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማቃጠል፣ በሕዝብ መካከል ሽብር ለመንዛትና ዜጎቻችንን ዕረፍት ለመንሣት ክፋት የተባሉትን ተግባራት ሁሉ ፈጽመዋል። የፈጸሙት እኩይ ሥራ እጅግ አሰቃቂና ዜጎቻችንን የጎዳ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያውያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ለሀገራቸው ባላቸው የጸና ፍቅር ምክንያት ጠላቶቻችን የሚፈልጉትን ግብ ሊያሳኩ አልቻሉም።

ከለውጡ በፊት ተቋማዊ ስብራት ከገጠማቸው መካከል የሕግና ጸጥታ ተቋማት ይገኙበታል። እነዚህ ተቋማት እንዲሰበሩ
የተደረጉት ሆን ተብሎ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ዓላማ ለማሳካት አንዲቻል ነው። በሀገር ውስጥ ሥልጣንና ሀብት ይዘው የነበሩት የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪዎች፣ የሕግና የጸጥታ ተቋማትን በሞትና በሕይወት መካከል እንዲኖሩ አድርገዋቸው ነበር። ከለውጡ በኋላ በእነዚህ ተቋማት ላይ በተሠራው ሥራ የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ ወደሚችሉበት ደረጃ ለማድረስ ተችሏል። እስከዛሬ ድረስ እነዚህን ተቋማት ለማጠናከርና ለዛሬ ችግሮች ምላሽ፣ ለነገ ፈተናዎች ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲባል፣ እያመመንም ቢሆን አያሌ ችግሮችን ተሸክመን ለማለፍ ተገደናል።

ዳሩ ግን ትዕግሥትም ልክና መጠን አለው። አሁን የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት በተሻለ ቁመና ላይ ስለሚገኙ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት ሁሉ ተመጣጣኝ ምላሽ ከመስጠት ወደኋላ አንልም። ከደህንነትና ከጸጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮቻችን በዘላቂነት እንዲቀረፉ የብዙ አካላት ርብርብና ተናብቦ መሥራትን እንደሚጠይቅ ምንም ጥርጥር የለውም። እኛኑ ለሚያሸብሩና እኛኑ ለሚያሰቃዩ ጠላቶች ሕዝብ ምሽግ ከሆነ የጸጥታ አካላት ጥረት ብቻውን መፍትሔ አያመጣም። ስለዚህ እያንዳንዱ ዜጋ፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሚዲያና ሌሎች የሕዝብ ዐይን፣ ጆሮና ክንድ ሆናችሁ የምትሰሩ አካላት ከጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በመግባባት ለመሥራት በሙሉ ልብ ቁርጠኞች መሆን አለባችሁ።

በለውጥ ጎዳና ላይ በመጓዝ ዴሞክራሲን የሚገነቡ ሀገራት በሁለት ጫፍ መካከል የሚቆም ፈተና ይገጥማቸዋል። በአንድ በኩል ዴሞክራሲያዊ ባህልን መገንባት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሀገርንና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በጥብቅ ርምጃዎች ማስከበር ነው። ዴሞክራሲያዊ ባህልን ለመገንባት ስንነሣ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያስከብሩ ጥብቅ ርምጃዎችቻን በነጻነትና መብት ስም እንዳይላሉ፤ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር የምንወስዳቸው ጥብቅ ርምጃዎችም ዴሞክራሲያዊ ባህልን እንዳያቀጭጩ በሚዛን መንቀሳቀስ ይገባናል። ሁለቱን በሚዛን ለማከናወን ደግሞ የእያንዳንዱ ዜጋ፣ ተቋም፣ ፓርቲ፣ ቡድን፣ ወገን፣ የሚጠበቅበትን ማድረግ አለበት። የሕግና የጸጥታ ተቋማትም ሕገ መንግሥታዊና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።

See also  ኑ ቀብዳችሁን ውሰዱ፤ ለአሸባሪውም አጥልቁለት - ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ

በመሆኑም ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ቡድኖችንና ግለሰቦችን፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሠራጨት ሕዝብና ሀገርን ሰላም
የሚነሡ አካላትን፣ በሕገ ወጥ መንገድ ታጥቀው የሕዝብን ሰላም የሚነሡና ለታሪካዊ ጠላቶቻችን በተላላኪነት የሚያገለግሉ
ቡድኖችን፣ በመሬት ወረራና በተለያዩ የሥርቆትና የማታለል ተግባራት የተሠማሩትን፣ የትራንስፖርትና ሕዝብ እንቅስቃሴዎችን የሚያውኩትን፣ የልማትና የኢንቨስትመንት ተግባራትን የሚያደናቅፉትን፣ በጥናትና በመረጃ በመለየት አስፈላጊው ሁሉ ሕግ
የማስከበር ርምጃ እንዲወሰድ የደኅንነት ምክር ቤቱ ወስኗል። በተመሳሳይ የምግብና ልዩ ልዩ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር በሕገ ወጥመንገድ ምርት የሚያከማቹ፣ በኮንትሮባንድ መልክ ነዳጅና ሌሎች ምርቶችን ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚያሾልኩ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ተገቢው እርምጃ ይወሰዳል።

ወላጆች ልጆቻችሁን፣ ሽማግሌዎች ወጣቶቻችሁን፣ የሃይማኖት አባቶች ምእመኖቻችሁን፣ የፓርቲ መሪዎች አባሎቻችሁን፣ የጎሳ መሪዎች ወገኖቻችሁን፣ በመምከር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከግጭትና ከሽብር ራሱን አርቆ፣ ለሰላምና ለሀገር ደኅንነት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ እንድታደርጉ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያችንን እያቀረብን፣ ከዚህ በተቃራኒው ተሰልፎ የሚገኝ ማንኛውም ሰው፣ አካልና ቡድን ላይ ሕጉ የሚፈቅደውን ተገቢውን ሕግና ጸጥታ የማስከበር ሥራ የምንሠራ መሆኑን እናሳውቃለን።

መጪው ቀናት ለሕዝበ ክርስቲያኑም ሆነ ለሕዝበ ሙስሊሙ የበዓላት ሰሞን እንደመሆኑ መጠን አማኞች በትብብርና በመግባባት የጠላቶቻችንን ፍላጎት በማክሸፍና የጋራ ደህንነታችንን በማረጋገጥ እንደ ሀገር የተሳካ ጊዜያት እድንናሳልፍ የደህንነት ምክር ቤቱ አበክሮ ይጠይቃል።

የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት
ሚያዚያ 14፣ 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Leave a Reply