«አጋር ጅርጅቶች ለትግራይ የሚያቀርቡት የህክምና ቁሳቁስ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ አለባቸው»

– እንደ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ያሉ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች የሚያሰራጩት መረጃ መሰረት ቢስ ነው፣

ለትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁስ እያቀረቡ ያሉ አጋሮች የሚያቀርቡት ቁሳቁስ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ እንዳለባቸው የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ገለጹ።

ኮሚሽነሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለአጋሮች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል።

አጋሮቹ በተለይም በጤና ዘርፍ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት መድሃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስና አልሚ ምግብ በአየርና በየብስ ትራንስፖርት ተደራሽ እያደረጉ እንደሚገኙ የሚታወቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ በተደረገ 44 ያህል በረራ ለህክምና የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና አልሚ ምግቦችን ማድረስ መቻሉን አንስተዋል።

የመድሃኒትና የህክምና አቅርቦት እጥረት በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ የሚያጋጥም ክስተት እንደሆነ ገልጸው፤ የትግራይን ጉዳይ ፖለቲካዊ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ችግሩን የትግራይ ክልል ብቻ አድርገው ማንጸባረቃቸው ስህተት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁስን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሆነ ተናግረው፤ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የህክምና ቁሳቁስንና አልሚ ምግብ ተደራሽነትን ለማሳደግ በሳምንት ሁለት ጊዜ የነበረውን የአዲስ አበባ መቀሌ በረራ ላይ ማሻሻያ መደረጉን አስታውሰዋል።

ወደ ክልሉ እየተጓዘ ያለው የህክምና ቁሳቁስና አልሚ ምግብ ለጤና ተቋማት በተለይም ለሆስፒታሎች በቂ እንደሆነ የገለጹት አቶ ምትኩ፤ እንደ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ያሉ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች የሚያሰራጩት መረጃ መሰረት የሌለው እንደሆነ ገልጸዋል።

“እጥረት አጋጥሟል ከተባለ ከጀርባ የሚፈጸም አንድ የሆነ ሌላ ጉዳይ ሊኖር ይችላል” ብለዋል።

ይህም እየቀረበ ያለውን የህክምና ቁሳቁስ ወስዶ ለሌላ ዓላማ የሚያውል አካል እንዳለ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ጉዳይ ደግሞ መጣራትና መመርመር ይኖርበታል በማለት ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ መድሃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስና አልሚ ምግብ በማቅረብ ዙሪያ እየሰሩ ያሉ አጋሮች ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል አቅርቦታቸው ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

See also  ከሃይል ሽኩቻው በተጨማሪ የዩክሬይን! ቁልፍ ጉዳዮች

Leave a Reply