ኦሮሚያ በበጋ መስኖ 27 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይጠበቃል

– በመኸር ምርት ዘመን ከ48 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ስንዴ ለማምረትም ታቅዷል

በኦሮሚያ ክልል በሁለት ዙር የበጋ መስኖ ብቻ 27 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለማምረት እየተሰራ መሆኑን ኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ ።

በመኸር ምርት ዘመን 48 ሚሊዮን 259 ሺህ 89 ኩንታል የስንዴ ምርት ለማምረት መታቀዱም አመልክቷል።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የበጋ ስንዴ ምርት ኢንሼቲቪ አስተባባሪ አቶ ጠሃ ሙሜ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከክልሉ በበጋ መስኖና በመኸር ምርት ዘመን ከፍተኛ የስንዴ ምርት በማምረት እንደ አገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። በበጋ መስኖ ብቻ 27 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማምረት እየተሰራ ነው።

በበጋ መስኖ 350ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ 355 ሺህ 106 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አመልክተው፤በአሁኑ ጊዜም በበልግ ዝናብ የሚታገዝ ሁለተኛ ምዕራፍ የመስኖ እርሻ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንና እስካሁንም 257 ሺህ 800 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፍን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።

እስከ በልግ መጨረሻ ድረስ አፈጻጸሙ እንደሚጨምር ገልጸው፤ ዕቅዱን እንደሚሳካም በመጀመሪያ ዙር የበጋ መስኖ የተመዘገቡ ዉጤቶች አመላካች መሆናቸዉን አስገንዝበዋል ።

በክልሉ የመኸር ምርት ዘመን ሳይጨምር በሁለት ዙር የበጋ መስኖ እርሻ ብቻ 27 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ምርት ለመሰብሰብ ጥሩ አፈጻጸም ላይ ይገኛል ብለዋል ።

አርሶ አደሩ የስንዴ ምርታማነት እንዲጨምር ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችን እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን አውስተው፤ በሁለቱም ዙር የበጋ መስኖ እርሻም 448 ሺህ 293 ኩንታል ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ ማቅረብ መቻሉን አብራርተዋል ።

በቢሮዉ የክረምት ሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ በየነ ማሞ በበኩላቸዉ ክልሉ በዘንድሮ የመኸር ምርት ዘመን ብቻ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል በመሸፈን 48 ሚሊዮን 259 ሽህ 89 ኩንታል ስንዴ ምርት ለማምረት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።

ዕቅዱን ስኬታማ ለማድረግም ምርትና ምርታማነትን በሚያሳድጉ ግብዓቶች አጠቃቀም፣ አዘገጃጀትና በመስመር መዝራት ዙሪያ ላይ የግንዛቤ የማስጨበጫ ሥልጠናዎች ለአርሶ አደሩ በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል ።

See also  "አሸባሪው ትህነግ"በማይጠብሪ፣ በዋግ በአበርገሌ አከባቢ፣ በራያና በአላማጣ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባታል

የማዳበሪያ እጥረት እንዳይከሰት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመው፤ የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም ወገን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ።

እንደ አገር የምግብ ዋስትና በአስተማማኝ መልኩ ማረጋገጥ የሚቻለው የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማት ሲጨምር መሆኑን አስታውቀዋል።

ገመቹ ከድር

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 17 /2014

Leave a Reply