የከተማ መሬትን በወረራ ለመያዝ ጥብቅ ደን በጨፈጨፉ 97 ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

የከተማ መሬትን በወረራ ለመያዝ አስበው በመደራጀት የመንግስት የሆነውን ጥብቅ ደን በጨፈጨፉ 97 ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

በእነ ጌጡ ቀለብ ሞገስ መዝገብ 97 ሰዎች ላይ ክስ የመሰረተው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዐቃቤ ሕግ ነው፡፡

የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ተከሳሾች በዋና ወንጀል ድርጊት ተካፋይ በመሆን መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት ከ12፡00-1፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ክልል ውስጥ ልዩ ቦታው ሳሪስ አዲሱ ሰፈር ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስትያን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይዞታው በመንግስት ስር የሚተዳደር ስፋቱ ሶስት ሄክታር የሆነ ጥብቅ ደን ውስጥ ዛፍ ለመቁረጥ የሚያገልግሉ መሳሪያዎች ማለትም መጋዝ፣ ገጀራ፣ ማጭድ እና መጥረቢያ ይዞ በመግባት ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳያገኙ ዛፎችን የቆረጡ በመሆኑ በፈጸሙት የጥብቅ ደን መቁረጥ ወንጀል ተከሰዋል ይላል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በክሱ የእያንዳንዱን ተከሳሽ የወንጀል ተሳትፉ አትቷል፡፡

ተከሳሾች በችሎት ቀርበው የዐቃቤ ህግ ክስ እንዲደርሳቸው ተደርጎ ክሱ በችሎት የተነበበ ሲሆን በክሱ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው በአብዛኛው ያመኑ ሲሆን የተወሰኑቱ ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ያላመኑ በመሆኑ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለሚያዝያ 19 ቀን 2014 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡

Via Attorney general

Leave a Reply