የፑቲን ቀጣይ ዒላማ – ኦዴሳ የወደብ ከተማ

የፖለቲካ 101- ትንተና

የማሪፖል ከተማ ነገር ያለቀለት መሆኑን በርካታ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ አዞቪስታል ከተባለው የኢንዱስትሪ መንደር ውጭ ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በሩሲያ እጅ ገብታለች፡፡ በዚህም ምክንያት በርካቶች የሩሲያ ቀጣይ መዳረሻ የት ይሆን? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡

የሩሲያ ማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሩስታም ሚኒንካዬቭ “ሩሲያ በምስራቅ እና ደቡብ ዩክሬይን የሚገኙ ቦታዎች ትቆጣጠራለች” በማለቱ አሁን ዕቅዱ ግልጽ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ቀጣዩዋ መዳረሻ የጥቁር ባህር ፈርጥ፣ የወደቦች ማዕከል የሆነቸው ታሪካዊቷ ኦዴሳ ከተማ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዩክሬይናውያንም ሆነ ለሩሲያ ስትራቴጂካዊ በመሆኗ በሁለቱም በኩል የሞት ሽረት ጦርነት ታስተናግዳለች ተብሎ ይጠበቃል።

የከተማዋ ስትራቴጂካዊ ጥቅም – ለሩሲያ

  • ኦዴሳ የወደብ ከተማ የተቆረቆረችው በሩሲያ ኢምፓየር ንግስት ታላቋ ካትሪን ሲሆን ታሪኳ ከሩሲያ ታሪክ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው፡፡ በሶቪየት ዘመን የሶሻሊስት ሪፐብሊኩ ትልቋ ወደብ እንዲሁም የባህር ሀይል ቤዝ ነበረች። በተጨማሪም በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የከተማዋ ነዋሪ ለናዚ ባሳየው አልገዛም ባይነት ምክንያት እንደ ስታሊንግራድ፣ ሌኒን ግራድ እና የክሬሚያዋ ሴቫስቶፖል ሁሉ “ጀግና ከተማ” የሚል የክብር ማዕረግ ተሰጥቷታል። ፑቲን በልቡ የሚመላለስ “ዳግማዊ ሶቪየት” ህልም ካለው ኦዴሳን ከመቆጣጠር የሚበልጥ ትልቅ ፕሮጄክት ሊኖረው አይችልም ማለት ነው፡፡
  • የኦዴሳ ወደብ በሩሲያ እጅ ገባ ማለት ፑቲን ድፍድፍ ነዳጅ፣ የተፈጥሮ ጋስ፣ የምግብ ዘይት፣ ብረት፣ እህልና ሱኳር የመሳሰሉ ምርቶች የሚንቀሳቀሱበትን የጥቁር ባህር የንግድ መስመርን ሚቆጣጠርበት በር ወለል ብሎ ይከፈትለታል፡፡
  • ሌላው ኦዴሳ ወደቀች ማለት ሩሲያ በሞልዶቫ የሚገኙትን ሩሲኛ ተናጋሪ ክልሎች በቀጥታ ታገኛለች። ይህም ክልል የመገንጠል ዝንባሌ ያለው በመሆኑ ሩሲያ ልትጠቀልለው ትችላለች የሚል ስጋት አለ፡፡ ሞልዶቫ የኔቶ አባል አለመሆኗን ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ ሩሲያ የአውሮፓን ካርታ መቀያይሯን ትቀጥላለች ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቀጣይ ሌላ ትኩሳት ሊያመጣ ይችላል።

የከተማዋ ስትራቴጂካዊ ጥቅም – ለዩክሬይን

  • አንድ ሚሊየን የሚጠጋ ነዋሪ ያላት ከተማዋ የሶስት ወደቦች ባለቤት ስትሆን 65 በመቶ የዩክሬይንን የባህር ንግድ ታቀላጥፋለች። ዩክሬይን ይህን ወደብ ካጣች ኢኮኖሚዋ ላይ የሚያርፈው ብርቱ ዱላ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ የሚያስከትል ይሆናል፡፡ IMF ቀድሞውኑም በጦርነቱ ምክንያት የዩክሬይን ኢኮኖሚ በ35% እንደሚላሽቅ ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
  • ሌላው ሩሲያ በ2014 ሴቫስቶፖል የባህር ሃይል ቤዝን ከክሬሚያ ጋር መውሰዷን ተከትሎ ኦዴሳ የዩክሬይን የባህር ሃይል ዋና ማዘዣ ነች። ስለዚህ ከተማዋ በሩሲያ እጅ ከገባች ዩክሬይን በ10 አመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የባህር ሃይል ዋና ቤዟን ትቀይራለች ማለት ነው፡፡
  • ከተማዋ ከዩክሬይን እጅ ከወጣች ጦርነቱ ቢጠናቀቅ እንኳን አገሪቷን መልሶ መገንባት አስቸጋሪ ይሆናል ማለት ነው። አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎች በባቡር አማራጭ ብቻ ተመላልሰው ዩክሬይንን ዳግም ሊያቆሙ አይችሉም።
  • በአጠቃላይ ኦዴሳ ላይ የሚገኝ ድል የጦርነቱን አሸናፊ የሚጠቁም ነው።

አሁን ከተማዋ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች??

  • አሁን ላይ በደቡብ ዩክሬይን ሩሲያ እጅ ያልገቡ ትላልቅ ከተሞች ማይኮላይቭና ኦዴሳ ብቻ ናቸው፡፡ የሩሲያ ጦር ከኦዴሳ በስተምስራቅ 120 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ማይኮላይቭ ተጠግቶ ነው ያለው፡፡ የሩሲያ ጦር ኦዴሳን ለመቆጣጠር ባለው ቁርጠኛ ፍላጎት የተነሳ ከአየር እና እግረኛ ጦሩ በተጨማሪ እጅግ ዘመናዊ የባህር ሀይሉንም ወደ ስፍራው አንቀሳቅሷል።
  • በተጨማሪም ከሰሞኑ በተደጋጋሚ ጊዜ የሩሲያ ሚሳሎች ኦዴሳ ከተማ ሲደበደቡ ውለዋል፡፡ መሰረተ ልማቶቿ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን በከተማዋ የኢንዱስትሪ ሰፈር እሳት እና ጥቁር ጭስ በግልጽ ይታይ ነበር፡፡
  • የዩክሬይን ጦር በበኩሉ ከተማዋን አሳልፎ ላለመስጠት በዙሪያዋ ጠንካራ ምሽጎችን የቆፈረ ሲሆን ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ መንገዶች ሁሉ ላይ መሰናክሎች አስቀምጧል። ነዋሪው ላይ ሰዓት እላፊ የተጣለ ሲሆን ወደቦቹም አገልግሎት እንዲያቆሙ ተደርገዋል። ፕሬዝዳንት ዜሌኒስኪ የከተማዋን ሲቪል አስተዳደር በወታደራዊ ዕዝ በመተካት ከተዋጊዎች በቀር ሰላማዊ ዜጎች ከከተማው እንዲለቁ አዘዋል። በተጨማሪም በከተማው የተተከሉት አየር መቃወሚያዎች የተወሰኑትን ሚሳሎች በአየር መቃወሚያቸው እያመከኑ መሆኑንም የዩክሬይን ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ እጣ ፈንታ በቀጣይ የሚታወቅ ይሆናል።
~ ፖለቲካ 101 ~

አገራዊና አለም አቀፍ ዘገባዎችን ለማግኘት እንዲሁም የፖለቲካ አድማሶን ለማስፋት ገጾቻችንን ይወዳጁ

Facebook – https://www.facebook.com/Politics-101Ethiopia-101653112504170

Leave a Reply