ሃገራዊ ምክክሩ – ሃገሪቱ ካለችበት ዉጥረት ተላቃ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ..

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሁለት ወራት ያከናወናቸዉ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች ለሃገራዊ ምክክሩ ስኬት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን የኢፊዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኮሚሽኑ የተግባር ዕቅድ ዙሪያ በኢፊዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁሉም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ጋር ዉይይት አካሄዷል።

በዉይይት መድረኩ ላይ የኢፊዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ: የሁሉም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና የኮሚሽኑ 11ዱም ኮሚሽነሮች ተሳትፈዋል።

የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርአያ በኮሚሽኑ የተግባር ዕቅድ ዙሪያ አጭር ዘገባ አቅርበዋል።

በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ: በዝግጅት ምዕራፍ: በክንዉንና በምክክር ዉጤቶች መተግበሪያ ምዕራፍ ዙሪያ ባለፉት ሁለት ወራት በተሰሩና ወደፊት ሊሰሩ በታቀዱ ተግባራት ዙሪያ ኮሚሽነሩ ፕ/ር መስፍን አርአያ ለቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል።

የኮሚሽኑን ጽ/ቤት ከማደራጀት: የኮሚሽኑን ጽ/ቤት ኃላፊ ከመሾምና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን በጊዜአዊነት ከመመደብና በኮሚሽኑ አስፈላጊነት ዙሪያ የኮሚሽነሮችን ግንዛቤ ከማሳደግ ረገድ በርካታ ስራዎች መሠራታቸዉን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ወደ ስራ በገባበት አንድ ወር አካባቢ ለሃገራዊ ምክክሩ ስኬት ጉልህ ሚና ያላቸዉ የተለያዩ ሐይማኖት አባቶች: የባህል መሪዎች: የሃገር ሽማግሌዎች: አባቶች: እናቶችና ወጣቶች በተገኙበት ጸሎትና ቡራኬ መደረጉን የተናገሩት ኃላፊዉ በሃገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ዙሪያ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ዉይይት መካሄዱን ገልጸዋል።

ለሃገራዊ ምክክሩ ስኬት ግብአት የሚሆኑ ሃገር በቀል ዕዉቀቶችን የማሠባሰብ: የመከባበርና መቻቻል ዕሴቶችን የማጠናከር ስራዎች እየተሠሩ መሆናቸዉን የተናገሩት ኮሚሽነሩ የአወያዮችና የአመቻቾችን ምልመላ: የዉይይት ጽንሰ ሃሳብና የአጀንዳ ቀረጻ: የምክክሩ ይዘት: ሂደትና ቅርጽን አስመልክቶ ሃገር በቀልና የተለያዩ ሃገራት ልምድ እየተቀመረ መሆኑም ተናግረዋል።

የቅድመ ዝግጅትና የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች ዉጤታማነት ለምክክር ሂደቱና ለምክክር ዉጤቱ ስኬታማነት ትልቅ መሠረት መሆናቸዉን የተናገሩት ኮሚሽነሩ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደዉ ምክክር ግልጸኝነት የሠፈነበት: አሳታፊና ትዉልድ ተሻጋሪ እንዲሆን እየሠራን ነዉ ብለዋል።

ኮሚሽነሩ እስካሁን ድረስ በታዩ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች ዙሪያ ማብራሪያ የሠጡ ሲሆን የአረዳድ ችግር: ጥርጣሬ: ስራዉ ቶሎ ያልቃል የሚል ጉጉትና የተከማቸ አጀንዳ መኖርን እንደ ተግዳሮት አንስተዋል።

የሃገሪቱ ህዝብ የጥይት ድምጽ በቅቶናል: ሞትና መፈናቀል ሠልችቶናል: ሠላምና ልማት ይሻለናል: ችግራችንን በዉይይት እንፍታ የሚል አቋም መያዙ ደግሞ እንደ መልካም አጋጣሚ ተነስቷል።

በቀረበዉ ሪፖርት ዙሪያ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች የተለያዩ ሃሳቦችንና አስተያየቶችን አንስተዋል።

በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ የተሰራዉ ስራ አበረታች መሆኑን ያነሱት የምክር ቤቱ አባላት ከምክክር ሂደቱ በፊት የተሰሩትን ስራዎች ለሕዝብ ማሳወቅ እንደሚገባም አንስተዋል።

የፖለቲካ ፖርቲዎች: ሚዲያዎችና ማህበራዊ ሚዲያዎች የሥነ ምግባር ህጎችን ሊያከብሩ ይገባል ያሉት አባላቱ ዬትኛዉም አጀንዳ ከህዝብና ከሃገር ስለማይበልጥ ሁሉም አካል ለሃገር ሉአላዊነት ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

የሃገራዊ ምክክሩ ፍኖተ ካርታን ጨምሮ ደንቦች: መመሪያዎችና የሥነ ምግባር ደንቦች በአጭር ጊዜ ተጠናቀዉ ተግባር ላይ ሊዉሉ ይገባልም ብለዋል።

ሕዝቡ ሃገራዊ ምክክሩ መች ይካሄዳል የሚል ከፍተኛ ጉጉት ስላለዉ የቅድመ ዝግጅትና የዝግጅት ስራዎችን ከህዝብ ፍላጎት ጋር አጣጥሞ መስራት ይገባል ብለዋል።

በቀረቡት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ዙሪያ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርአያና ሌሎች ኮሚሽነሮች ምላሽ ሰጥተዋል።

በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ የተሰሩ ስራዎች ለሃገራዊ ምክክሩ ስኬት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን የተናገሩት የኢፊዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ምክር ቤቱ ለምክክሩ ስኬታማነት ተገቢዉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት ሃገር መሆኗን የተናገሩት አፈ ጉባኤዉ ሃገሪቱ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያን የማይመጥን ባለመሆኑ ሃገሪቱ ካለችበት ዉጥረት ተላቃ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች: ሚዲያዎች: ምሁራን : የሃይማኖት መሪዎችና መላዉ የሃገሪቱ ህዝብ በቅንነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል። via -OBN

Leave a Reply