የምስ.አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ስትራቴጂክ ከፍተኛ የአማካሪዎች መድረክ በአ.አ በመካሄድ ላይ ነው

በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ውይይቱን ያስጀመሩት የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር አብርሀም በላይ በምስራቅ አፍሪካ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን ማበጀት እንደሚገባና ለዚህም የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ስትራቴጂክ ከፍተኛ የአማካሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሀይል የስትራቴጂክ ከፍተኛ የአማካሪዎች ቡድንን እንደ ተቋም ማደራጀቱ ለሰላም ግንባታ ስራው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለፁት ዶ/ር አብርሀም፤ አፍሪካውያን ያሉንን በጎ እሴቶችና ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም ለሰላም መረጋገጥ ማውል ይገባናልም ብለዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሀይል ዋና ዳይሬክተር ብ/ጄ ጌታቸው ሽፈራው፤ በቀጠናው የሚታዩ የፀጥታ መደፍረሶችን ለመከላከል የተለያዩ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው፤ በቀጠናው ግጭቶች ሳይፈጠሩ በፊት ለመከላከል የሚያስችል ስልት ተነድፎ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የቀድሞ የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ዶሚቲን ንዳይዜ ጨምሮ ከአስሩ የምስራቅ አፍሪካ የተውጣጡ የቀድሞ አምባሳደሮችና ከፍተኛ የጦር አመራሮች በአባልነት የተካተቱበት የስትራቴጂክ ከፍተኛ የአማካሪዎች መማክርቱ በቀጠናው የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመከላከል በሚቻልበት ዘዴ ላይ ምክረ ሀሳቦችን ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የሀገር መከላከያ ሰራዊት በማህበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡

(ኢ ፕ ድ)

You may also like...

Leave a Reply