“ሕገወጦች በድንጋይ ከሰል አመላላሽ አሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው”

ሕገወጦች በድንጋይ ከሰል አመላላሽ አሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ በመሆኑ በሲሚንቶ ምርት አቅርቦት ላይ ስጋት መደቀኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች አስታወቁ።

 አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጣቸው ምርቱን ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማቅረብ እንቸገራለን ሲሉ አሽከርካሪዎች ገልጸዋል።

ከድንጋይ ከሰል ምርት ወደሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያመላልሱ አሽከርካሪዎች በህገወጦች ምክንያት ዘረፋና የግድያ ሙከራ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተናግረዋል።

በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ችግሩ የከፋ መሆኑን የጠቆሙት አሽከርካሪዎች፤ በየቦታው ገንዘብ የሚጠይቁ ወጣቶች ተበራክተዋል ሲሉ በምሬት ገልጸዋል።

የኬላ ክፍያ በሚል ስም ገንዘብ ካልከፈላችሁ አታልፉም የሚሉ ወጣቶች በመበራከታቸው ለአንድ ተሳቢ ተሽከርካሪ በድምሩ እስከ 20 ሺህ ብር እየከፈሉ እንደሚያልፉ የከባድ መኪና አሽከርካሪው በቀለ ሻፊ (ስማቸው የተቀየረ) ተናግረዋል።

የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችእኔ ለሕይወቴ ስለምሰጋ በየቦታው የሚጠብቁ የአካባቢው ወጣቶች ነን የሚሉ ህገወጦች ሲያጋጥሙኝ አንድ ሺህም ሆነ ሁለት ሺህ እየከፈልኩ አልፋለሁ፤ እንቢ ያሉት ግን የፊት መስታወታቸውን ከመስበር ባለፈ በጩቤ ተወግተው ተጎድተዋል ሲሉ ለኢፕድ አስረድተዋል።

በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፏፏቴና 42 የተባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል አርጆ፣ አቤል ፣ ጅርማ፣ ጊምቢና ነጆ አካባቢዎች ለአሽከርካሪዎች ምሬት ዋነኛ ምንጭ ከሆኑ ስፍራዎች መካከል ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዘረፋውና የደህንነት ስጋቱ በማየሉ የድንጋይ ከሰሉን ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማቅረብ እንቸገራለን ያሉት አሽከርካሪው፤ ይህም በሲሚንቶ ምርት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርምና ከወዲሁ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የድንጋይ ከሰል ምርት ወደሲሚንቶ ፋብሪካዎች በማመላለስ ሥራ ላይ የተሰማሩት ጃንቦ ተዘራና አለሙ አሸናፊ በበኩላቸው፤ ህጋዊ ደረሰኝ ከሚሰጠው ባለፈ በየአካባቢው ያሉ ህገወጦች ገንዘብ ተቀብለው ህጋዊ ደረሰኝ እንኳን ስለማይሰጡ አሽከርካሪዎች ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ተናግረዋል።

ከአርጆ ከተማ እስከ ድንጋይ ከሰል ማውጫው ስፍራ ድረስ በተዘረጋው የፒስታ መንገድ ላይ በየመንደሩ ወጣቶች ተሰባስበው ገንዘብ አምጡ ይሉናል ሲል አሽከርካሪዎቹ ሁኔታውን አስረድተዋል።

ደረሰኝ ካልሰጣችሁኝ በየቦታው የምጠየቀውን አልከፍልም ያለ አሽከርካሪ ድብደባና እንግልት ይደርስበታል። ገጀራና ህገወጥ መሳሪያ ይዘው የሚያስፈራሩም በርካታ ናቸው ብለዋል።

አሽከርካሪው ጃምቦ ተዘራም እኔ “ሲኖ ትራክ” የተሰኘ ተሽከርካሪ ስለምይዝ ቢያንስ በየቦታው የምከፍለው ሲደመር አስር ሺህ ብር ደርሷል፤ ተሳቢ ተሽከርካሪዎች ደግሞ እጥፉን ይጠየቃሉ። አብዛኛውም ለሕይወቱ ሲል ያለውን እየከፈለ ያልፋል ሲል ተናግሯል።

ይህ ችግር በዚሁ ከቀጠለ የድንጋይ ከሰል ምርቱን በበቂ ሁኔታ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማድረስ አዳጋች ይሆናል። ይህም መልሶ የሲሚንቶ ምርት እጥረቱ እንዲስፋፋ ያደርጋል ሲል አስረድቷል።

ስለዚህ ችግሩ አገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከባድ መሆኑን በመገንዘብ የእርምት ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብሏል።

ወጣቶች ነን፤ ተደራጅተን ነው በሚል ሰበብ ውንብድና ላይ የተሰማሩትንም አደብ በማስያዝ አሽከርካሪዎችን ካላስፈላጊ እንግልትና የደህንነት ስጋት መታደግ ያስፈልጋል ሲሉ አሽከርካሪዎቹ ምክረ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የተጠየቁት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጄይላን አብዲ መረጃውን በተመለከተ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃላፊዎች ዘንድ ስልክ ደውለው ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል። ስለዚህም በአሽከርካሪዎች ላይ እየተፈጠረ ስላለው ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ መስጠት እንዳልቻሉ ለኢፕድ ገልጸዋል።

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply